ወደ አስተያየት/ትችት ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

 

እኛ እነማነን?

ዘላለም በእምነቱ (የንጋት ባልደረባ)

መልሱ ግልጽ ነው። “ኢትዮጵያዊ ነን”። ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ በምትባለው አገር ስንኖር የጋራ ቤታችን ናት። በደስታዋ እንደሰታለን። በኀዘኗ እናዝናለን። አንዳንዴ ችግር የጋራ፣ ደስታ የግል የሚሆንበት ታሪካዊ አጋጣሚ ባይጠፋም። ለዚህም ቢሆን ተጠያቂዎች እኛው ነን። ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ፖለቲካዊም ሆኑ ማኅበራዊ ክስተቶች ጣታቸውን የሚቀስሩበት አቅጣጫ ግለሰብ፣ መንግሥት፣ ድርጅት፣ ቡድን፣ … እየሆነ ብዥታ ውስጥ ይከቱናል እንጂ ዓለም እኛን የሚያውቀን ኢትዮጵያውያን መሆናችንን ነው። ብዙ ምክንያት ኖሮን ለችግራችንም ሆነ ለድህነታችን እርስ በርስ ብንካሰስም ለመካሰሳችንም ተጠያቂነቱ ከራሳችን ላይ አይወርድም። በዚህ አጋጣሚ አንድ ገጠመኜን ላንሳ።

ኋላቀር ስለሚባሉትና በተለይም ስለአፍሪካ አገሮች ሦስት ሆነን ስንወያይ አንዱ ጓደኛችን “ለዚህ ሁሉ ኋላቀርነት መንስዔው ቅኝ ገዢዎች ናቸው” በማለት አጥብቆ ይከራከር ነበር። ከዚህም አልፎ “… እኛ አፍሪካውያን በስልጣኔም ቢሆን ቀደምት ነበርን …” እያለ ሲተርክ አልዋጥ ያለው ጓደኛዬ “በሁሉም እንበልጣቸዋለን ካልክማ ቀድሞውኑ አለመወረር ነበረብን” ሲል መልሶለታል። አዎን መወረር የውድቀት በር ሊከፍት ይችል ይሆናል። በሌላም በኩል መወረሩ ጥንትም ቢሆን ደካማነትን ይመሰክራል።

ይህን ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም። ደኸየን፣ ተራብን፣ ኋላ ቀረን፣ … ባልን ቁጥር ተጠያቂ ወገንና ለዘመናት ተቀርፎ የማያልቅ ምክንያት መደርደር በግሌ ባዶ ገልቱነት ይመስለኛል። ከዚህ እምነቴ በመነሳት እንደ አገር ወደራሳችን ኢትዮጵያ ስንመጣ ደግሞ ሚሊዮን አይነት መከራከሪያ ነጥብና ቁጥር ስፍር የሌለው ምክንያት ብንደረድርም ለሁሉም ነገር ተጠያቂዎቹ እኛ ኢትዮጵያውያን ከመሆን የሚያድነን አንዳች ነገር የለም። ምክንያቶቹ እውነት ሊመስሉና ሊሆኑም ይችላሉ። እኒያ ምክያቶች ከመፈጠራቸው በፊት በአርቆ አስተዋይነት ለመመከት አለመቻል ራሱ ከድክመት ውጭ ምን ሊያሳይ ይችላል? ተወቃሹ ኢትዮጵያዊነታችን እንጂ ግለሰብ ወይም ቡድን ወይም መንግሥት ወይም ህዝብ … እያሉ ነጣጥሎ መፈረጅ ከእምነቴ ጋር አልጣጣም እያሉኝ ነው። ፍልስፍናም በሉት ቅዠት ወይም አላዋቂነት የግል ምልከታዬ ነው። በተቻለኝ ጥቂት ነገር ልበል።

በአሁኑ ወቅት ብቻ ሳይሆን ባለፉት መንግሥታትም ሆነ በዘመናት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የነበረውን (ታሪክ) ስንፈትሽ ሁሉም መንግሥታት ደጋፊና ተቃዋሚ አጥተው አያውቁም። ይህ ደግሞ የሚጠበቅም ነው። ስንቃወምም ሆነ ስንደግፍ በምን መልኩ ነው የሚለው ጥያቄ እንኳን በአንድ ፅሁፍ ቀርቶ በአያሌ ጥራዞች ተተንትኖ አያልቅም። አቅሙም የለኝም። ሁሉም የየዘመናቸው እውነታ ቢኖራቸውም በሁሉም ዘመን የምንጋራው ባህሪ አልነበረም ማለት ግን አይቻልም።

እነኚህን የጋራ ባህሪያት ስንፈትሻቸው ደግሞ የማንነታችን መገለጫዎች መሆናቸውን ለማመን እንገደዳለን። ለዚህም ነው ተወቃሽና ተንጓጣጭ ወገን ከመፈረጃችን በፊት በጥልቅ ኢትዮጵያዊነትን በተጠያቂነት ለመፈረጅ የፈለግሁት። በየትኛውም ዘመን፣ በየትኛውም መንግሥት ስር ስንተዳደር ወይም ስንገዛ ተቃውሟችንም ሆነ ድጋፋችን እውነትንና አገራዊነትን ምርኩዝ ያደረገ ነው ብዬ ለማመን ይቸግረኛል። ከዘመናት ጉዞ በኋላ ‘ሰለጠነ’ በሚባለው ዘመን አስተሳሰባችን አለመለወጡ ያሳዝን እንደሆነ ነው እንጂ ተቃውሞአችንም ሆነ ድጋፋችን በውርስ ሲወራረድ የመጣበትን መልክ አለመቀየሩ እውነት ነው። የውርስ አስተሳሰባችን በዘመን ሂደት ሊቀየር ባለመቻሉ የውርስ አገራችንም ልትቀየር አልቻለችም። ይህ ከሆነ ደግሞ የአንድ አገር የመቀየር (የማደግ) ዕድል ያለው ወይም መሰረቱ የአስተሳሰብ መቀየር መሆኑ እንቶ ፈንቶ ፍልስፍና እንደርት ካላልን በቀር እውነት ይመስለኛል።

የአስተሳሰብ ለውጥ ስል በተለይ የማነሳው ነጥብ አለ። ለአስተሳሰብ አለመለወጥ አያሌ ጉዳዮችን መዘርዘር ቢቻልም ትምህርት ግንባር ቀደሙን ሚና ይጫወታል። ይህ ማለት ግን በእኔ እምነት ዛሬ ተነስተን ሚሊዮን ሰዎችን ትምህርት ቤት በመክተት ብቻ የምንገላገለው ነገር ቢሆን ኖሮ ይህንን ተስፋ ‘ተማሩ’ በምንላቸው ወገኖቻችን እንኳን ከትምህርቱ ይልቅ ውርስ እምነታቸውና የልማድና የባህል እስረኝነታቸው ጐልቶ ወይም ጠፍሯቸው የኛኑ ‘የመኃይሞቹን ቋንቋ’ ሲናገሩና ሲተገብሩ እናያቸዋለን። ይህን ባስተዋልን ቁጥር በተናጠል ተወቃሽ ወገን ከመፈለግ ይልቅ ‘ኢትዮጵያዊነትን’ መፈተሹ አማራጭ ዕድል ይመስለኛል። ምን ማድረግ ይቻላል?

የመሣፍንቱንና የነገሥታቱን ዘመን አርቀን ሳይሆን የቀረቡትን እንኳን ለመቃኘት ስንሞክር ተፃፈውም ሆነ የሚነገረው ሁሉ በአብዛኛው በግለሰቦች ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው። ጊዜ በገፋ ቁጥር ደግሞ የእነዚያ ግለሰቦች ታሪክ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ እስኪመስል ድረስ ጀግንነታቸው ጀግንነታችንን፣ ጭካኔአቸው ጭካኔአችንን፣ … እኛንም ሆነ ሌላውን እያሳመነ መጣ። ይህ በመሆኑም እነሱ ካለፉ በኋላ አፈር ሊያስገቧቸው ሲዶልቱ የኖሩትም፣ ሕያው ሆነው እንዲኖሩ የታገሉትም፣ አገርን አሳልፈው ባንዳ የሆኑትም፣ … ደግ ደጓን ታሪክ በጋራ እየተቀራመቱ ክፉ ክፉዋን እየሸፋፈኑ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር መሽሞንሞን ቀጠሉ። ይህ ሁሉ ጥቅል ነገር እንዳለ ይሁንና በየዘመናቱ የነበሩትን ተቃዋሚና ደጋፊዎች ሚና ስንፈትሽ ደግሞ ጥቂት የተለየ አገራዊ አጀንዳ የነበራቸው ባይታጡም (አናት አናታቸውን የተባሉት) የአብዛኛው ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ ግላዊ ስሜትና ፍላጐት፣ አካባቢያዊና አድሎአዊነት የተፀናወተው መሆኑ አይካድም።

ይህ ብቻ አይደለም። በሁሉም ዘመን ደግፈን ላነሳነውና ላወደስነው በእምነታችን ዘልቀንና ፀንተን እስከ ዳርቻው አንዘልቅም። በደምሳሳው ሲመለከቱት ሲወጡ ማሞገስ ሲወድቁ መሳለቅ የነገሥታቱ ዘመን (በተለይ) ሁነኛ መገለጫ ነበር ቢባል ድፍረት አይደለም። ለዚህም ሁነኛ ምሳሌ በታሪካችን ውስጥ ቴዎድሮስ ናቸው። የቴዎድሮስ አወዳደቅ የፈጠነው በውጭ ኃይሎች ብርታት ብቻ አይደለም። ይልቁንም በዙሪያቸው ተኮልኩለው የሚገዘግዟቸውና ግራ የሚያጋቧቸው ወገኖቻቸው ቁጥር ስፍር አልነበራቸውም። “አምበሣው … ጀግናው …” ሲሏቸው የኖሩት በስንኝና በቀረርቶ ሲቀኙላቸው እንዳልነበር ሁሉ፤ ‘በክፉ ቀን’ በዚያው አፋቸው “ኤድያ! እሱም ብሎ ንጉሥ፣ ከንቱ ደፋር፣ …” ለማለት ውለው አላደሩም። ሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆናቸው መዘንጋት የለበትም።

ይህ ሁሉ ይቆየንና ውርስ እምነት ብዬ ስለጠቀስኩት ነጥብ ትንሽ ልበል፦ አዎን! አገርን ከትውልድ ወደ ትውልድ ስንረካከብ አገር ብቻ አይደለም የተረካከብነው፤ ባህል፣ እምነት፣ ወግና አስተሳሰብን ሁሉ ተረክበናል። ይሁን እንጂ ለምን ሆነ? ብለን አንከራከርም። ሊሆን የሚገባው ነውና። እነሱን ለመውቀስም የምንጠቀምበት እውነት የለንም። ቢሆንም ግን ህዝብም አገርም ካለበት ሳይነቃነቅ መጪው ሂያጁን ለመንቀፍ ድፍረት አላጣንም። እኒያ የጥንቶቹ ምንም ይሁን ምን እንደጊዜያቸውና እንደእምነታቸው ኖረው አልፈዋል።

ይሁን እንጂ እነሱም ቢሆኑ በዘመናቸው ሳይንቲስቶችና የጠፈርም ሆነ የፊዚክስ ሊቃውንት አልነበሩም። ልክ እንደዛሬዎቹ እኛ ለተለያየ ሳይንስ ወለድ እውቀት ሌላውን ዓለም ሲቀላውጡ የነበሩ መሆናቸውን አለማድበስበስ ያስፈልጋል። የነገሥታቶቻችንን ደብዳቤዎች እንኳን ብንፈትሽ ‘ታሪካዊነታቸው’ ቢያስደምም ሁሉም ድጋፍና እርዳታ መለመኛ መሆናቸውን ለራስ ማመን ያስፈልጋል። ቢሆንም እንደጊዜው ኖረዋል። ይህ ራሱ በቂ ነው። እኛ ግን እንደጊዜያችን መኖርም እንደጊዜያችን ማሰብም አልቻልንም። እኛ ከዚህ ዘመን ጋር ሆድና ጀርባ ሆነን በውርስ እምነትና በትዝታ እየኖርን ነው። እኛ ግራ ገብቶናል። መፍጠርም መኮረጅም አቅቶናል። እኛ እንዳስቀመጡን የተቀመጥን የአደራ ዕቃ ሆነናል። እኛ መኩራት ብንፈልግ በእጃችን ያለው በአደራ የተቀበልነውና አደራችንንም ተወጥተን በክብር ያቆየናት ድንግል አገራችን ነች። ድንግል አገር ይዞ መራብ የሚያሳፍር ቢሆንም እኛ ግን እንኮራበታለን። ምርጫ የለንማ።

ሌላ የኩራት ምንጭ ጥሩ ብንባልም ከተፈጥሮ ጫንቃ አንወርድም። ኒያላና ዋሊያን አንድ ብለን አሞራ፣ ወፍና ቀበሮ (በሌላው ዓለም የሌሉ በሚል ፈሊጥ) ከመቁጠር አናልፍም። ያሳደግናቸው ዶሮዎች ይመስል ሳያውቁንና ሳናያቸው በየግል መኩራት መብታችን ሆኖአል።

የረሳችሁት ነገር ካለ ጨምሩ ከተባልንም የፈረደባቸው ‘ጣዖቶች’ አሉን። የአክሱም ሐውልትና የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን የመሰሉ ጥርብ ድንጋዮች ያኮሩናል። እነዚህ ሁሉ ደግሞ የኩራት ምንጭ የማንነት አሻራ መሆናቸውን የሚክድ ባይኖርም የዛሬዎቹ እኛ አንዲት ጠጠር እንዳላቀበልን ማስታወስ አይከፋም። ኩራታችንም ውርስ ነው ማለት ነው። ይህ ቅዠት የሚመስል ኩራት ደግሞ ብዙ ነገር አስረስቶናል። ከዚያም አልፎ ከውርስም ይሁን ከተፈጥሮ ፀጋዎቻችን ያገኘነውን ጥቅም መፈተሽም ተገቢ ነው። እርግጥ ነው ጥቂት የዋሆች ፊት ይህንን መናገር እራስን ማንኳሰስና ገመናን አደባባይ ማውጣት ከመሆን አልፎ ከወንጀልም ሊቆጠር ይችላል። የበለጠ ወንጀል የሚሆነው ግን ከሌላው አልፎ የራስን ሕሊና ሲዋሹ መኖር ይመስለኛል።

በአንድ ታሪካዊ ሲምፖዚየም ላይ አንድ ‘ምሁር’ - “እኛ የተለየን ህዝቦች ነን …” ብለው ሲናገሩ ከጐኔ የተቀመጠው ሰው የተናገረው ሁሌም ትዝ ይለኛል። “ቀንድ የለን ጭራ በምንድን ነው የተለየነው?” ነበር ያለው። እራስ ወዳድነት ካልሆነ በቀር ያለይሉኝታ የተለየን የሚያደርገን ነገር ቢኖር ‘እንዳስቀመጡን የተቀመጥን የአደራ ህዝቦች’ (የሚባል ነገር ካለ) መሆናችን ነው። ይህ በዚህ ይብቃን። ነገሬን ወደተነሳሁበት ነጥብ ልመልስና አጨራረሴን ላሳምር።

ዛሬ እንኳን በሞቴ! ዛሬ በ፳፩ኛው (21ኛው) መቶ ክፍለዘመን እንኳን! በግልም ይሁን በወል ስንነቅፍም ሆነ ስናወድስ፣ ስንደግፍም ሆነ ስንቃወም ማዕከላችንን አገር ለማድረግ አልቻልንም። የግል ወይም የቡድን ፍላጐታችን በረካ ቁጥር አገሪቱ የተለወጠች ይመስለናል። መመዘኛችን የግል ሆዳችን በሆነ ቁጥር ደግሞ ገመናችን ተገልጦ ሲነገረን ቡራከረዩ እንላለን። ለብልጽግና የሚያበቃ አስተሳሰባችን ማቆጥቆጥ ቀርቶ ገና አልበቀለም። ዛሬም የአባቶቻችን ልጆች ነን። ይህ በሆነበት አገርና ህዝብ መሃል ደግሞ ፍቅር የተላበሰ መረባረብና በአስተሳሰብ ራስን ለመለወጥ ከመፍጨርጨር በፊት “እኔ የተሻልኩ ነኝ” ብሎ መወራጨትም እውነት አይደለም። የነበረውም፣ ያለውም፣ የሚመጣውም ኢትዮጵያዊ ነው። የአመለካከት ለውጥ ካልተፈጠረ ሁሉም እውነት አይደሉም። ሕልም ናቸው። እውነተኛው የብልጽግና ጮራ የሚፈነጥቀው እኛ ኢትዮጵያውያን እንደዛሬው ዓለም ሰው ማሰብ የጀመርን ዕለት ነው። ሳይታሰብ የሚከወን ነገር የለምና።

ነገሬን ላሳርግ። … በኢትዮጵያዊነት ብቻ ሳይሆን በአፍሪካዊነት ሳይቀር ወሰን የሌለው ኩራት የሚሰማን ካለን ለደቂቃ ቆመን እናስብ። “እውነተኛው የኩራት ምንጭ ምንድነው?” ብለን እንጠይቅ። ይህ ድፍረትም ንቀትም መስሎ ከታየን ደግሞ መኩራት ይቻላል። እኔ ስላወራሁ ኩራታችንን የሚከለክለን የለም። እኔ ቃዥቼም ይሆናል፤ ግን የመሰለንን ሃሳብ መሰንዘር ተፈቅዷልና ምን ታረጉታላችሁ?

በመጨረሻ አንድ ነገር ልናገር። ከመግቢያዬ እንደጠቆምኩት “ጥያቄአችን ኢትዮጵያዊነት ላይ ያነጣጥር” ማለቴን አስታውሳለሁ። ብዙ ያልተብራሩ ነገሮች እንዳሉ ይሰማኛል። ስሜቴን ከተረዳችሁልኝ ወደ ቃላት ጨዋታ ባትገቡ ደስ ይለኛል። ይህንን ስል በአስተሳሰብም ሆነ በተግባር ሁላችንም ተጠያቂ ነን ማለት ፈልጌ ነው። አዎ! ተጠያቂ ነን። ወደዚህ ዘመን ስንመጣ ደግሞ መሪዎቻችን ላይ የምናነጣጥርባቸው ነገሮች አሉ። እኔ የማወራው ስለፖለቲካ ጉዳይ አይደለም። መሪም በሏቸው ገዢዎች ኢትዮጵያዊ ናቸው። እነሱ ወደዚህ ዘመን አስተሳሰብ ተሻግረው ካላየን (በራሳቸው) ግለሰቦቹን ከመንቀፍ ይልቅ ለእኔ እምነት የሚቀርበው ኢትዮጵያዊነት ምን ነክቶታል? ብዬ ብጠይቅ ነው። የማንም ቲፎዞ ወይም ተቃዋሚ ሆኜ መናገሬ አይደለም። በራሱ ትርጉም እንደዚህ የሚያስብ ካለ መኖሩን ባላወግዝም - ያ ሰው ተሳስቷል።

እደግመዋለሁ! አዎ! አሁንም ቢሆን መሪዎቻችን በአንደበታቸው ሳይሆን በውስጣቸው ከነበረውና ፀንቶ ከኖረው አመለካከት እራሳቸውን ፈትሸው መቆም አለባቸው። ወደ ዘመን ለመጠጋትና አገራቸውንና ወገናቸውን ከውርደትና ከልመና ለማዳን ይወስኑ። ከላይ እስከታች ኢትዮጵያዊነት ከሰው በታች የመሆን ጉዳይ ሆኖአልና በባዶ ኩራት አይመሰጡ። ራሳቸውንም ሆነ ወገናቸውን ክብር ለማጐናፀፍ እልህና ቁጭት፣ ራዕይና ተስፋ የሌላቸው ከሆነ በግል እምነቴ አሁንም ከግለሰቦቹም ሆነ ከቡድኖቹ ጋር ጉዳይ የለኝም። በዚህ እምነቴም ደጋፊም ተቃዋሚም አለ ብዬ አልናገርም። ምናልባት ለብቻዬ ሳወራ ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት ነው? ብዬ እራሴን ስጠይቅ እኖር ይሆናል። እስከ መቃብር።

አበቃሁ!!

 

ወደ አስተያየት/ትችት ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

 

 

Hosted by www.Geocities.ws

1