ወደ ማኅበራዊ ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

ከድክመቶቻችን ጀርባ የቆመው ማነው?

ፀዳለ ክፍሌ

 

በትራፊክ አደጋ ብዛት ከዓለም ስንተኛ እንደሆንን እንደ በጐ ነገር ደግሜ አልናገረውም። ይሁን እንጂ በምን ምክንያት እንዲህ "እንዳሻቀብን" መጠየቅ አግባብ ይሆናል። ብዙ ነገሮች ልብ ብለው ሲያስተውሏቸው ለዘመናት በምክንያትነት ሲደረደሩ የኖሩ ጉዳዮች አንዳንዴ ባዶ ናቸው ባይባልም ዋናው ምክንያት እየተረሳ በቅብብሎሽ ሲወተወቱ የኖሩ መሆናቸው ይገባናል። ለትራፊክ አደጋ መፈጠር ዋና ዋና ተብለው ሲጠቀሱ የኖሩና ያሉ ምናልባትም ዓለማቀፍ ይዘት ያላቸው ነጥቦች አሉ። "ከጠጡ አይንዱ - ከነዱም አይጠጡ" ከሚለው ማስጠንቀቂያ ጀምሮ የመኪናውን ሙሉ አካል ጤነኛ መሆኑን ማረጋገጥ ይመከራል። አሽከርካሪዎች ከሃሺሽና ጫትን ከመሳሰሉ አደንዛዥ ዕፆች እንዲርቁም ከምክር አልፎ በሕግ እስከማገድም ተደርሷል።

የየአገሮች ሁኔታ የተለያየ ቢሆንም የመንገዶች ጥበትና የተሽከርካሪ ብዛትም ለአደጋ ምክንያት ይሆናል። የመንገድ ምልክቶችና መብራቶችም በተገቢው መሥራት አግባብ መሆኑ ይታመናል። ተገቢ ባልሆነ ቦታ ከተገቢው በላይ መብረር፣ በኩርባ መንገድ ላይ ፍጥነትን አለመቀነስና ባልተመቸ ቦታ ተሽከርካሪን መቅደም የአደጋ መንስዔ ሊሆን ይችላል ...

ለመሆኑ ከነዚህ ሁሉ ምክንያቶች በእኛ አገር የበለጠ የሚመለከቱን የትኞቹ ናቸው? ሁሉም ወይስ በከፊል? ወይስ ከአውደ-ትራፊክ ጥራዝ ውስጥ ያልተጠቀሰ ሌላ ምክንያት ይኖር ይሆን? ብሎ መጠየቅ ክፋት ያለው አይመስለኝም። ደንቦችና ሕጐች ዘላለማዊ አይደሉም። ከሰማይ የወረዱ ትዕዛዛትም አይደሉም። ይህ ከሆነ ደግሞ ከሁኔታዎች ጋር መዳበርና መለወጥ ይኖርባቸዋል።

ይህን ለማድረግና ለመፈተሽ ሳንፈቅድ ስንቀር ቀሪው ተግባር የሚሆነው በመስኩ የሚፈጠረውን አደጋ መቀነስ ሳይሆን ሥራችን የየዓመቱን ስታትስቲክስ ማውጣት ብቻ ይሆናል። እየሆነ የምናየውም ይህንኑው ነው። በዓመት በወርና በሣምንት ውስጥ አዲስ አበባ ውስጥ የሚጠፋውን የሰው ሕይወት፣ የሚጐድለውን የሰው አካልና የሚወድመውን ንብረት የመተንተን ዓላማ የለኝም። ይህ እንዲሆን የሚፈልግ ካለ የትራፊክ ጽሕፈት ቤት ቅርብ ይመስለኛል። ከዚህ ይልቅ ለመሆኑ ያልተፈተሹና ያልተነገሩ ምክንያቶች ይኖሩ ይሆን? ወደሚለው ጥያቄና መልስ ባመራ ይሻለኛል።

እኔ መኪና የለኝም፣ አሽከርክሬም አላውቅም። በዕለት ከዕለት ኑሮዬ ግን እንደ እሬሳ ሳጥን ተጭኜ ነፍስና ስጋዬን ለሾፌር አደራ ሰጥቼ መንቀሳቀሴ አልቀረም። ይህ ሲሆን ደግሞ ትኩረት ካልተነፈገው በቀር ብዙ ነገር ለመታዘብ ይቻላል።

በአንድ ወቅት አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደ የንግድ ትርዒት ላይ የተገኙ አፍሪካዊ ሴቶችን የማነጋገር አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። ስለ አገራቸውና ስለ አገራችን አንዳንድ ነገሮች ካወጋን በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ከተመለከታችሁት ነገር የበለጠ የገረማችሁ ወይም ያስደሰታችሁ ነገር ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ሰነዘርኩ። አንዷ በቅጽበት የሰጠችኝ ምላሽ ፈጽሞ ያልጠበቅሁት ነበር። ምን አለችኝ መሰላችሁ? "ሴቶቻችሁ መኪና ሲነዱ እንዴት ደስ ይላሉ?" አለችኝ። በአግራሞት አልገባኝም ነበርና "እንዴት?" አልኳት።

"ከወንድ ይበልጣሉ - ተዝናንተው እንደ ጄት ነው የሚበሩት" አለችኝ ደስተኛ ሆና እየሳቀች። በአድናቆቷና በስሜቷ ውስጥ አንዳችም የአሽሙር ቅላፄ አልነበረውም። በሌላ አገላለጽ እንዲህ መክነፍ አልነበረባቸውም ለማለት ሳይሆን በሴትነቷ "እንደነሱ በሆንኩ" በሚል ስሜት ነበር። እኔንም ደስ የሚል ስሜት ወረረኝ። ይህን የሰነበተ ገጠመኝ ካወጋኋችሁ ወደ ዋናው ጉዳዬ ልመለስ።

አንድ ጤነኛ የሆነ ሰው መንጃ ፈቃድ አውጥቶ መኪና መንዳት መብቱ ነው። የዕድሜ ገደብ ቢኖረው እንጂ ሴት ወንድ፣ ወጣት ሽማግሌ፣ የተማረ ያልተማረ የሚሉ ጥያቄዎች ቦታ ያላቸው አይመስለኝም። ከዚህም አልፎ በአገራችን ለሙያው ያለው ግንዛቤ በጣም ተራ ሙያ ከመባል አልፎ ለሙያተኛውም የሚሰጠው ቦታ የሚያተርፍለት ከበሬታ እንደሌለ እናውቃለን። ሾፌርና ሾፌርነት ሌላ ነገር ከጠፋ እጠቀምበታለሁ በሚል ፈቃድ የሚጨበጥበት መስክ ነው። ፈቃዱን በማውጣቱ ሂደትም ቢሆን ሙያው የሚጠይቀው ስልጠና እጅና እግርን የተቀናጀ መፈራረቅ ከመፍጠር የሚዘል አይደለም። በቴክኒክ ት/ቤት ተምረው ስለተሽከርካሪ ውስጣዊ ባህሪና አጠቃላይ እውቀት ቀስመው የሚያሽከረክሩት ከቁጥር የሚገቡ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ አብዛኛው አሽከርካሪ እጅና እግሩን ያሰለጠነ ነው። ልምድ የማይናቅ ነገር ቢሆንም ስልጠና ደግሞ የበለጠ ያጠናክረዋል። ይህ ከሆነና አንዳንዴም እጅና እግሩ በስልት መንቀሳቀስ ሲሳነው በገንዘብ ጉርሻና በተጭበረበረ ፈቃድ የሚነዳው ሁሉ ሾፌር ነው። ያለምንም ልምምድ ከግቢ ውስጥ የቆመች የወላጆቹን መኪና ሰርቆ "በድፍረት" ፒያሳና መርካቶ የሚዞርና የምትዞር ወጣትም ይጠፋል አይባልም።

ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ሾፌር ተብለው በአብዛኛው በሾፌርነት ስለሚተዳደሩትም ሰዎች ሌላ ነጥብ ማንሳት ይቻላል። እንደጠቀስኩት ስልጠናው የእጅና የእግር ጉዳይ ነው ብለናል። ይህ በመሆኑም ሌላ መስፈርት ተነፍጐታል። እጅና እግር ደግሞ ካለ ነገራቸው በጭንቅላት የመታዘዝ ተፈጥሮአዊ ባህሪ አላቸው። በዚህ የሥራ መስክ ደግሞ ጭንቅላት የሚመረመርበትም ሆነ የሚለካበት መስፈርት የለም። ይህን ካልን ደግሞ በቀጥታ የምናመራው ወደ ትምህርት ደረጃ ይሆናል። ሁኔታው በአግባቡ ሲጤን ብቃትና ልምድ አላቸው የሚባሉት እንኳን እያንዳንዷን የትራፊክ ሕግ አክባሪዎች ቢሆኑም ጥንቃቄአቸው በራስ መተማመናቸው ላይ ያበቃና በሌላ ሰው ስህተት አደጋ ሊደርስ እንደሚችል ይዘነጉታል። አንዳንዶቹ ደግሞ መሃል መንገድ ላይ ገብቶ ለሚገጭ ፍጥረት ተጠያቂነታቸው የላላ መስሎ ስለሚሰማቸው በዚያ ቦታ ላይ መግደል መብታቸው ይመስላቸዋል። ሌሎች ደግሞ ሕጉን በሕግነቱ ማክበር ሲገባቸው ከትራፊክ ጋር ድብብቆሽ ይጫወታሉ። ብሎም ሕጉን ለመጣስ ተግተው የሚሠሩ ናቸው።

ልብ ብላችሁ ከሆነ ለዚህ የሥራ መስክ የመንግሥትም ሆኑ የግል ድርጅቶች የሚያወጡትን ማስታወቂያዎች ታገኛላችሁ። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ማስታወቂያዎች፦ "አምስተኛ መንጃ ፈቃድና የ6ኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቀ፣ አራተኛ መንጃ ፈቃድና የአራተኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቀ፣ ..." የሚሉ ሆነው እናገኛቸዋለን። ይህ ማለት ለዚህ የሥራ መስክ ትምህርት አያስፈልግም የሚልን እምነት ያዳብራል። በዚህ የትምህርት ደረጃም የሚቀጠሩ ለወግ የበቁ ናቸው። "ማንበብና መፃፍ የሚችል" ተብሎ ማስታወቂያ እንደሚነገርም ልብ በሉ። ከዚያም በታች ቢሆን ዋናው መንጃ ፈቃድ መሆኑ አያከራክርም። ስለዚህም መኪና ለማሽከርከር በጭንቅላት "የማይታዘዝ" እጅና እግር በቂ ሆኖአል።

በቂ ነው እንዳንል ደግሞ እጅና እግር በጭንቅላት ይታዘዛል ብለናል። ከዚህ አልፎም ሌላ ጣጣ ይታየኛል። ትምህርት የምንም እውቀት መሠረት መሆኑን እንተማመን። ደረጃው ይለያይ እንጂ በማንኛውም እንቅስቃሴ ውስጥ ትምህርት ከፍተኛውን ኃላፊነት ይወስዳል የሚል እምነት አለኝ። ለመኪና ማሽከርከርም አግባብ የሚኖረው ሁኔታ አለ። በመኪና ማሽከርከር ሂደት ውስጥ ዓይን በሚያየው መንገድ ላይ ብቻ ማፍጠጥ በቂ ነው ብዬ አላምንም። አብዛኛውን ነገርም ከደረሱና ከሚደርሱ አደጋዎች እንዲማሩ መፍቀድና በሌላው ጥፋት መማር ብቻ አግባብ አይደለም። የትራፊክ ሕግጋትን ብቻ መሸምደድም በቂ አይደለም። ከነዚህ ሁሉ በተጨማሪ የሚገምት፣ የሚያመዛዝንና ሊደርስ የሚችልን ያልታየና ያልነበረ አደጋ አይነት ሊሆን ይችላል ብሎ ሊገምት ሊያመዛዝንና ኃላፊነት የሚሰማው ጭንቅላት እንዲኖር የግድ ይላል።

በመርካቶ መሃል እንደ ጄት የሚበሩ፣ ኩርባ መንገድ ላይ በመጡበት ፍጥነት የሚምዘገዘጉ ሾፌሮች ከየት የመጡ ይመስሏችኋል? የተለያየ ግላዊ ስሜት ቢኖርም ስሜትን የሚቆጣጠር የበሰለ ጭንቅላት አለመኖሩን ማን ይክዳል?

ስም እንዳወጣንለት ሁሉ መንጃ ፈቃድ (በተለይ ለሚተዳደሩበት) "የመኃይም ዲግሪ" እየተባለ መቀጠል ያለበት አይመስለኝም። መኃይም ህዝቦች ነን። እንኳን ለሾፌርነት ሌላውም መስክ የተማረ ህዝብ እጥረት እንዳለብን ይገባኛል።

እንዲያም ሆኖ ግን ቢያንስ የምናወጣቸው ማስታወቂያዎች የባለሙያውን ጥረት የሚጠይቁ ሊሆኑ ይገባል። ከሙያው ባሻገርም በትምህርት ደረጃው መሠረት የተሻለ ክፍያ እንዲኖር ማድረግም ጥሩ ማወዳደሪያ ስለሚሆን ትጋትን ይፈጥራል።

ርዕሰ ጉዳዬ ባይሆንም ይህ እጅና እግርን ከጭንቅላት ገንጥሎ መመዘን በብዙ ቦታ ላይ ሲያዘቅጠን ይስተዋላል። በነገራችን ላይ ከዚሁ ከትምህርት ጉዳይ ዙሪያ ሳልወጣ አንድ ነጥብ ላንሳ። ዛሬ ዛሬ እየዳበረ የመጣ አንድ ልማድ መታዘብ ይቻላል። ከሚያጋጥሙን ሥራ-አጦች ውስጥ አብዛኛዎቹን ብታነጋግሯቸው "ትምህርቴን ጨርሼ ሥራ አጣሁ" ሲሉ ትሰማላችሁ። ወላጆቻቸወም ቢሆኑ እሮሮአቸውን ሲጀምሩ "ልጄ ትምህርቱን ጨርሶ ሥራ አጣ" ይሏችኋል። ልብ በሉ በራሳችን ላይ የጣልነው የራዕይ ድህነት ይታያችሁ። በቃ ትምህርትና እውቀት እንዲያም ሲል የጥበብ ዳርቻችን 12ኛ ክፍል መሆኑን ተስማምተን አጽድቀናል። ግንዛቤ የተነፈጋቸው ችግሮቻችን ደግሞ ከዚህ እምነት ይፈልቃሉ።

ለአብነት ስለ እግር ኳሳችን የዘለዓለም ዝቅጠት በተቸንና በነቀፍን ቁጥር ልጆቻችን በቀለም ትምህርት ታግዘው ጭንቅላታቸው የሰላ እንዲሆን መክረን አናውቅም። ሁሌም የተደበቀውን ትልቅ እንቅፋት ወደጐን እንተውና ወይም እንዘነጋውና ሁሌም አፍጥጦ በሚመለከተው መለስተኛ ችግር ላይ ብዙ ጊዜ እናጠፋለን።

ነገሬን ምን ያህል ግልጽ አድርጌው እንደሆነ ባላውቅም ማለት የፈለግሁትን አስረግጬ አስተያየቴን ልቋጭ። በትራፊክ አደጋ፣ በእግር ኳስ ስፖርት፣ ሌላው ቀርቶ ክፉ በሚባሉና እኛ ግን በዓለም ከአንድ እስከ ሦስት ደረጃ እየያዝን የምንዋረድባቸው ነገሮች ሁሉ የጀርባ ታሪካቸውን ልብ ብለን እንመርምር። የመሰለኝን ፍንጭ ለመጠቆም እንጂ ብዙዎቹን ምክንያቶች ገልጫቸዋለሁ ብዬ አላምንም። እንዲያም ሆኖ ከነዚህ ሁሉ ሰንኮፎች ጀርባ እንደ ጅብራ የተገተረው ጠላታችን መኃይምነት ነው የሚል እምነቴን ለማንፀባረቅ እፈልጋለሁ። ድህነትም ሆነ በሽታ - ውድመትም ሆነ ሽንፈት አሳዳጊና አለኝታቸው መኃይምነት ነውና ታግለን እስክናሸንፈው ቢያንስ ጠላታችንን ለይቶ ማወቁም ከምንም ይሻላል። ከድክመቶቻችን ጀርባ የቆመውን 'እርኩስ መንፈስ' እንመልከት።

 

ወደ ማኅበራዊ ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

Hosted by www.Geocities.ws

1