ወደ ማኅበራዊ ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

 

የሚሸጡ ልጆች

ፀዳለ ክፍሌ (የንጋት ባልደረባ)

ልጆች ወልደዋል? ደሃ ነዎት? ታዲያ ለምን አይሸጧቸውም? እውነቴን’ኮ ነው። በተለይ ቀላ ብለው ድንቡሽቡሽ ያሉ ከሆኑ የደራ ገበያ አለ። የኔ ነገር ወሬውን አጋጨሁት መሰለኝ። ልጅ የሚያሸጥ ድህነት ላይ ከተደረሰ ልጁ ድንቡሼ ሊሆን እንደማይቻል ዘነጋሁት። ሰው ኑሮውን ነዋ የሚመስለው። ክፋቱ ደግሞ ዝንብ የወረረውና የሽሮ ቅል የመሰለ ልጅ ለገበያ አይመችም። ቆንጆም ቢሆን ጥቁር ከሆነ አይድከሙ። እርሶስ ቢሆን በግ እንኳን ሲገዙ ምን ቢሰባ ጥቁር ከሆነ ገሸሽ ያደርጉት የለ። እውነቴን’ኮ ነው የጥቁር በግ ዋጋ’ኮ ይቀንሳል። ስለዚህ ጥቁር ከወለዱ ተስፋ ይቁረጡ። ጥቁር ልጅ ፈጽሞ አይፈለግም። ጥቁር ዋጋ አያወጣም። ጥቁር ልጅ ተፈለገ ከተባለ መጠርጠር ነው። ከጀርባው መከራ አለ። የጦርነት፣ የረሃብ፣ የበሽታ (የፖሊዮ)፣ የልመና፣ … ማሳያ ከመሆን አያልፍም። በዚህ ረገድ ‘ዋጋ’ ያወጣል። ቢፈልጉ “ኒውስዊክ”፣ ቢያሻዎ “ዋሽንግተን ፖስት” ካሰኞትም “ታይም” መጽሔት ‘ይገዛዎታል’። በዚህ አይጠራጠሩ። በተለይ እግሩ የተቆረጠ፣ ዓይኑ የተገለበጠ፣ ሆዱ ያበጠና ፀጉሩ የተላላጠ ከሆነ ጥሩ ማሳያ ስለሚሆን “ይፈለጋል!!!”። ነጭ ድንቡሼ ሕፃን ከነዚህ ክፉ ነገሮች ጀርባ ተቀርጾ ማየት መጥፎ ሟርት አይመስሎትም?

ክፋቱ ደግሞ ይህም ዕድል ሆኖ ገበያው እሩቅ ነው። የጥቁር ፎቶው ቢላክ ይሸጥ ይሆን? አይመስለኝም። ፎቶ ዋጋ የሚያወጣው ከባህር ማዶ ወደዚህ ሲመጣ እንጂ ከዚህ ወደዛ ሄዶ ሲሸጥ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። ምናልባት ከርስዎ ልጅ የተሻለ የዋልያና ቀይ ቀበሮ ፎቶ ሳይሸጥ አይቀርም። ይባስ ብሎ ደግሞ አገር ቤትም ገበያ የለውም። የኛን ፎቶ የኛ አገር ሰው ምን ሊያደርግለት ይገዛል? ጥቁርን ጥቁር ገዝቶ ምን ይጠቅመዋል? ነጭ ደግሞ ያለምክንያት የጥቁርም ሆነ የነጭን ፎቶ አይገዛም። ባይሆን ጥቁር የነጭን ፎቶ ያለ ምክንያት ሲገዛ ያምራል አይደል? ለዚህ እኮ ነው ቀላ ቀላ ያሉ ልጆች ካሎት ገበያውን መጋራት ይችላሉ ለማለት የፈለግሁት። ቀይ ወይም ነጣ ያለ ልጅ ካሎት ወደ ገበያው ከመግባቶ በፊት ምክር ልለግሶት።

ፈገግ ብሎ ሲስቅ ፎቶ ያስነሱት፣ አፈንድዶ ሲድህ ቢሆንም ግዴለም። የአባቱን ጫማ አድርጐ ለመሄድ ሲወላከፍ ፎቶ ቢነሳም ደስ ይላል። ሚዛን ላይ ቆሞ ወደ ላይ ሲያንጋጥጥ ቢነሳም ነውር የለውም። ብቻ ልጁ ነጣ ይበል። በጀርባው ተንጋሎ በእግሮቹ የያዘውን ጡጦ በእጁ እረዳትነት ሲጠባ ቢነሳማ በልጆ ይኩሩ። በትንሽዬ የሕፃን ብልቱ/ቷ የሚሸናውን ሽንት አጎንብሶ ሲመለከት ፎቶ ቢነሳ የሚፈጥረው ደስታ ቀላል አይደለም። ሙዝና ብርቱካን እየበላም ቢሆን ያዋጣል። በተለይ በተለይማ ሁለት ነጫጭ ሕፃናት ትላልቅ ባርኔጣ አድርገው ከንፈር ለከንፈር ሲሳሳሙ ቢነሱ ገበያውን ልነግሮት አልችልም። ይህም ባይሳካ ጽጌረዳ አበባ አስይዘው ቢያስነሱትም ይሸጣል።

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ‘አደጋ’ እንዳይገጥሞት ማሳሰቢያ አለኝ። በምንም አይነት ሁኔታ … እደግመዋለሁ በምንም አይነት ሁኔታ ይህንን ድርጊት በጥቁር ሕፃን ላይ ፈጽመው ለገበያ አቀርባለሁ ቢሉ እኔ የለሁበትም። በ‘ወንጀል’ ሊጠየቁ ይችላሉ። ያም ባይሆን የአገር መሳቂያ ይሆናሉ። ለመሆኑ የት አገር ነው ጥቁር ልጅ ብልቱን እያየ ሲሸና ደስ የሚለው? እንኳን ለባዳ የወለደችው እናቱም ደስ ላይላት ይችላል። ደግሞስ ጥቁር ሕፃናት ሲሳሳሙ አስነስተው ወደ ገበያ ቢመጡ የትኛው ባለመኪና የትኛው ባለታክሲ ነው ገዝቶ መኪናው ላይ የሚለጥፈው? ፅጌረዳ የያዘ ጥቁር ሕፃን ያስጠላል አይደል? ደግሞስ የአባቱን ጫማ አድርጐ የሚወላከፍ ጥቁር ሕፃን ከተገኘ ይኮረኮማል እንጂ ምኑ ውበት ሆኖ ፎቶ ይነሳል? ጨርቁን የጣለ ‘እብድ’ ካልሆነ በቀር የርስዎ ምጥማጥ ሙዝ ሲበላ ፎቶ ስለተነሳ ገዝቶ ቤቱ ግድግዳ ላይ የሚለጥፍ ይኖራል ብለው እንዳይጠብቁ። ለነገሩ እርስዎም የእጆን ነው ያገኙት። ከጥቁር ልጅዎ ፈገግታ ይልቅ የነጭ ልጅ ሳቅ አይደል ቀልብዎን የሚሰርቀው። ታዲያ እርስዎ ያቀለሉትን አሞሌ ማን እንዲገዛሎት ይናፍቃሉ?

ጥቋቁር ልጆችዎን ልብ ብለው አይተዋቸዋል? የነጭ ልጅ ፎቶ ወረቀት ላይ ሲመለከቱ’ኮ ይስሙታል። የእናቱን ፎቶ እንኳን እንደዚህ በፍቅር አይስምም። ለነገሩ’ኮ ‘ባለጌው’ እርስዎ እራስዎ ነዎት - ብስኩት የገዙለት ይመስል ቢራና አረቄዎን ቀራርመው ወደ ቤት ሲገቡ እንደብቅል ከተሰጣው የነጭ ሕፃናት ፎቶ ገዝተው ይገቡ የለም? መንፈሣዊ ባርነቶን ለልጆችዎ ሲያወርሱ ለአፍታ እንኳን ትዝ አይሎትም።

እራስዎ የሰለቡት የልጅዎ ሕሊና የርስዎን ፎቶ ማየትና መሳም ቢጠላ ምን አዲስ ነገር አለው? ከፖስት ካርድ አቅም እንኳን ተሻምተን የምንገዛው ነጭ ካለበት ነው። አሣታሚውስ ቢሆን ጥቁር አትሞ ለምን ይከስራል? ባለ ካሜራውስ ቢሆን ምን በወጣው ጥቁር ላይ ያነጣጥራል። መክሰርን ማን ይፈልጋል። ጥቁርነት አክሳሪ ነው አይደል? አሁን ማን ይሙት አንዱ ‘ደፋር’ ተነስቶ ቆንጆ ቆንጆ ጥቋቁር ሕፃናት በፖስተር እየሠራ ልክ እንደ ነጮቹ ሕፃናት መንገድ ዳር ዘርግቶ ለመሸጥ ቢነሳ ምን የሚያጋጥመው ይመስሎታል? መገመቱ ራሱ ይከብዳል አይደል? ፎቶ እያዞረ ለሚሸጠው ቢሰጠው መቼም በሳቅ ፈርሶ እንደሚሞት አይጠረጠርም።

ስንት አይነት ሞት አለ ጃል? እባክዎትን ዘረኝነትን እያቀነቀንኩ እንዳልሆነ በቅን ልቦና ይመኑኝ። አጓጉል መበለጥ ግን አይከነክንም?

ለመሆኑ እንዴትና በየት በምን ሳቢያ ይሆን እነዚህ የሚሸጡ ነጫጭ ሕፃናት ‘የሚገቡልን’? እርግጥ ነው ሕፃናት ደስ ይላሉ። ከገረመን አይቀር በደንብ ይግረመንና የሚሸጡት የሕፃናቱ ፎቶ ብቻ አይደሉም። ታሪክ ያላቸው ታዋቂ ሰዎች ፎቶ በዓለም ዙሪያ መሸጡ የተለመደ ነው። ነውርም አይደለም። እኛ ግን ማን እንደሆነ የማናውቀውና “ደስ አለኝ” በሚል ስሜት ብቻ የነጭ ፎቶ የምንሸምተው በምን ሂሳብ ነው?

ኩሩ ህዝቦች አይደለንም እንዴ? ታዲያ ለምን እራሳችንን በራሳችን እየገዘገዝን የልጆቻችንን መንፈስ ለምርኮኛነት እናዘጋጃለን?

 

ወደ ማኅበራዊ ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

 

 

Hosted by www.Geocities.ws

1