ወደ ስደት ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

 

ከ፦ስደተኛው - ፬

የቤተሰብ ፍቅር

ያሬድ ክንፈ ከስዊድን (የንጋት ዋና � ዘጋጅ)

************************************

እንደምን ከረምክልኝሳ ጌትዬ? እኔ አንድዬ የተመሰገነ ይሁን እተነፍስልሃለሁ። ‘ናፍቆት’ አይገባኝም ነበርና ’ባክህ። እኔና አንተ ብዙም ልዩነት እንደሌለን እርግጥ ነውና በል እንግዲህ አድምጠኝማ።

“ምን ናፈቀህ?” ብለህ ብትጠይቀኝ “ያልናፈቀኝን ጠይቀኝ” የሚል ነው ምላሼ። ካገርህ ስትወጣ አገርህ፣ ቤተሰብህ፣ ጓደኞችህ፣ … ብቻ አይደለም የሚናፍቁህ አየሩ ሁሉ ሳይቀር ይናፍቅሃል። ስንቱን ዘርዝሬ እንደምጨርስልህ ባላውቅም እስቲ ልሞክር።

ሃያ አንደኛዋ የቤት አከራዬ ወ/ሮ ጣይቱን አስታወስካቸው? ለቤት ኪራይ የከፈልኳቸው ገንዘብ ወሩ አጋማሽ ላይ ስታልቅባቸው ነው መሰል በገባሁ በወጣሁ ቁጥር የሚነዘንዙኝና በነገር ጠቅ የሚያደርጉኝ፣ ያቺ ነገረኛና ባለአለብላቢት ምላሳሟ ያንተ የቤት አከራይ፣ እኛ “ማታ ማታ ወይም ጠዋት ጠዋት ካልሆነ ውሃ መቅዳት አትችልም፤ ሊያውም አንድ ባልዲ” ይሉኝ የነበሩት የመጀመሪያው የቤት አከራዬ - አቶ አበበ፣ በየተከራየሁባቸው አርባ ሦስት ቤቶች አካባቢ ያሉ ባለሱቆች፣ ብድር ይከለክሉኝና ይሰጡኝ የነበሩት ባለሱቆች፣ “ሽንት ቤት ብዙ ትጠቀማለህ፣ በዚህ ላይ ጓደኞችሁ ሁሉ በመጡ ቁጥር ሽንት ቤት ሳይገቡ አይሄዱም” ብለው ከቤታቸው ያስለቀቁኝ ሰላሳኛው የቤት አከራዬ፣ “ጓደኛ ታበዛለህ” - “አምሽተህ ትገባለህ” - “ስትወጣና ስትገባ ሠላም አትለኝም” - “ስትወጣና ስትገባ አትታይም” - “የግል ጋዜጣ ላይ እንደምትሠራ ለምን አልነገርከኝም” - “የግል ጋዜጣ ታነባለህ” - “ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ መብራት ለምን ታበራለህ?” … ብለው እያሉ ከቤታቸው ያስለቀቁኝ የቤት አከራዮቼ ሁሉ ናፍቀውኛል። ጓዴ በ’ናትህ አጠገባቸው እስካለህ ድረስ ምን ቢበድሉህ፣ ቢያስቀይሙህና ቢጠሉህ፤ አንተ ግን ውደዳቸው። እንደኔ ከተሰደድህ የነሱ ሁሉ ናፍቆት አያስቀምጥህምና።

የሚገርምህ ሰዎቹ ብቻ አይደሉም የሚናፍቁህ። ሌላ ሌላውም ጭምር ነው። እዚህ ስዊድን በየመንገዱ ቆሻሻ አታይም። በየሄድክበት ሁሉም ነገር ንፁኅ ነው። ሻይ ቤት ወይም ምግብ ቤት ገብተህ ባንድ እጅህ ዝንቦች እያባረርህ በሌላኛው አትጠጣም። አትበላም። "ልበላ ነው ዝንብ ላባርር ገንዘቤን የከፈልኩት" ብለህ የቤቱን ባለቤት አታሳቅለውም። ስዊድን ውስጥ ዝንቦቹ ከነመኖራቸው እስክትጠራጠር ድረስ ንጡህ ነች። የትም ሄደህ ንፁኅ ሽንት ቤት (መፀዳጃ ቤት) ነው የሚገጥምህ። መፀዳጃ ቤት የሌለው ቤት ከነጭራሹ አይሰራም። በየመንገዱ የሚፀዳዳ የለም - ነውርም ነው። ከፈለግህ ገንዘብ ከፍለህ በህዝብ መፀዳጃ ቤቶች ትፀዳዳለህ። የህዝብ መፀዳጃ ቤቶቹን በየሄድክበት ታገኛቸዋለህ። እነሱን ካጣህ እንዳሸን ከፈሉት ሱፐር ማርኬቶች አንዱ ጋር ጎራ ብለህ ዕቃ ከገዛሃቸው በነፃ፣ ሽንት ቤቱን ብቻ ከፈለግህ ገንዘብህን ከፍለህ ሸክምህን ታቀላለህ። በነገራችን ላይ ሰው ቤት ሄደህ ሽንት ቤታቸውን መጠቀም ከፈለግህ "ሽንትቤታችሁን መዋስ እችላለሁን?" ብለህ በአክብሮት መጠየቅ ባህል ነው። ጓደኛህ ቤትም ቢሆን እንኳ በአክብሮት ትጠይቀውና ሲፈቅድልህ ነው የምትፀዳዳው እንጂ፤ ብድግ ብለህ የሰው ሽንት ቤት ከፍተህ መግባት ከነውር ይቆጠራል። ተፀዳድተህ ስትመለስ "ሃሪፍ ነበር?" ተብለህም ትጠየቃለህ። ሸክም ማቃለል ያስደስት የለ?!

ለዓይን የሚማርክ ነገር ነው በየሄድክበት የምታገኘው። ክረምቱ ሊገባ ሲል (በረዶው ሊጀምር ሲል) የዛፎቹ ቅጠሎች በሙሉ ወደ ቢጫነት ይለወጣሉ፣ ከጥድ በቀር። (በነገራችን ላይ ገና በበረዶ ወራት ስለሆነ ቤት ውስጥ ከሚተከሉት ዕፅዋት በተቀር ውጪ በረዶው ላይ አረንጓዴ ሆኖ የምታገኘው ጥድ ብቻ ስለሆነ ነው ለገና ጊዜ በገና ዛፍነት የሚጠቀሙበት። ጥጥ ጣል ጣል የሚደረግበት ደግሞ የበረዶው ምልክት መሆኑ ነው።) ከዚያ ቅጠሎቹ በሙሉ ይረግፋሉ። ይሄኔ የፅዳት ሠራተኞቹ ለቅመው ከመንገዱ ላይ ያነሷቸዋል። በበጋ ጊዜ አቧራ የሚባል ነገር የለም። የሰዉም፣ የሳይክለኛውም፣ የመኪናውም መንገድ ሁሉ አስፋልት ወይም ድንጋይ የተነጠፈበት ነው። የተቀረው ደግሞ በሳር የተሸፈነ ነው። ስለዚህ አቧራ አይገጥምህም፣ እንቅፋት አይመታህም። ድንጋይ በየመንገዱ የለማ። እዚህ አገር ከገባሁ ጫማዬን ቀለም የቀባሁበት ቀን ትዝ አይለኝም።

“የአህያ ስጋ አልጋ ሲሉት አመድ” ብለህ ብትተርበኝም ግድ የለኝም እውነቱን ግን እነግርሃለሁ። እንዲህ ሁሉም ነገር ንፁኅ ሆኖ ሳለ ግን የኛ አገሩ አቧራ፣ ጭቃው፣ እንቅፋቱ፣ በየመንገዱ የሚጣለው ወረቀታ ወረቀት፣ ቁሻሻው፣ ሰገራው፣ በየመንገዱ የሚሸተውና የሚገማው፣ በየመንገዱ የሚሸናውና የምሸናው፣ የሚፀዳዳውና የምፀዳዳው፣ አሴ ሻይ ቤትም ሆነ እንትና ምግብ ቤት ከዝንብ ጋር እየተሻማሁ የምመገበውና የምጠጣው፣ ሰገራ ስቀመጥ እየተንቦራጨቀና እየተፈናጠቀ ቂጤን (መቀመጫዬን) ይበክሉት የነበሩት የተከራየሁባቸው ቤቶች ሽንት ቤቶች፣ እነኛ አፋቸው ጢም ብሎ የሞሉት የካዛንችስ ቡና ቤቶችና የፋይቭ ዶሮቹ ሽንት ቤቶች፣ በየመንገዱ የማይታጡት የኔቢጤዎች፣ ይገላምጡኝና አላስገባ አላስወጣ ይሉኝ የነበሩት የድሮ የኪራይ ሰፈሮቼ ጎረምሶች፣ … ሳይቀሩ ይናፍቁኛል።

ናፍቆቱ እያደር እየጨመረ ይሄድና ለግድያ የምትፈልገው ጠላትህ ቢኖር እንኳ ይናፍቅሃል። “ምነው አብሬአቸው ዘላለም ብኖር” ብለህ ልትል ሁሉ ትችላለህ። ጌትዬ! የኔ ምክር ምን ጠላትህ ቢሆን እንኳ ውደደው፣ አፍቅረው። እሱ/ሷ ፍቅር ካልሰጡኝ እኔ አልሰጥም ብለህ ጨካኝ አትሁን። ደግ ሁን። ውደዳቸው። አፍቅራቸውም። እንደኔ ተሰደህ የናፍቆት ትርጉሙ እስኪገባህ ድረስ አትጠብቅ።

ጌትዬ! ስለስዊድን እስከዛሬ የጣፍኩልህ ጥሩ ጥሩውን ነገር ብቻ በመሆኑ “መንግሥተ ሰማያት” ነው ብለህ አታስብ። ወይም ደግሞ የምትፈልገውን ነገር ሁሉ የምታገኝበት አገር/ዓለም አድርገህ አታስበው። ስለስዊድን በነገርኩህ ቁጥር ሌላውም አውሮፓ ተመሳሳይ መሆኑን አትዘንጋ። እስቲ ባቅሜ የታዘብኩትን ላካፍልህ።

ባለፈው እንዳልኩህ ሰዎቹ ለሥራ ትልቅ ፍቅር አላቸው። በተቃራኒው ደግሞ ለቤተሰብ ያላቸውን ፍቅር ከኛ አገሩ ጋር ስታወዳድረው አይገናኝም። እኛ እንበልጣቸዋለን። በነሱ አመለካከት ግን እኛ ስህተተኞች ነን። የተጋቡ ወይም አንድ ላይ የሚኖሩ ወንድና ሴት ልጅ ከወለዱ፣ ከሁለት አንዳቸው ለስምንት ወር ወይም ለአንድ ዓመት ሥራ የማቆም መብት አላቸው። ሥራ ሲያቆሙ ደሞዛቸው አይቆምም። እረፍታቸው ካበቃ በኋላ በሥራ ሰዓታቸው ልጁን መዋዕለ ሕፃናት (በስዊድንኛ ‘ዶጊስ’) ያውሉታል። በስምንት ወሩ። ከልጃቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ በጣም ጥቂት ነው። በዚህና በሌሎች ምክንያቶች እዚህ አገር በቤተሰብ መሃል ያለውን ፍቅርና መተሳሰብ ካጀማመሩ የላላና የላሸቀ ይሆንና በዚያው ይቀጥላል - እንደላላና እንደላሸቀ። ስዊድን ያለውን የቤተሰብ ፍቅር ከእኛ አገሩ ጋር ስታወዳድረው የእኛ እንደሚበልጥ አትጠራጠር።

ልጆችም ወላጆችም ሁሉም ለራሱ እንጂ ለሌላው ግድ የለውም። ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ጊዜአቸውን ከሚያሳልፉ ሥራ ሠርተው ገንዘብ ቢያገኙበት ይመርጣሉ። እዚህ አገር ከሁሉ በላይ የሚፈቀረው ገንዘብ ነው። ገንዘብ ከሌለህ ምንም ማድረግ አትችልም። ሱቅ ገብተህ የአንድ ሺህ ክሮነር ከሃምሳ ሣንቲም ዕቃ ገዝተህ ሃምሳ ሣንቲሟ ብትጎድልህ ባለሱቁም ሆነ አብራህ ያለችው እናትህ ብትሆን እንኳ ሽልንጓን አይሞሉልህም። “የራስሽ ጉዳይ ... የራስሽ ጉዳይ …” ነው ያለው ዘፋኙ? በቃ እንደሱ ነው ሁሉም ነገር።

ልጅ አባቱን “የቤቴን የግድግዳ ቀለም/ወረቀት ስለምቀይር ልትረዳኝ ትችላለህን?” ብሎ ቢጠይቀውና አባትየው “አዎ!” ከሆነ ምላሹ፤ ልጅየው ቀጥሎ ማለት የሚገባው “በሰዓት ይህን ያህል እከፍልሃለሁ” ነው። አባትየው መግደርደርም ሆነ ሌላ ነገር ማለት አይገባውም “እሺ!” እንጂ። ክፍያው ካልተስማማውና ቅር ካለው “ክፍያውን ጨምር” ሊለው መብቱ ነው። ይሉኝታ ብሎ ነገር አይሠራም። አባት ለልጁ ማሽን ወይም የተለየ መሳሪያ በተውሶ አይሰጥም፤ ያከራያል እንጂ። ልጅ ትርፍ ዕቃ ኖሮት እናቱ ዕቃውን ብትፈልገው ይሸጥላታል እንጂ በነፃ አይሰጣትም። ደግ ከሆነ ያውሳታል፤ የራስዋን እስከትገዛ። እናት የባንክ ሂሳቧ ውስጥ ለምን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አይኖራትም ለልጇ ገንዘብ ታበድራለች እንጂ በነፃ አትሰጠውም፤ መቶ ክሮነርም (ብርም) እንኳ ቢሆን። ወዳጅህ፣ ጓደኛህ፣ አባትህ፣ እናትህ፣ እህትህ፣ ወንድምህ፣ … በጉልበትህ ወይም በዕቃ እንድታግዛቸው ከጠየቁህና ካገዝካቸው እንደእገዛህ አይነት አስልተው የሠራህበትን ይከፍሉሃል። አንተም በተራህ እንዲሁ። ምንም ነገር ነፃ አይደለም፤ ከስጦታ በቀር። ለዚህም ነው መሰል “ግራቲስ ኤ ጎት” (ነፃ ነገር ይጣፍጣል) ይላሉ። የፈለገህ አይነት ሆቴል ወይም ቡና ቤት አልያም ሻይ ቤት ገብተህ ጉርሻ ሳትሰጥ ብትሄድ የሚገላምጥህ የለም። ይልቅስ የምትገለመጠው ጉርሻ ሰጥተህ ብትሄድ ነው።

እዚህ አገር ሰዎች ሲያረጁና ሲደክሙ ወደ ለአሮጊቶችና ለሽማግሌዎች የተዘጋጀ መጠለያ ይገባሉ። አልያ ቤታቸው እየሄደ የሚረዳቸው ይመደብላቸዋል። እናታቸው፣ አባታቸው፣ አያታቸው ወይም ቅድመ አያታቸው ከደከሙና ወደእርጅና መጠለያ ከገቡ ወይም ደከም ብለው እቤታቸው መዋል ካዘወተሩ ምናልባት - ምናልባት በጣም የቤተሰብ ፍቅር ያለበት ሰው በዓመት አንዴ ወይም በሁለት ዓመት አንዴ ሄዶ ይጠይቃቸዋል። ልብ በል እሱንም ‘ምናልባት’ ነው። እንደኛ አገር እናት፣ አባት፣ አያት፣ ቅድመ አያት፣ አክስት፣ አጎት፣ … ጎረቤት፣ ... መርዳት፣ መጠየቅ፣ ለበዓል 'እንኳን አደረሳችሁ!' ማለት፣ አክፋይ ይዞ መሄድ፣ …. ብሎ ነገር የለም። አልፎ አልፎ ከእናትና ካባታቸው ጋር ጥሩ ግንኙነት ያላቸው ሊያጋጥሙ ይችላሉ። የእነሱንም ግንኙነት ጠለቅ ብለህ ስትጠይቅ ስቀህ ወይ ተገርመህ ታልፋለህ - አልሸሹም 볊ር ነውና።

እዚህ አገር የትራንስፖርቱን ቅልጥፍና ልነግርህ አልችልም። የትኛውም ክፍለሀገር ለመሄድ አዳር አያስፈልግህም፤ ሊያውም ባቡርና ኦቶቡስ ተጠቅመህ። በኦቶቡስ የሦስት መቶ ኪሎሜትሩን መንገድ በሦስት ሰዓት ውስጥ (ሊያውም ባነሰ) ትጓዘዋለህ። የቤት መኪና ከሆነ ደግሞ ከበዛ በሁለት ሰዓት ከሃያ። እናቱ እሱ ካለበት ከተማ ሦስት መቶ ኪሎ ሜትር የማይሞላ እየኖረች ለአስር ዓመት አግኝቷት አያውቅም ሲባል ስትሰማ ይሰቀጥጥሃል። ተጣልቷት እንዳይመስልህ፤ ምክንያቱ በጣም ሥራ ስለሚበዛበት ነው። “ለእምዬ ነው ሥራ የሚበዛበት!?” አያሰኝም? ቅድም የቤተሰብ ፍቅር ገና ካጀማመሩ የላላና የላሸቀ ነው ያልኩህ ለዚህ ነው። እናትም “ልጄ ጠፋ” ብላ ሃሳብ አይገባትም። ጉዳይዋ አይደለም። ተገናኝቶ ስለመጠያየቁ ሲገርምህ ስልክ እንኳ ተደዋውለው የማያውቁ አሉ ብልህ ምን ይሰማሃል?

አንዳንድ እውነተኛ ክስተቶችን ልንገርህ። አንዳንድ ሰዎች በርቀት መነጽር የሌሎች ሰዎችን ቤት ማየት ይወዳሉ። የዚህ አገር ቤቶች መስኮቶች ሰፋፊዎችና ባለመስታወቶች ናቸው። አንዷ አሮጊት ሁሌም እንደምታደርገው በርቀት መነጽሯ ባካባቢዋ ያሉ አፓርታማዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ቤቶች ስትመነጥር አንዱ ሰውዬ ቴሌቭዥኑን ከፍቶ ሶፋ ላይ ቁጭ ብሎ ታየዋለች። በማግስቱም ሰውየው ቲቪ እያየ ነው። በሦስተኛውም ቀን እንዲሁ። መጨረሻ ላይ ሊያውም ሣምንት ካለፈው በኋላ ለፖሊስ ደውላ ታሳውቃለች። ፖሊስ ሰውየው ቤት ሄዶ ቢያንኳኳ አይከፈትለትም። ሰብረው ሲገቡ ሰውየው ከሣምንት በፊት ለዘለዓለሙ አሸልቧል።

ፖስታ የሚደርስህ በበርህ ቀዳዳ ነው። የፖስታ ሣጥን ቁጥር አያስፈልግህም። በቤትህ አድራሻ በበርህ ቀዳዳ ዘወትር ይመጣልሃል። ደብዳቤ የሚልክልህ ወዳጅ ዘመድ ከሌለህ የምታነበው አታጣም። የማስታወቂያ ጋዜጦች፣ አንዳንድ የንግድ ተቋማት፣ መስሪያ ቤቶች፣ … ይልኩልሃል። የማስታወቂያ ጋዜጦቹና መጽሔቶቹ ብዛታቸውንና ክብደታቸውን ልነግርህ አልችልም። አንዱ ፖስተኛ አንደኛው በር ቀዳዳ ውስጥ ለማስገባት እየቸገረው ይመጣል። አንድ ቀን ፖስታ በመክተቻው ቀዳዳ አጮልቆ ሲመለከት ለረዥም ጊዜ የከተታቸው ፖስታዎች ተከመረው ስለነበር ኖሯል ማስገባት የተቸገረው። በዚህ ላይ የዚያ አፓርታማ ጠረን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጠ መጥቶ ነበርና ለፖሊስ ያመለክታል። በዚህኛው ጊዜ ደግሞ አንዲት አሮጊት ሕይወቷ ካለፈ ወራቶች ተቆጥረዋል። ለልጆችዋ ስልክ ተደውሎ ማረፏ ተነገራቸው።

እናቱ ማረፏ በፖሊስ ሲነገረው “እኔ ሥራ ስለሚበዛብኝ፤ እናንተ አስቀብሯት” ብሎ የሚልም አለ። ከዚያም ፖሊስ ለቀብር ድርጅቶች ደውሎ ይነገራቸውና እነሱ ከፍነው፣ በሳጥን አድርገው፣ የቀብር ቦታ ተከራይተው ይቀብሯትና የሠሩበትን ሂሳብ ከሟችቱ አካውንት ይወስዳሉ። ልጅ ለናቱ/ቷ የቀብር ማስፈፀሚያ አይከፍልም/አትከፍልም።

እናት ልጇ ቤት ሳትደውል ከሄደች፣ ልጅየዋ በሩን ከፈት አርጋ በእጇ ይዛ እዚያው ደጃፉ ላይ እንደቆመች ሠላምታ ሳትሰጣት “ለምን ሳትደውይ መጣሸ?” ነው የመጀመሪያ ጥያቄዋ። “እማዬ! … እናቴ! …” ብሎ ጮሆ ማስተናገድ ምናምን ብሎ ነገር የለም። እናትየዋም እዚያው በር ላይ ቆማ ባለመደወሏ ይቅርታ ጠይቃ፣ የመጣችበትን ጉዳይ ተናግራ ከበሩ ትመለሳለች። የልጇን ዓይን ማየት ናፍቋት መጥታ ቢሆን እንኳ አየት አድርጋ ከበሩ ላይ ትመለሳለች። አለቀ ይኸው ነው።

ሌላም ሌላም የሚገርምና አስደንጋጭ ነገር ይደረጋል፣ ይሰማል። ዞሮ ዞሮ የዚህ ሁሉ ምክንያቱ የቤተሰብ ፍቅር አለመኖር ነው። አልፎ አልፎ፣ ሊያውም ከሺህ አንድ ከቤተሰቡ ጋር የሚጠያየቅ መኖሩን መስማት አስደናቂ ነገር ሆኖብኛል።

ጌታው! ለዛሬ አይበቃህም? በል እንግዲህ በሌላ ደብዳቤዬ እስክንገናኝ ሠላም ሁንልኝ! ሄይዶ!!!

ወደ ስደት ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

 

 

Hosted by www.Geocities.ws

1