ወደ አስተያየት/ትችት ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

ለገበሬው ከልብ ከተለቀሰለት ... መድኃኒቱ ቀላል ነው

ዮሐንስ አማኑኤል

 

አለመታደል ሲነሳ ሁሌም በአዕምሮዬ የሚመላለሰው የአገራችን ገጠሬና ገበሬ ነው። ምናልባት በአንድ ወቅት የግብርና ተማሪ ስለነበርኩና በመስኩ ዲፕሎማ ስላለኝ ሊሆንም ይችላል። ግን ለዚህ ብቻ አይመስለኝም። በእርግጠኝነት መናገር የምችለው ደርግ እና ኢህአዴግ ወደ ስልጣን የወጡት፣ ሌሎችም ወደ ስልጣን ተቃርበው የነበሩት "ትግላችን 85 በመቶ ለሚሆነው የአገሪቱ ገበሬ (ለዜጋችን) ነው" የሚል መፈክር አንስተው ስለነበር ነው። እንደሚገባኝ ከሆኑ ሁሉም ፓርቲዎች በገበሬው ስም የነገዱና ያስነገዱ ፍልፈሎች መሆናቸው ነው።

አሁን አሁን ወኔው እየጠፋ ወይም እየከበደ መጣ እንጂ አንድ ሁለት ጠብመንጃ ማንገብ የሚቻል ከሆነ "ትግሌ ገበሬውን የመሬት ባለቤት ለማድረግ ነው!" ብሎ ጫካ መግባት ከ17 ዓመት ትግል በኋላም ቢሆን ምኒልክ ቤተመንግሥት አስገብቶ አልጋቸው ላይ ያስተኛል። በቃ! የስልጣን ጥም ካለብዎ እና ደፋር ከሆኑ የጥፍር መቁረጫ ላይ ያለችው ሰንጢም ብትሆን በእጅዎ ካለች ይሸፍቱና "ገበሬውን የመሬት ባለቤት አደርጋለሁ" ብለው ይነሱ! ዛሬም ገበሬው የያዘው መሬት የእሱ አይደለማ! - የመንግሥት ነው። ለመሆኑ ጫካ ለመግባት ድፍረቱ አለዎ?

ወኔዎ ተቀሰቀሰ እንዴ? ... ገበሬው እንደድሮው መሞኘት ስለተወ ባይለፉ እመክርዎታለሁ። ሁሉንም ምላሳሞች አይቶ አይቶ፣ አድምጦ አድምጦ ጠግቧቸዋል። ብሎም አንቅሮ ተፍቷቸዋል - አልረቡትማ! "በቃኝ!" ብሏል። ከጊዜ የማይማር ድንጋይ ብቻ መሆኑን ያስተውሉ። ገበሬውም ጊዜ አስተምሮት ባኗል። ነቅቷል። ከእንግዲህ አይታለልምና ወደ ጫካ የመግባት ሃሳብዎን አሽቀንጥረው ወደ ጥልቁ ባህር ይጣሉ።

ገበሬውን ስናነሳ ስለመሬት ፖሊሲ ማንሳታችን አይቀሬ ነው። ስለመሬት ባለቤትነትም ቢሆን ነፃው ፕሬስም ሆነ አገር ወዳድ ግለሰቦችና ድርጅቶች የቻሉትን ያህል መንግሥት ፖሊሲውን እንዲያሻሽል ቢለፈልፉም ቢወተውቱም ለመደመጥ አልታደሉም። ጆሮ ያለው ሲገኝ አይደል መደመጥ የሚቻለው፤ ታዲያ ኢህአዴግ ጆሮ አለው ያላችሁ ማነው? እኔም ሰሚ አገኛለሁ ብዬ ስለመሬት ፖሊሲው አልለፈልፍም። የጽሑፌ ዓላማ ግብርና ሚኒስቴር አካባቢ ያሉ ባለስልጣናትና ሙያተኞች ጆሮ ካላቸውና ካደመጡ አንዳንድ ተጨባጭ እውነታዎችን ለመናገር እወዳለሁ። አንብበው አስተያየት መስጠት በመደገፍ፣ በመቃወም፣ ወይም የራሳቸውን ዕይታ ከቻሉም መልካም ነውና ንጋት ታስተናግዳቸዋለች። መንግሥትም ቢሆን ስለመሬት ጉዳይ ለማንሳት ስለማልሞክር ጆሮ ካለው ያድምጥ። ቢዋጥለትም ባይዋጥለትም ማድመጡ አይከፋም። ለማንኛውም እኔ ወደ ርዕሰ ጉዳዬ እገባለሁ።

ምዕራብ ሐረርጌ አካባቢ የዛሬ አምስት ዓመት ከተከሰተ አንድ እውነታ ልጀምር። በአንድ ወረዳ ውስጥ በግብርናው መስክ የተሰማሩ ሁለት ድርጅቶች ነበሩ - በወቅቱ። አንደኛው ኬር (መንግሥታዊ ያልሆነና የውጭ አገር ግብረሰናይ ድርጅት) ሲሆን፣ ሁለተኛው የወረዳው ግብርና ጣቢያ ነበሩ። እንደሚታወቀው ኬር ኢትዮጵያ በተለይ በሐረርጌ አካባቢ ስንዴ፣ ዘይትና የመሳሰሉትን በእርዳታ መልክ መስጠት ካቆመ ሰባት ዓመታት አልፈውታል። እናም ከገበሬው ጋር በመተባበር ለገበሬው አስፈላጊ የሆኑ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ይገነባል እንዲሁም ሙያዊ እገዛ ያደርጋል።

ሐረርጌ በቡና ምርት ትታወቃለች። በዚያ ወረዳ ያለው የግብርና ጣቢያ የቡና ምርጥ ዘር በማፍላት ለገበሬው በሽያጭ ያቀርብለታል። ገበሬው ያንን ችግኝ በመግዛት የቡና ምርቱን ለማሳደግ ለዓመታት ጥረት ቢያደርግም ሊሳካለት አልቻለም። "ምርጥ" የተባለው የቡና ችግኝ አንዴ አፍርቶ ይቀነጭራል፣ በቡና በሽታ ይጠቃል። በግብርና ጣቢያው ያሉ ኤክስፐርቶች ምርጥ ዘሩ የሚላክላቸው ከአዲስ አበባ ነበር። ምርጥ ዘሩ እዚያ ሲሄድ ግን ውጤት ማምጣት የሚችል ሆኖ አልተገኘም።

በአጋጣሚ በአካባቢው ያለው የኬር ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ለዚያ ወረዳ ገበሬዎች ሁለት ሠራተኞቹን ይልካል። ሁለቱም በግብርና ሳይንስ በዲፕሎማ የተመረቁ ወጣቶች ነበሩ። እዚያ ወረዳ ሲላኩ የተሰጣቸው ሥራ ገበሬውን በማደራጀት የውሃ ጉድጓድ ለመሥራት ነበር። የውሃ ጉድጓዱ የሚሠራበት ወጪ የሚሸፈነው በኬርና በገበሬው ነው። ኬር መጠነኛ ገንዘብና ሙሉ ለሙሉ ሙያተኞችን ሲያዋጣ፤ ገበሬዎቹ ደግሞ የሰው ኃይልና ከኬር ከፍ ያለ ገንዘብ በማዋጣት የውሃ ጉድጓዱ ይሠራል። ተሠርቶ ሲያልቅ ገበሬው (የአካባቢው) የራሱ ኮሚቴ አዋቅሮ ሕግና ደንብ አውጥቶ የራሱ ያደርገዋል። ኬር ከዚያ በኋላ አያገባውም። እነኚያ ሁለት ወጣቶች በአካባቢው የነበረውን የቡና ምርት መቀነስ ከገበሬዎቹ እንደተረዱ ለድርጅታቸው ወዲያውኑ ያሳውቃሉ። ኬርም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ጥናት አጥንተው ፕሮጀክት እንዲነድፉ ይስማማል። ሁለቱ ወጣቶች ከገበሬው ጋር አብረው በመዋልና በማደር ሁኔታውን ሲያጠኑ ይሰነብታሉ። በመጨረሻም የአካባቢውን ገበሬዎች ይሰበስቡና ውይይት ይጀምራሉ። ከገበሬዎቹ ተመሳስለው ጫት እየቃሙ።

ገበሬዎቹም ችግራቸውን አንድ በአንድ ይዘረዝራሉ። የቡና ምርታቸው የቀነሰው በአካባቢው ያለውን የቡና በሽታ የሚቋቋም የቡና ዘር ባለማግኘታቸው እንደሆነ፣ በዚህም ምክንያት የቡና እርሻቸውን ወደ ጫት እርሻነት እየቀየሩ መሆኑን፣ የወረዳው ግብርና ጣቢያ "ምርጥ ዘር" ብሎ የሚሸጥላቸው የቡና ችግኝ ውጤት እንዳላስገኘላቸው፣ ... ሌላም ... ሌላም ...

ሁለቱ የግብርና ሙያተኞች ጥያቄ ይጠይቃሉ፤ ገበሬዎቹ ይመልሳሉ። አንዱ ገበሬ ሲሳሳት ሌላው ያርመዋል። ገበሬዎቹ እርስ በእርሳቸው ይከራከሩና በክርክሩ የረታው ወገን ሃሳብ ተቀባይነት ያገኛል። ወጣቶቹ እዚያ ወረዳ ተወልደው ያደጉ ባይሆኑም የአካባቢውን ቋንቋ (ኦሮምኛ) አቀላጥፈው ስለሚናገሩ የገበሬዎቹ የእርስ በእርስ ክርክር አላመለጣቸውም። እነሱ ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተማሩትን ገበሬዎቹ ከልምድ ያውቁታል። ሁለቱ ወጣቶች ገበሬዎቹ ከሚሰጡት አስተያየት ውስጥ በትምህርት ቤት ሳይማሩት የቀረ ነገር እንዳለም ተገንዝበዋል።

ወጣቶቹ ከእናንተ ውስጥ በየዓመቱ የቡና ምርቱ የማይስተጓጐልበት አለ ወይ? የሚል ጥያቄ ሰነዘሩ። ገበሬዎቹ ከረዥም ክርክርና ንትርክ በኋላ ከመሃከላቸው አንዱን ገበሬ ጠቆሙ። (የገበሬው ስም መሐመድ ነው) ምክንያቱን ሲጠየቁ ምክንያታቸውን ዘረዘሩ። ወጣቶቹ አሁንም ጥያቄ አነሱ። የመሐመድ ቡና በበሽታ ይጠቃልን? ገበሬዎቹ እንደማይጠቃ መሰከሩ። ወጣቶቹ ውይይቱ እንዲቋረጥ አልፈለጉም ነበርና ውይይቱን አረዘሙት። የውይይቱ መርዘም "ሌቦች" ራሳቸውን እንዲያጋልጡ አስገደዳቸው።

"ሌቦች" ግለሂስ አደረጉ። አንዱ ደፋር ገበሬ "ለምሳሌ እኔ አሳቻ ሰዓት ጠብቄ ከመሐመድ የቡና እርሻ ሁለት እግር ችግኝ ሰርቄ እኔ እርሻ ላይ ተክዬ ነበር። እስከ አሁን ድረስ ያፈራሉ" ብሎ ሌብነቱን በራሱ ላይ መሰከረ። ሌሎችም ገበሬዎች ግለሂስ አድርገው ሌብነታቸውን አጋለጡ።

ወጣቶቹ ከዚህ ውይይት በኋላ አንድ መደምደሚያ ላይ ደረሱ። ከዚያ በፊት ግን የመሐመድን የቡና እርሻ ጐበኙ። በቡና በሽታ የተጠቃ አንድም የቡና እግር በእርሻው ውስጥ አልነበረም። ጥናታቸውን ስላጠናቀቁ ፕሮጀክት ነድፈው ለመስሪያ ቤታቸው አቀረቡ። ፕሮጀክታቸው ለገበሬው ችግኝ ጣቢያ መስራት፣ ገበሬውን በችግኝ አፈላል ማሰልጠንና ችግኝ ጣቢያውን ለገበሬው ማስረከብ ነው።መስሪያ ቤቱም ፕሮጀክቱን አጥንቶ አስፈላጊውን በጀትና ማቴሪያል መደበላቸው። ለችግኝ ማፍያ መሬት ያስፈልጋቸው ነበርና ከሚመለከተው አካል የሚፈልጉት መሬት ተፈቀደላቸው። ከዚያም ፕሮጀክታቸውን መተግበር ጀመሩ።

በዕቅዳቸው መሰረት ከመሐመድ ላይ በርካታ ኪሎ ቡና ከመደበኛው የአካባቢ መሸጫ ዋጋ ከፍ አድርገው ገዙት። የገዙትን የቡና ምርት (ፍሬ) በተሰጣቸው መሬት ላይ የችግኝ ማፊያ መደብ አዘጋጅተው ስለነበር ችግኝ ማፍላቱን ተያያዙት። ይህንን ሲያደርጉ ከገበሬዎቹ ውስጥ አንድ ቡድን አዋቅረው ነበር። የችግኝ መደብ አሰራሩን፣ የችግኝ አፈላሉን፣ ችግኙ ተወስዶ እስኪተከል የሚደረግለትን እንክብካቤና አያያዝ ለተቋቋመው የገበሬዎች ቡድን አስተማሩት። ችግኙ ፈልቶ ለመተከል ዝግጁ ሲሆን ለገበሬው ሸጡለት። የሽያጩ ገቢ የሚውለው ለችግኝ ጣቢያው እንጂ ለኬር አይደለም።

ገበሬዎቹ ገዝተው መትከል ጀመሩ። ገና ከጅምሩ ውጤቱን አወቁት። የቡና ተክሉ እያደገ ሲሄድ በበሽታ እንደማይጠቃ አረጋገጡ። ይህንን የተረዱት ሁለቱ ወጣቶች በድጋሚ ከመሐመድ ላይ ቡና ገዝተው ችግኝ አፈሉ። በዚህ ጊዜ አንድ ችግር ተፈጠረ። የወረዳው ግብርና ጣቢያ የቡና ችግኝ የሚገዛው አጣ። የፈላው ችግኝ እስከመበላሸት ደረሰበት። "ከሰርኩ" ብሎ ክስ መሰረተ። ክሱን ያቀረበው ለወረዳው መስተዳድር ነበር።

የወረዳው መስተዳድር የግብርና ጣቢያው የመሰረተውን ክስ ተቀብሎ ኬር እና ገበሬዎቹ የሚሉትን አድምጦ ውሳኔ ለመስጠት ተቸገረ። ጉዳዩ ከወረዳው አልፎ ወደ በላይ አካል ዘለቀ። በመጨረሻ የወረዳው ግብርና ጣቢያ ተሸነፈ። ሽንፈቱን ወዶ ሳይሆን በግዱ ተቀበለና በአካባቢው ያደርግ የነበረውን ችግኝ የማፍላትና የመሸጥ ሥራ አቆመ። ኬርም የችግኝ ማፊያ ጣቢያውን ለገበሬው በባለቤትነት አስረክቦ ለሌላ ፕሮጀክት ሁለቱን ወጣቶች ወደ ሌላ ወረዳ አሰማራቸው። የአካባቢው ገበሬዎች ራሳቸውን ችለው የችግኝ ጣቢያውን በጋራ ለማስተዳደር በቁ። የቡና እርሻቸውን ወደ ጫት እርሻነት የቀየሩትም መልሰው ወደ ቡና እርሻነት ቀየሩት። ቡና ማምረትም ጀመሩ። ውጤት ያለው ሥራ።

ይሄንን ያህል ስለሁለቱ ወጣቶችና ስለቡና የዘበዘብኩት ካለምክንያት አለመሆኑን ትረዱኛላችሁ ብዬ አምናለሁ። ሁለቱ ወጣቶችና ኬር ከላይ በዘረዘርኩት የቡና ተክል ዙሪያ ላስመዘገቡት አመርቂ ውጤት መሰረቱ ከገበሬዎቹ ጋር ተዋህደው መሥራት መቻላቸው (በተለይ ሁለቱ ወጣቶች) እንደሆነ ግልጽና የማያሻማ ነው። ገበሬው የሚጠጣውን ጠጥተው፣ የሚበላውን ተመግበው፣ የሚተኛበት ላይ ተኝተው መቀላቀላቸው ነው ለችግሩ መፍትሄ እንዲያገኙለት ያስቻላቸው። ገበሬውን ሳይንቁት አክብረው የሚለውን መስማት መቻላቸው ወጤታማ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

ኬር ደግሞ የችግኝ ጣቢያውን ከመሰረተ በኋላ ካለማቋረጥ ገቢ ሊያስገኝለት የሚችል ሆኖ ሳለ ለገበሬዎቹ "የእናንተ ነውና ተቆጣጠሩት - ተጠቀሙበት - እዘዙበት - ፍለጡበት - ቁረጡበት - እንዳሻችሁ አድርጉት ..." ብሎ የባለቤትነት መብት ሰጥቷቸው በስርዓት አስረክቧቸዋል። ከዚህም ሌላ ገበሬው ሙያዊና ቁሳዊ እገዛ ባሻው ቁጥር ኬርን ይጠይቃል - ኬርም እገዛውን ይለግሳል፤ እንጂ ኬር ገበሬውን "ከዚህ በኋላ ሥራህ ያውጣህ!" ብሎ እስከመጨረሻ ጥሎት አይሄድም። ይሄ የኬር ተግባር ገበሬውን ለሥራ ከማነሳሳት ጀምሮ "የራሴ" የሚለው ሀብት እንዲኖረው አስችሎታል። የአካባቢው ገበሬ የራሱ የሆነ ችግኝ ጣቢያ ሳይኖረው ሦስት ሺህ ዓመታትን አሳልፎ ነበር። እዚህች ላይ እኛ ኢትዮጵያውያን "የኔ" የምንለውን ነገር እንዴት እንደምንንከባከበው ልብ እንድትሉልኝ እሻለሁ። ኬርም ይህንኑ ተገንዝቦ ነው የችግኝ ጣቢያውን ያስረከባቸው።

የወረዳውን ግብርና ጣቢያና በውስጡ ያሉትን "ኤክስፐርት" ተብዬዎችን ስንመለከት ደግሞ ከሥራቸው ጥፋታቸው ያመዝናል። ጣቢያው ከአካባቢው ገበሬዎች ጋር ራሱን አወዳድሮ እሱ የመንግሥት አካል በመሆኑ ተኮፍሶ ተቀምጦ ትኩረቱን ከችግኝ ሽያጩ በሚያገኘው ገንዘብ ላይ አድርጓል። "ኤክስፐርት" ተብዬዎቹ ገበሬውን ተጠግተውና አካባቢውን መስለው ከመኖር ይልቅ የግል ጐጆአቸውን በማሞቅ ሥራ ላይ ተወጥረው ስለነበር ውጤት ያለው ሥራ መስራት አልቻሉም።

ገበሬው የሚያስፈልገው "እናውቅልሃለን" ብለው የሚያስገድዱት አካላት፣ ተቋማትና ግለሰቦች አይደሉም። ለዚህም ነው የግብርና ጣቢያውና 'ኤክስፐርቶቹ' ውጤት ያለው ሥራ ሳይሰሩ የቆዩት።

የአገራችን ገበሬ ካለበት ችግር ሊላቀቅ የሚችለው "ማዳበሪያ በብድርም ቢሆን ካልገዛህ ወየውልህ!" እየተባለ ሳይሆን ቀረብ ብለነው የችግሮቹን መንስዔዎችና መድኃኒቱን አብሮን እንዲፈልግ ስናደርገው ብቻ ነው። መንግሥት፣ ግብርና ሚኒስቴር፣ በግብርና መስክ የተሰማሩ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች፣ የግብርና ሙያተኞች፣ ... "ገበሬውን እናውቀዋለን"ን ትተው መጀመሪያ አብረውት ለመኖር ጥረት ያድርጉ። አብረውት መኖር ቢጀምሩ የገበሬውን ማንነትና ምንነት ማወቅ ይችላሉ። ማንነቱንና ምንነቱን ካወቁ ደግሞ ችግሩን ለይተው ማወቅ የማይችሉበት ምክንያት የለም። ችግሩን ሲያውቁለት ደግሞ መድኃኒቱን ለማግኘት ይቀላል።

መድኃኒት ፍለጋው ላይም ሆነ በማናቸውም ሥራ ላይ ገበሬውን ማሳተፍ ውጤታማነትን ያጐለብታል። በመሆኑም ከተማ ተቀምጦ ስለገበሬው በሽታ (ችግር) እና መድኃኒት ከማውራት ይልቅ ገበሬውን ተቀላቅሎና መስሎ በመኖር መፍትሄ ለማግኘት መጣር ያዋጣል። "ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም" እንደሚባለው ሁሉ መንግሥትም በገበሬው ስም የሚያለቅሰው ከልቡ ከሆነ የገበሬውን ሕይወት ለመቀየርና ለማሻሻል የማይችልበት ምክንያት የለም። አይኖርምም።

 

ወደ አስተያየት/ትችት ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

Hosted by www.Geocities.ws

1