ወደ ኪነጥበብ ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

 

የቴሬሣ ደብዳቤዎች

ድርሰት፦ ማክሲም ጐርኪ፣

ትርጉም፦ ካሌብ ዮፍኒ

አንድ ቀን ጓደኛዬ እንዲህ ሲል አጫወተኝ፦

ሞስኮ እየተማርኩ ሳለሁ እኖርባት ከነበረች ክፍል አጠገብ አንዲት ቴሬሣ የምትባል ለየት ያለች ፖላንዳዊት ጎረቤት ነበረችኝ።

እረዥምና ጠንካራ ናት። ቡናማ ዓይን፣ ችፍርግ ያለ የዓይን ሽፋል እና በመጥረቢያ የተቆረጠ የሚመስል ቅንድብ አላት። ዓይኖቿ ይከብዳሉ። ሰርሳሪ ድምጿ ያስፈራል። ነገረ ሥራዋ ሁሉ በሕይወት ለመቆየት የሚታገሉትን ያስመስላታል። ግዙፍ ሰውነቷ እንዲያው በአጠቃላይ ሁለንተናዋ በሚያስፈራ ሁኔታ አስጠሊታ ነው።

በምኖርበት ሕንፃ ላይኛው ደርብ ላይ ትይዩ ክፍሎች ነበሩን። እሷ ቤቷ መኖሯን ካወቅሁኝ በፍፁም በሬን አልከፍትም። አንደንዴ ግን በመተላለፊያው ወይም በደረጃው ላይ አገኛታለሁ።

ሳገኛት በኮመጠጠ ፈገግታ እያየችኝ ትስቅብኛለች። ሁል ጊዜ ወደ ቤቷ ስትመጣ ዓይኗ ቀልቶ ፀጉሯ ተንጨባሮ ነው የማገኛት። ታዲያ ያኔ “ሃሎ ተማሪው!” ትለኛለች።

ያ አስጠሊታ ሳቋ ደግሞ ሳይጠሩት እየመጣ ይረብሸኛል።

እሷን ላለማግኘት ስል ክፍሌን መቀየር ሊኖርብኝ ሆነ። ግን አልሆነም - ክፍሌን እወዳታለሁ - ከተማዋን በግልፅ ለማየት አመቺና በጣም ደስ የምትል ናት። በዛ ላይ እኔ በነበርኩበት ክፍል በኩል ያለው አውራጐዳና ፀጥታ የሰፈነበት ነበር።

አንድ ጠዋት ለባብሼ አልጋዬ ላይ አረፍ እንዳልኩ ወዲያውኑ በሩ ተከፈተና ቴሬሣ በሩ ላይ ተከሰተች።

በሰርሳሪው ድምጿ “ሃሎ ተማሪው! አለችኝ …

“ምን ፈልገሽ ነው?” ብዬ ጠየቅዃት …

አተኩሬ ሳያት ከዚህ በፊት በማላውቀው ሁኔታ ፊቷ ግራ መጋባትን የሚያንፀባርቅና ብሩህነትን የተላበሰ ነበር።

“ተማሪው አንድ ውለታ እንድትውልልኝ ልጠይቅህ ፈልጌ ነበር። እባክህ! እንቢ አትበለኝ” አለችኝ … ምንም አላልኳትም።

“ለቤት ደብዳቤ መፃፍ እፈልጋለሁ …” ስትል ቀጠለች።

በትክክል የምትፈልገው ነገር ምን ይሆን ስል አሰብኩና ከአልጋዬ ዘልዬ ተነስቼ ወረቀትና ብዕር አዘጋጀሁና ወንበር ስቤ “ግቢ ቁጭ በይና ንገሪኝ” አልኳት።

ገብታ ከፊት ለፊቴ በጥንቃቄ ተቀምጣ በጉጉት ዓይኖቼን ተመለከተች።

“ጥሩ! ለማን ነው የምጽፍልሸ?” ስል ጠየቅዃት።

“ስዌንዚአኒ በዋርሶ የባቡር መንገድ ለሚኖረው ለቦሌስሎቭ ካሶችፑት”

“ምንድን ነው እንድጽፍልሽ የፈለግሽው? ቀጥይ …”

“የኔ ውድ ቦሌስ - የኔ ተወዳጅ - የኔ ፍቅር - ነፍሴ - እግዚአብሔር ይጠብቅህ! ውዴ ሁሌም ለምትበሳጨው ትንሽ እርግብህ ለቴሬሣ ለረዥም ጊዜ ደብዳቤ ሳትጽፍላት የቀረኸው ለምንድን ነው? …”

ሳቄን በግድ ገታሁት - ይህቺ ትንሽ እርግብ ወደ አንድ ሜትር ከሰማኒያ ቁመት ያላት ጤነኛና ጠንካራ መዳፍ ያላት እና በሕይወት ዘመኗ ጉድፉን ከማጥራት ሌላ ምንም የማትሠራዋ እርግብ ፊት እንዲያ ከሆነ የገረጣች ነች።

አንገቴን ቀና አድርጌ “ቦሌስሎቭ ማነው?” ስል ጠየቅዃት። በመገረም “ክቡር ቦሌስ?” ስትል ደገመችልኝ ልክ ማንም ሰው የቦሌስን ማንነት እንደሚያውቅ ሁሉ … ቀጠል አድርጋ “ቦሌስን ላገባው ነው!”

“ልታገቢው?”

“ምነው በጣም ተገረምክ ተማሪው? እንደኔ አይነት ኮረዳ ፍቅረኛ ሊኖራት አይችልም?”

“ኮረዳ? ምን አይነት ቀልድ ነው?! ምን አልባት …”

እንዲህ አልኳት “ኧረ! ይቻላል! ለመሆኑ ከተጫጫችሁ ለምን ያህል ጊዜ ቆያችሁ?”

“ለ … አስር ዓመት!”

“መልካም!” ደብዳቤውን ጻፍኩላት።

ፀሐፊዋ ቴሬሣ ባትሆን እኔ በቦሌስ ቦታ ብሆን የምወደው ዓይነት፣ በፍቅርና በስሜት የተሞላ ደብዳቤ ነበር።

“ተማሪው! ከልቤ ነው የማመሰግንህ!” አለችኝ ልቧ የተነሳ ይመስላል።

“ምን ላድርግልህ?”

“ምንም! አመሰግናለሁ!”

“ተማሪው! ሸሚዞችህንና ልብሶችህን ላጥብልህ እችላለሁ” አለችኝ።

ይሄ ትንሽ አስቆጣኝ። ከሷ ምንም አገልግሎት እንደማልፈልግ ግንባሬን ቋጥሬ አረጋገጥኩላት።

ከክፍሌ ለቃ ወጣች።

ሁለት ሣምንቶች ካለፉ በኋላ አንድ ማታ መስኮቱ ጋ ተቀምጬ እያፏጨሁ ጊዜዬን እንዴት በደስታ ማሳለፍ እንደምችል አስባለሁ። የውጭው አየር መጥፎ ስለነበር መውጣት አልፈለኩም። ያኔ በሩ ተከፈተ።

ቴሬሣ ነበረች … “ተማሪው አሁን ሥራ ይበዛብሃል እንዴ?” አለችኝ።

ሌላ ሰው ባይ እመርጥ ነበር።

“አይ! ምነው?”

“ደሞ ሌላ ደብዳቤ እንድትጽፍልኝ ፈልጌ ነበር”

“እሺ! ለቦሌስ ነው?”

“አይ! የሱን መልስ ነው የምፈልገው”

“ምን?” ጮህኩ።

“… ይቅርታ! ተማሪው የማልረባ ደደብ ነኝ። እራሴን በትክክል አልገለጽኩልህም ነበር። እ … ለኔ አይደለም ለአንድ ጓደኛዬ ነው። ከምቀርባቸው አንዱ ነው። እንዴት እንደሚጻፍ አያውቅም። እንደኔ አይነት ፍቅረኛ አለችው።”

ትክ ብዬ አየኋት። ያፈረች ትመስላለች። እጆቿ ይንቀጠቀጡ ነበር። ግራ ገብቷታል። እንደነቃሁባት ገመትኩ።

“ስሚኝ ልጅት ስለራስሸ፣ ስለቦሌስሎቭ እና ሌላው የነገርሽኝ ሁሉ ባዶ ፈጠራ ነው። ዋሽተሽኛል። ያ ሁሉ እዚህ ለመምጣት ምክንያት እንዲሆንሽ ነው። ከአሁን ወዲያ ካንቺ ጋር የሚያገናኘን ምንም ጉዳይ የለን! ገባሽ? …”

እንደፈራች አየሁ። ፊቷ ቀልቷል። አንድ ነገር ለመናገር በብርቱ ፈልጋለች።

በስህተት ነው የፈረድኩባት። ከዚህ ነገር ጀርባ አንድ ነገር አለ። ግን ምን?

“ተማሪው! …” ስትል ጀመረች። ግን በዚያው ቅፅበት ፊቷን አዙራ ከክፍሌ ወጣች። እኔ ግን ልቤ ሲከብደኝ ተሰማኝ። የበሯ ደፍ ሲዘጋ ሰማሁ። ተናዳ ነበር።

መልሼ ልጠራት ወሰንኩ - አዝኜላታለሁ። ስለሆነም ደብዳቤውን … እጽፍላታለሁ።

ወደ ክፍሏ ሄድኩ። ጠረጴዛዋ ጋ እራሷን በመዳፎቿ ቀብራ ተቀምጣለች።

“እቱ! … አንቺ! …” አልኳት።

በሕይወት ታሪኬ ውስጥ ወደዚህ ነጥብ ስመጣ ሁል ጊዜ በጉዳዩ ልቤ በጣም ይነካል።

ዘልላ ተነሳች። ዓይኖቿ እያንፀባረቁ ቀጥታ ወደኔ መጣች። ክንዶቿን ትከሻዬ ላይ አስቀመጠቻቸውና ልቧ እንደተሰበረ በጥልቅ ተነፈሰች።

“እነዚህን ትንሽ መስመሮች መጻፍ በአንተ ላይ ምን ለውጥ ያመጣል? ኦ! … አንተን እንደጥሩ ሰው አይህ ነበር። አዎ! ልክ ነህ ቦሌስሎቭ የለም። ቴሬሣም የለችም። ያለሁት እኔ ብቻ ነኝ። እኔም ብቻዬን!”

“ምን?” አልኳት በአባባሏ ተገርሜ። “እና ቦሌስ ጭራሽ የለም ነው የምትይኝ?”

“የለም!”

“እና ቴሬሣም የለችም?”

“አዎ! የለችም። ቴሬሣ እኔ ነኝ”

በመገረም ተመለከትኳት። ከሁለት አንዳችን በእርግጥ ቀውሰን ነበር።

ወደ ጠረጴዛዋ ሄዳ አንድ ወረቀት ይዛ መጣችና … “ይኸውልህ ይሄን ደብዳቤ መልሰህ ውሰደው። ሁለተኛውን ደብዳቤ ልትጽፍልኝ አትፈልግም አይደል? … ሌሎች ደግ ልብ ያላቸው ይጽፉልኛል።”

ለቦሌስሎቭ የጻፍኩላትን ደብዳቤ በእጇ ይዛዋለች።

“ስሚኝ ቴሬሣ! ይሄ ሁሉ ነገር ምንድነው? ይሄን ደብዳቤ ካልላክሽውስ ለምን ሌሎች ሰዎች ሌላ ደብዳቤ እንዲጽፉልሽ ፈለግሽ?”

“ለማን ልላከው?”

ማድረግ የምችለው ወጥቶ መሄድ ብቻ ነበር። ነገር ግን ንግግሯን ቀጠለች።

“አዎ! እሱ ሊያገኘው አይችልም። ቦሌስሎቭ የለም። ነገር ግን እሱ እንዲኖር እፈልጋለሁ። እንደ ሌሎቹ እንዳልሆንኩ አውቃለሁ … ማን መሆኔንም አውቃለሁ፤ ነገር ግን ለሱ መጻፌ ማንንም አይጎዳም።”

“ምን ማለትሽ ነው? ለማነው የምትጽፊው?”

“ለቦሌስሎቭ”

“ግን እኮ ቦሌስሎቭ የሚባል ሰው የለም ብለሻል።”

“ኦ! ታዲያ ባይኖር እኔ ምን ግድ አለኝ! … ማንም የለም። ነገር ግን እኔ ቦሌስሎቭ እንዳለ አስባለሁ። በቃ! እሱ ልክ በእውን እንዳለ እጽፍለታለሁ እና እሱም ይመልስልኛል። ደግሜ እጽፍለታለሁ፤ እሱ ደግሞ እንደገና ይጽፍልኛል …”

በመጨረሻም ገባኝ። … ጥፋተኛነት ተሰማኝ። ተረበሽኩ … ሰውነቴ ተሸማቀቀ። ባጠገቤ አንዲት የነፍሷን ጉዳት ልታዋየው የምትችለው ሰው በዓለም ላይ የሌላት ምስኪን የሰው ልጅ አለች። ቤተሰብ የላት፣ ጓደኛ የላት፣ … እና ይህቺ ምስኪን ለራሷ አንድ ሰው ፈጠረች …

በሰርሳሪ ድምጿ ቀጠለች፦

“ይህን ለቦሌስሎቭ የጻፍክልኝ ደብዳቤ አንድ ሰው ጮክ ብሎ እንዲያነብልኝ ጠየቅኹት። አዳመጥኩትና ቦሌስሎቭ እንዳለ አሰብኩ። እና ከዛ ደግሞ መልሱን ቦሌስሎቭ ለቴሬሣ እንዲጽፍላት ጠየቅኹህ - ማለትም ለኔ። ቦሌስሎቭ �በእርግጥ አንድ ቦታ እንዳለ አመንኩ - የት እንደሆነ አላውቅም። እንዲኖር ግን ማድረግ እችላለሁ። ይሄ በጣም ከባድ፣ በጣም አስፈሪና ባዶ አይደለም።”

ከዛን ቀን ጀምሮ በመደበኝነት በሣምንት ሁለት ጊዜ ከቴሬሣ ለቦሌስና ከቦሌስ ለቴሬሣ ደብዳቤ እጽፋለሁ። በእውነት ደብዳቤዎቹ በጥልቅ ስሜት የተሞሉ ናቸው - በተለይ መልሶቹ።

እሷ ራሷ ሲነበብላት ሲቃ ያንቃታል። ትስቃለች ደስ ይላታል።

በምላሹም ልብሶቼን፣ ሸሚዞቼን፣ ካልሲዎቼን ታጥብልኛለች። ጫማዬን ትጠርግልኛለች። ኮፍያዬን ትቦርሽልኛለች።

ከሦስት ወር በኋላ በአንድ ወንጀል ተጠርጥራ ወሕኒ ገባች። ከዛን ጊዜ ጀምሮ አይቻት አላውቅም። … ሞታ መሆን አለበት።

 

ወደ ኪነጥበብ ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

 

 

Hosted by www.Geocities.ws

1