ወደ ኪነጥበብ ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

ቀጠሮ በሥነ-ቃል ሲገለጽ

ለቀጠሮ ደንታ ቢስ መሆን የኢትዮጵያዊነት መለያ!?

በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር

************************************

ስለቀጠሮ አንድ ሺ አንድ ጊዜ ብዙ ቢባልም፣ እኔም ለአንድ ሺ ሁለተኛ ጊዜ ትንሽ ልበል። ስለምን? አሁን ያለነው በአዲሱ ዓመት አናት ላይ ነውና “ካምናው ዘንድሮ ባሰበት” አይነት ትችት እንዳይገጥመን፣ “ከርሞ ጥጃ” በሚል እንዳንወቀስና “የሰው ቀጠሮ ቀርጥፎ የሚበላ” ተብለን በሰው አፍ እንዳንገባ ትምህርት ይሆነን ዘንድ ማንሳቱ አስፈላጊ ስለሆነ ነው።

በአዲሱ ዓመት አናት ላይ ቂብ ተብሎ ወይም አሮጌ ዓመት ዳርቻ ላይ ተሆኖ ወደፊት ይተገበራሉ የምንላቸውን ቁምነሮች እቅድ መልክ መንደፍ የተለመደ ነገር ነው። እቅድ በራሱ ወደፊት ሊፈፀም ይችል ዘንድ በቀጠሮዎች የተያዘ ነገር (ቀጠሮ) ነውና። ስለዚህ ስለቀጠሮ ትንሽ ቢባል የሚያስከፋ አይሆንም።

አስር ደቂቃ ምንም አይደለም። ሃያ ደቂቃም እንዲሁ። ኧረ! ሰላሳ ደቂቃም ቢሆን ለሚወዱት ሰው ተገትረው ቢውሉ ከቁም ነገር የሚጣፍ አይሆንም። ኤዲያ ሰላሳ ደቂቃስ ምን አላት? አንድና ሁለት ሰዓትስ ቢሆን ቀጠሮ ቦታ መገተር ከባሰብን መጐለት ለእኛ አዲሳችን ነው እንዴ?! ድንቄም እቴ! “ይሉትን በሰማሽ፣ ገበያም ባሎጣሽ” አለች ስንዴነሽ። እኛ እኮ ምርጥ አበሻ፣ ጥሩ ኢትዮጵያዊያን እኮ ነን። ማንም ሳይሾመን እራሳችንን ጊዜን አንቀው ከሚገድሉ ጐራ የመደብን አይደለንም እንዴ!? ቀጠሮ ያላከበረ፣ በቀጠሮ ሰዓት ያልተገኘ ሰው ሲገጥመን ምንድን ነው የምንለው? “ድሮስ አበሻ” አይደል? ግን … ግን … ግን “ጊዜ ወርቅ ነው” ተብሎ እንደጥቅስ በሚነበነብበት፣ “… ጊዜ ታክሲ አይደለም፣ አይጠብቅም ቆሞ” … እና መሰል ግጥሞች ስለጊዜ ክቡርነት በሚነገሩበት አገር፣ የሰው በቀጠሮ አለመገኘትና ሰዓት አለማክበር ማርፈድ የኢትዮጵያዊነት ምልክት ተደርጐ መወሰዱ ለምን ይሆን?

ይህ ደግሞ የኛ መገለጫ የኢትዮጵያዊነት መለያ ስላለመሆኑ ዋቢነት ፍለጋ እሩቅ መማሰኑ፣ ጉልበት ማባከኑ አስፈላጊ አይሆንም። ከዚሁ ከቅርቡ ጽሕፈት ትናንትና ከመምጣቱ በፊት በቃል ሲነገሩና እየተነገሩ ያሉትን ሥነ-ቃሎች መመልከቱ ይበቃል። ጊዜና ቦታ የሚገድበን ስለሆነና ነገሩን ሳናሰፋ፣ ጥላሁን ገሠሠ በአንድ የሙዚቃ ካሴቱ ላይ ቀጠሮን ያለማክበር ምች ያጠናገራቸውን ሰዎች፣

“… አርቆ ማሰቢያ እያለው አዕምሮ፣

ሰው እንዴት ይሳነው ለማክበር ቀጠሮ …”

በማለት የነቀፈበትን ባለሁለት ስንኝ ግጥም መንደርደሪያ አድርገን በዚሁ ጉዳይ ላይ ስለተነገሩ በጣም ጥቂት ሥነ-ቃሎች ትንሽ እንበል።

“ጊዜ አለው ለሰው፣ ዕድሜ ካላነሰው” የሚለውን ብሂል መሰረት ያደረጉ አባቶቻችን “ከቶ አይቀርም ሞቱ፣ ምንም ቢዋትቱ” ከሚለው የሞትን አይቀሬነት ከሚያስረዳ መንታ ግጥማቸው ባሻገር፣

“አያሳስትም ሰዓት፣

ቀጠሮ ያከብራል ሞት።”

በማለት ጊዜውን ጠብቆ የሚመጣ፣ ቀጠሮ አክባሪው ሞት ነው ሲሉ የሞትን አይቀሬነት ገልፀዋል። እዚህ ላይ ስለቀጠሮ ምንነት ልብ ይሏል።

ስለሞት በዚህ እናቁምና ከቀጠሮ አከባበር ጋር ተዛምዶ ያላቸውን አንድ አራት መንታ የፍቅር ሥነ-ቃል ግጥሞችን እንመልከት።

“በኋላ ከሰዓት፣ ነገ፣ ከነገ በስቲያ ነይና ፍቅራችንን እንገላለጽ፣ እናጣጥም” እያለ ቢመክራት፣ ቢዘክራት የከንፈር ወዳጁ፣ “እንቢኝ አሻፈረኝ” ያለችው ወጣት አፍቃሪ ቀጠሮው አለመከበሩ ቢቆጨውና ቢያሳዝነው፣

“ነይ ስልሽ ጊዜ አትመጪም ወይ፣

ሎሚ ለሽታ አይደለም ወይ?”

በማለት ለምን እንደፈለጋትና ፍቅረኛሞች ተቃጥረው ምን እንደሚያደርጉ ለመግለጽ ሞክሯል።

“ቀጣፊን ያመነ፣ ጉምን የዘገነ” እንዲሉ አበው፣ ዘወትር እየቀጠረችው በቀጠሮው ቦታና ሰዓት ከዓይኑ የገባችው ልጃገረድ አለመገኘቷ ያበሸቀውና የነደደው አንድ ወጣት ብስጭት በተሞላበት መንታ ግጥም፣

“አንቺም ሰው ሆንሽና ሰው ቀጥሮ መጥፋት፣

ደባደቦ ምንጭር አክንባሎ ፊት”

ሲል ንቀት በታከለበት ውረፋ ወርፏታል።

የሚገናኙበትን ሰዓትና ቦታ ልቅም አድርጐ ነግሯት፣ እመጣለሁ ብላ በምላስ ደልላ የቀረችበት ወጣት፣

“ከቤትሽ በስቲያ ተኮረብታው ላይ

እመጣለሁ ብለሽ መቅረትሽ ነወይ?”

ወደ እንስቲቱ መለስ እንበልና ደግሞ፣ የሚወደውን ታቦት አስጠርታ፣ “እዛ እምንገናኝበት ቦታ በይህን ያህል ሰዓት አደራ እንዳትቀር” ብላ አጥብቃ ነግራው፣ ወዳጇ ግን ቀጠሮውን ነገሬ ሳይል ዘንግቶ ቢቀርባት፣

“በአቦ በሚኻኤል ምሎ ተገዝቶ፣

ሰው እንዴት ይቀራል ቀጠሮ ዘንግቶ”

በማለት የባልንጀራዋን ልበቢስነት አስረግጣ ተናግራለች።

ሌላው ደግሞ “ውዴ፣ ፍቅሬ፣ …” የሚላትን “የእኔ የዓለም ቆንጆ …” እያለ እየቀጠረ በረባ ባልረባው ምክንያት አልገኝ ብትለውና በቀጠሮው ስፍራ እያመላለሰች መከራውን ብታሳየው፣

“በሽታየ አንቺው ነሽ በሽታም የለብኝ

እመጣለሁ እያልሽ እየቀረሽብኝ”

ሲል በማንጐራጐር የፍቅር ሕመሙ እንደጠናበት ለማሳየት ሞክሯል።

ከላይ በተለያዩ ጥቂት ሥነ-ቃሎች አባቶቻችን ለጊዜ ክቡርነት ምን ያህል እንደሚጨነቁ፣ ለቀጠሮ ክቡርነት ምን ያህል እንደሚጠበቡ ከብዙ በትንሹ ለማሳየት ተሞክሯል። እናም አሁን የያዝነውን አጉል እምነት አሽቀንጥረን ጥለን፣ “የጊዜን ክቡርነት የተረዳው ፈረንጅ ብቻ ነው” የሚለውን ተራ ዲስኩር እንደአሮጌው ዓመት ወደኋላ ትተን “ለጊዜ ዋጋ እንስጥ!”፣ “ለቀጠሮ ዋጋ እንስጥ!” የአዲሱ ዓመት መፈክራችንም ይሁን።

ጠብቄሽ ነበረ

መንፈሴን አንጽቼ

ገላዬን አጥርቼ

አበባ አሳብቤ

አዱኛ ሰብስቤ

ጠብቄሽ ነበረ

ብትቀሪ ጊዜ

መንፈሴን አሳደፍኩ

ገላዬን አጐደፍኩ

አበባው ደረቀ

አዱኛው አለቀ

ብትቀሪ ጊዜ

የጣልኩብሽ ተስፋ

እኔን ይዞ ጠፋ

------------------------------------------------

{‘ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ’ - ደበበ ሰይፉ}

 

ወደ ኪነጥበብ ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

 

 

Hosted by www.Geocities.ws

1