ወደ ስደት ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

ከ፦ስደተኛው - ፪

ሥራ

ያሬድ ክንፈ ከስዊድን (የንጋት ዋና አዘጋጅ)

***********************************

እንዴት ነህ ’ባክህ ጌታው? ወዳጆቻችንስ እንዴት ናቸው? … እኔ አማን ነኝ። የስደት ሕይወት ባይጣፍጥም እየኖርኩት ነው። ከእርግማን ባትቆጥርብኝ ”ከስደት ይሰውርህ!” ብዬ ብመርቅህ ወደድሁ። ፭ (5) እና ፲ (10) ዓመት እዚህ ስቆይ ”ለስደት ይዳርግህ!” እንደማልልህ ግን እርግጠኛ አይደለሁም።

እዚህ ከመጣሁ ከተገረምኩባቸው ነገሮች አንዱ ”ሥራ” ነው። የፈለግህበት የመንግሥትም ሆነ የግል መስሪያ ቤት፣ ቢሮ፣ ሱቅ፣ ሱፐር ማርኬት፣ ሆስፒታል፣ መዝናኛ ቦታ፣ … ስትሄድ እንዴት ያለ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንደሚሰጡህ ልነግርህ አልችልም። ከምነግርህ በላይ ረክተህ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጉዳይህን ፈጽመህ፣ ሳትጉላላ፣ ቢሮክራሲ ሳይጫንህ - ሳይገላምጥህ - ሳያንጓጥጥህ፣ የምትሻውን አግኝተህ፣ … ወደቤትህ ትመለሳለህ። አንድ ጉዳይ ቢኖርህ የግድ እዚያ መስሪያ ቤት መሄድ የለብህም። የፈለግህበት ሆነህ ስልክ ደውለህ ወይም በኢንተርኔት ጉዳይህን ታስፈጽማለህ። የምትገዛው ነገርም ቢሆን እቤትህ ሆነህ ትገዛዋለህ። የገዛኸው ነገር በርህን አንኳኩቶም ይሁን ሳያንኳኳ ቤትህ ድረስ ይመጣልሃል።

የሆነ መስሪያ ቤት ጉዳይ አለህ እንበል። ከስልክ ማውጫ ላይ የመስሪያ ቤቱን ስልክ ትወስድና ትደውላለህ። (የስልክ ማውጫው በነፃ በየዓመቱ በየቤቱ ይታደላል)። የአንዳንዶቹ መስሪያ ቤቶች ስልኮች ኮምፒዩተራይዝድ ስለሆኑ መስመር ላይ እንድትቆይና ስንተኛው ተራ ጠባቂ እንደሆንህ ኮምፒዩተሩ ይነግርሃል። መስመሩ ላይ ካሉት አንድ ሰው ጉዳዩን ጨርሶ ስልኩን ሲዘጋ አንድ ቁጥር ቀንሶ ተራህን ደግሞ ይነግርሃል። አብዛኞቹ ጋር ደግሞ ስልክ ተቀባይዋ ካልመለሰችልህ የድምፅ መልዕክት ማስቀመጫው መልዕክትህን እንድታስቀምጥ ይነግርሃል። ስልክህንና ስምህን ትተዋለህ። ስልክ ተቀባይዋ ቆይታ መልዕክትህን ታገኘዋለች። እናም ትደውልልሃለች። አታውቃትም። አታውቅህም። የምትፈልገውን ነገር ትነግራታለህ። ምን ማድረግ እንዳለብህ በግልጽና በአጭሩ ትነግርሃለች። የግድ መስሪያ ቤቱ ድረስ መሄድ ካለብህም ትነግርሃለች። የምትሞላው ፎርም (ማመልከቻም ሊሆን ይችላል) ካለ አድራሻህን ትነግራታለህ የዛኑ ዕለት ትልከዋለች። ከየትኛውም የስዊድን ከተማ ትላንት የተላከ ፖስታ ዛሬ እቤትህ ድረስ ይመጣልሃል። (በሥራ ቀን)። የምትሞላውን ሞልተህ መልሰህ ትልክላታለህ። እንደመስሪያ ቤቱ አይነትና እንዳንተ ጉዳይ አይነት ይለያያል እንጂ ፎርሙን ሞልተህ በነፃ የምትልክበት የመስሪያ ቤቱ አድራሻ የታተመበት ፖስታ አንድ ላይ ይላክልሃል። የቴምብሩን ዋጋ (፭ /5/ ክሮነር - ፭ የኢትዮጵያ ብር ገደማ) ለፖስታ ቤቱ የሚከፍለው መስሪያ ቤቱ ይሆናል ማለት ነው። በፖስታና በስልክ ብቻ ጉዳይህን ትፈጽማለህ - ታስፈጽማለህ።

ብትታመም ወይም ሐኪም ማየት ብትፈልግ ስልክ ትመታለህ። የባሰብህ ካልሆንክ ቀጠሮ ይሰጡሃል። ቀጠሮው የዕለቱ ዕለት ወይም በቀናት ወይም በሣምንታት ወይም በወራት ሊራዘም ይችላል። ዶክተር ጋር የምትቀርብበት ቀንና ሰዓት ይነገርሃል። በሰዓቱ መገኘት የማትችል ከሆነ ቀደም ብለህ ደውለህ መናገር አለብህ። በነገራችን ላይ ስዊድን ከበለፀጉት አገሮች አንዷ ብትሆንም የዶክተሮች እጥረት አለባት። ለኦፕራሲዮን ፯ (7) ወር ልትቀጠር ትችላለህ - በሽታህ የ፯ ወር ዕድሜ የሚሰጥህ ከሆነ። አስጊ ከሆነ ግን ጊዜ አይሰጠውም።

ጥቁር ሆንክ - ቢጫ ሆንክ - ቀለም አልባ ሆንክ፣ ደሃ ሆንክ - ሐብታም፣ የተጎሳቆልክ ሆንክ ያማረብህ፣ ሞባይል ያዝክ አልያዝክ፣ እግረኛ ሆንክ ባለመኪና፣ ባለቤቢ ፊያት ሆንክ ባለሜርሴዲስ ወይም ባለፌራሪ፣ ወንድ ሆንክ ሴት፣ … የምትሄድበት መስሪያ ቤትም ሆነ የንግድ ቤት አስተናጋጅ ወይም እንግዳ ተቀባይ በትልቅ ፈገግታ ይቀበልሃል። ፊቱን አያከሰክስብህም፣ አይንቅህም፣ አያመናጭቅህም፣ ፊት አይነሳህም፣ …። እጅግ በሚማርክ መስተንግዶ ይቀበልሃል/ትቀበልሃለች። ማናገር ወይም መገናኘት ያለብህ የመስሪያ ቤቱ ሠራተኛ ካለ እንድታገኘው ትደረጋለህ።

አንዳንድ መስሪያ ቤቶችና ሱቆች ውስጥ ስትገባ ደግሞ ፊት ለፊትህ ማሽን ታገኛለህ። ቁልፉን ስትጫነው እላይዋ ላይ ቁጥር የታተመባት ብጫቂ ወረቀት ትወጣልሃለች። የወረፋ ቁጥርህ መሆኑ ነው። የአዲስ አበባ ባንኮች ውስጥ ገንዘብ ልታወጣ ስትሄድ የሚጠቀሙበት አይነት። ቁጥርህ በደወል ይጠራል ጉዳይህን ፈጽመህ ትወጣለህ።

ልብ ብለህ እንደሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ጉዳይ ለማስፈፀም የሆነ መስሪያ ቤት ሄደህ (የመረጃ ክፍል ያለውም ይሁን የሌለው፤ የአዲስ አበባውን ውልና ማስረጃ ቢሮንና ኢሚግሬሽንን አይጨምርም) ”ስለእንትን ጉዳይ የማናግረው የትኛውን ክፍል ነው?” ብለህ ስትጠይቅ ”፲፫/13 ቁጥር ሂድ” የሚል መልስ ታገኛለህ። ቢሮ ቁጥር ፲፫ ገብተህ ላገኘኸው ሠራተኛ ጉዳይህን ስትነግረው ”ይህንን ጉዳይ ፳፩ (21) ቁጥር ነው የሚመለከተው” ይልሃል። ቢሮ ቁጥር ፳፩ ስትሄድ ደግሞ ”ይሄንንማ ፶፫ (53) ቁጥር ነው የሚያየው” ይልሃል። ዕድለኛ ከሆንክ ፶፫ ቁጥር ስትሄድ ትክክለኛው ክፍል ሆኖ ታገኘው ይሆናል። እዚህ እንዲህ ብሎ ነገር የለም። እመስሪያ ቤቱ እንደገባህ ያናገርከው የመስሪያ ቤቱ ሠራተኛ ወይም እንግዳ ተቀባይ (የመረጃ ክፍል ሠራተኛ) በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከተውን ክፍል ይነግርሃል። ያገናኝሃል።

እኛ አገር ግብር ልትከፍል ከጠዋቱ ፪፡፴ (2፡30) ሰዓት ላይ ሄደህ ቢያንስ አምስትና ስድስት ቢሮዎች ማስፈረም አለብህ። ”ለሻይ ወጥተዋል” ተብለህ ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ አንዱን ’ለፊርማ የተቀመጠ’ ባለሥልጣን ልትጠብቅ ትገደዳለህ። የዚያን ቀን አምስቱንም ወይም ስድስቱንም ”ፈራሚዎች” ሳታገኝ ቀርተህ በማግስቱ ትመለሳለህ። አልያም ደግሞ ”ግምገማ ላይ ናቸው”፣ ”ተሃድሶ ላይ ናቸው”፣ ”የፓርቲ ስብሰባ ላይ ናቸው”፣ … ተብለህ አንድ ወር ወይም ከዚያ በላይ ትጠብቃለህ። አንዳንዴ ደግሞ ገንዘብ ተቀባይዋ ቢሮውን ቆልፋ ከጓደኞችዋ ጋር እያስካካች ”ገንዘብ ቆጠራ ላይ ነኝ” የሚል ወረቀት መስኮቱ ላይ ትለጥፍልሃለች። ወይም ቦይፍሬንዷ መጥቶባት ሻይ ቡና ልትለው ከወጣች ሁለት ሰዓት ሙሉ ቁጭ ብለህ ትጠብቃታለህ። እዚህ ስዊድን ግን ቢሮህ ወይም ቤትህ ሆነህ አምስት ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኢንተርኔት ትከፍለዋለህ። የምታስፈርመውና ደጅ የምትጠናው ባለሥልጣን፣ ተጎልተህ የምትጠብቃት ገንዘብ ተቀባይ፣ … የሉም። መስሪያ ቤቱ ድረስ ከሄድክ እጅህን ስመው፣ አመስግነው ያሰናብቱሃል።

አንዳንድ ሠራተኛ ልብ ብለሃል? በደሙ ተዋህዶበት ሥራውን የሚሠራው አለቃውን ሲያይ ብቻ ነው። ”አለቃ” ተብዬዎችንስ ልብ ብለሃል? ከእነሱ በታች ያሉት በሙሉ እንዲፈሩዋቸው ከባዶ ሜዳ ተነስተው በሆነ ባልሆነው ይጮሃሉ፣ ይቆጣሉ፣ ደምወዝ ይቆርጣሉ፣ …። እናም ሠራተኞች በሙሉ ይፈሩዋቸዋል። ”መጣ” ከተባለ ሠራተኞቻቸው ድመት ያየች አይጥ ይሆናሉ። እዚህ ስዊድን አለቃህ ሲመጣ ”እንደምን ዋልክ?!” ለማለት አታሸረግድም። እጅ አትነሳም። ልክ እንደማንም ሰው ”ሄይ!” ወይም ”እንደምን አደርክ?!” ትለዋለህ። ከደበረህም ዘግተኸው ታልፋለህ። ልቆጣህ፣ ልፍለጥህ፣ አሸርግድልኝ፣ እኔ ስገባ ከመቀመጫህ ለምን አትነሳም?፣ … ብሎ ነገር የለም።

ጌታው! እዚህ ስዊድን አለቃህ ቀጣሪህ፣ አሠሪህ፣ ከበላይህ ያለው፣ … ሰው አይደለም። ትክክለኛ አለቃህ ሕሊናህ ነው። ሥራህን በአግባቡና በሰዓቱ መሥራት አለብህ። አንተም ካለምንም ግዴታ ትሠራዋለህ። መሥራት ካልቻልክ አለቃህ ሳይሆን አጠገብህ ያሉት የሥራ ጓዶችህ ”ይባረር!” ብለው የመወሰን ሥልጣን አላቸው። ”ይባረር!” ሲሉ ግን ስለደበርካቸው አይደለም፤ በአግባቡ ስለማትሠራ ወይም የሥራ ብቃትህ ዝቅተኛ ስለሆነ እንጂ።

”የሻይ ሰዓት” ተብሎ እኛ አገር ካለሥራ የሚባክነውን ሰዓት ታውቀዋለህ። እዚህ እንዲያ ብሎ ነገር የለም። የሻይ ሰዓትህን የምትወስነው አንተ እንጂ አለቃህ ወይም መስሪያ ቤቱ አይደለም። ”የሻይ ሰዓቴ ነው” ብለህ የምትወስናት በየአንድ አንድ ሰዓቱ ከ፭ (5) ደቂቃ አትበልጥም። ከፈለግህ ልታጠራቅማት ትችላለህ። በሻይ ሰዓትህ ካለሥራ ሻይህን ወይም ቡናህን መጠጣትና ሲጋራህን ማጨስ መብትህ ነው። ከፈለግህም እንደሥራህ አይነት እየሠራህም መጠጣት ትችላለህ። ጥምባሆም የምታጤስ ከሆንክ ከቢሮው ወጣ ብለህ ለማጨስ የተፈቀደበት ቦታ ሄደህ ታጨሳለህ። በሻይ ሰዓትህ ቁጭ ብለህ አለቃህ መጣ አልመጣ፣ ባለጉዳይ መጣ አልመጣ አትሸማቀቅም። የሻይ ሰዓትህ የተከበረች ነች - አንተ ሥራህን እንዳከበርክ ሁሉ።

ቅድም እንዳልኩህ የተመደብክበትን የሥራ ኃላፊነት በብቃት የማትወጣ ከሆነ እዚያ ቦታ እንዳትሠራ ትደረጋለህ። አቅምህና ችሎታህ ታይቶ ሌላ ሥራ ይሰጥሃል። ላንተ የሚሆን የሥራ ድርሻ ወይም ሥራ ከሌለ (የሥራ ችሎታና ዕውቀት ከሌለህ፣ ለተሰጠህ ኃላፊነት የማትመጥንና ብቁ ካልሆንክ) ትባረራለህ። ከተሰጠህ የሥራ ኃላፊነት በላይ ዕውቀትና ችሎታ ካለህና ላንተ የሚመጥን ከፍ ያለ የሥራ ኃላፊነት ካለና ክፍት ከሆነ ይሰጥሃል። እየሠራህ ባለኸው ሙያ ላቅ ያለ ትምህርት እንድትማር መስሪያ ቤትህ ወጪህን ሸፍኖ ያስተምርሃል። ከደምወዝህ በላይ እየተከፈለህ ትማራለህ። ካንተ ሥራ ጋር የተያያዘ አዲስ ቴክኖሎጂ ወይም አዲስ የአሠራር ዘዴ ከተገኘ ለተወሰኑ ቀናት ወይም ሣምንታት ሥራህን አቁመህም ይሁን እየሠራህ ትማራለህ። ከደምወዝህ ሌላ ስለተማርክ ይከፈልሃል። ይህ ሁሉ የሚደረገው በመንግሥትም በግልም መስሪያ ቤቶች አካባቢ ነው።

ለምሣሌ እዚህ ከመጣሁ ቅርጫት ኳስ አብሮኝ የሚጫወት ቡና ቤት ውስጥ የሚሠራ ልጅ ያጫወተኝን ልንገርህ። የ’ባር ቴንደር’ነት (መጠጥ ቤት ውስጥ መጠጥ የሚቀምመው ወይም የሚደባልቀው ሰው) ሙያ ለስድስት ሣምንት መማር ጀምሯል። ትምህርቱን የሚያስተምረው የቡና ቤቱ ባለቤት ነው።

ጌታው! እዚህ አንዳንድ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ደግሞ ሁሉም ሠራተኛ በትብብር ሲሠራ ታያለህ። ከተሰጠህ የሥራ ድርሻ ባሻገር ሌላውንም የሥራ ጓድህን እየረዳህ ትሠራለህ። ግዴታ የለብህም። ግን በቃ ትረዳዋለህ። እሱም ይረዳሃል።

ጌትዬ! እዚህ አገር ሁሉም የሥራ ኃላፊነቱን በሚገባ ይወጣል። የሥራ ኃላፊነቱን በአግባቡና በሰዓቱ የሚወጣው የሥራ ድርሻውን በትክክል ስለሚያውቅ ነው። ከዚህም ሌላ ለተመደበበት የሥራ ኃላፊነትና ድርሻ የሚመጥን ዕውቀትና ችሎታ ያለው ስለሆነ ነው። የማይመጥን ከሆነ ወይ ዝቅ ብሎ እንዲሠራ ይደረጋል፤ አልያ ይባረራል። የጉልበትም ሥራ ቢሆን እንኳ። እንደኛ አገር ስለመዝገብ አያያዝ ምንም ያልተማረ ወይም የማይችል ወይም ስሙን በትክክል መፃፍ የማይችል ግለሰብ መዝገብ ቤት አይመደብም። ከታች እስከላይ ሁሉም ቦታ ብትሄድ ችሎታ፣ አቅም፣ ዕውቀት፣ የሥራ ልምድ ያለው ሰው ነው በእያንዳንዱ አይነት የሥራ መስክ ላይ የሚመደበው።

ስድስት ወር ሠርተህ ከመንግሥት መስሪያ ቤት ወይም ከ”እንትና ሻይ ቤት” ብትባረር ወይም ብትቀነስ፤ ሌላ ሥራ እስክታገኝ ስትሠራ ይከፈልህ ከነበረው ደምወዝ ጋር የሚመጣጠን ገንዘብ በወር ይከፈልሃል። የሚከፍልህ ከኢንሹራንስ ወይም ከሕዝብ የተሰበሰበ ቀረጥ ነው። ሕሊና ከሌለህና ማሰቢያህ የማይሰራ ከሆነ ስድስት ወር አንዱ ጋር በሃሪፍ ደምወዝ ተቀጥረህ ሠርተህ ብትባረር ”ሥራ አላገኘሁም” በሚል የፈለገህን ጊዜ ተቀምጠህ 'ልትጦር' ትችላለህ። እኛ አገር እንዲህ ቢሆን ስንቱ ነው ቁጭ ብሎ የሚበላው? እዚህ ግን ይህን ስታደርግ ሕሊና የሌለህ መሆን አለብህ። ታመህ ከሥራ ብትቀር የደምወዝህ ሰማንያ በመቶ ይከፈልሃል። የሚገርምህ ነገር ታመው ከሥራ ስለቀሩ ይበሳጫሉ። የግድ ሥራ መሥራት ይፈልጋሉ። ከሥራ ቢቀሩ እንኳ ቤታቸው ውስጥ የሚሠሩት ሥራ ፈልገው ራሳቸውን በሥራ ይወጥራሉ። እናም የፈለገ ቢሆን በተለይ ስዊድናውያን የሆኑቱ ቁጭ ብለው የሕዝብ ገንዘብ መብላት አይፈልጉም።

ስዊድናውያን ያልሆኑት ስደተኞችና መጤዎች እዚህ አገር ሲቆዩ ብዙዎቹ ይለወጣሉ። እናም መጤውም ቢሆን እንደነሱው የሥራ ፍቅር ያድርበትና ሲፈጋ ይኖራል። እዚህ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያንም በሥራ አይታሙም፤ ወገባቸው እስኪጎብጥ ድረስ ነው የሚሠሩት።

አብዛኛውን ስዊድናዊ ከቤተሰቡና ከሥራው ማንን እንደሚያፈቅር ብትጠይቀው ”ቤተሰቤን” ብሎ ይመልስልኛል ብለህ ከሆነ ተሳስተሃል። ከቤተሰቡ ይልቅ የሚያፈቅረው ሥራውን ነው።

ጌታው! ሥራን በተመለከተ ከእኛ ጋር ልታወዳድራቸው ከቶውኑም አትችልም። እጅግ በጣም ጥለውን ሄደዋል። የዚህ ምክንያቱ ቴክኖሎጂው አይደለም። ቴክኖሎጂው ራሱ የመጣው በሥራ ነው። የራሳቸው ቴክኖሎጂ ባይሆን እንኳ ሠርተው ባገኙት ገንዘብ ቴክኖሎጂውን ይገዙታል። የኅብረተሰቡ የሥራ ፍቅር፣ የተዘረጋው የሥራ ስርዓት፣ የአገሪቱ የአስተዳደር ዓየር ንብረት (አትሞስፌር)፣ ኅብረተሰቡና መንግሥት እጅና ጓንት ሆነው ለአገሪቷና ለህዝቡ ዕድገት መሰለፋቸው - መመካከራቸው - መማማራቸው - መወቃቀሳቸው - መደማመጣቸው - መከራከራቸው - …፣ መንግሥትም - የፖለቲካ ፓርቲዎችም - ግለሰብም - ድርጅቶችም - ተቋማትም - … የሥራ ድርሻቸውንና ኃላፊነታቸውን በሚገባ አውቀውና ተከፋፍለው ሁሉም የየራሳቸውን ኃላፊነት በአግባቡና በሰዓቱ መወጣታቸውን ስታይ ያስቀናሉ። በእውነት ነው የምልህ በቅናት እየነደድሁ ነው።

ወንድሜ ሆይ! እስቲ እባክህ እናስብበት! አገራችን ትንሽ እንኳ ካለችበት ፈቀቅ እንድትል ከዛሬ ጀምሮ እንደስዊድሾቹ ለሥራ ፍቅር ይደርብን! ከዛሬ ጀምሮ እኔና አንተ የተሰጠንን የሥራ ኃላፊነት በሚገባ እንወጣ! የራሳችንን ካስተካከልን በኋላ ደግሞ አጠገባችን ያሉት እንዲስተካከሉ እንጣር። ስንፍናችንን በሰበብ አንሸፋፍነው። ሳንደባበቅ፣ ሳንፎጋገር፣ ሳንደላለል፣ … እውነት እውነቷን እየተወያየን፣ እየተማማርን፣ እየተመካከርን፣ እየተወቃቀስን፣ እየተደማመጥን፣ … የሥራ ፍቅር እንዲያድርብን እንትጋ!

ጌትዬ! መቼም ፅሁፌን አንብበህ ከጨረስከው ሳላመሰግንህ አላልፍምና፤ አ - መ - ሰ - ግ - ና - ለ - ሁ! (’ታክ!’ - በስዊድንኛ)

ውድ ወንድሜ! በስዊድንኛ ’ቻዎ!’ ብልህ ምን ይመስልሃል? - ”ሄዶ!”

ወደ ስደት ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

 

 

Hosted by www.Geocities.ws

1