ወደ ስደት ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

ከ፦ስደተኛው - ፩

እህልና እኛ

ያሬድ ክንፈ - ከስዊድን (የንጋት ዋና አዘጋጅ)

***************************************************

እንደምን አለህማ ወዳጄ ሆይ? አዲስ መዲናችን እንዴት ነች? እንደአዲስ ሊሠሯት ሩጫ ላይ መሆናቸውን ሰማሁ። እንዳንተው ወሬኛም አይደለሁ?! ወሬ አያመልጠኝም ማለት ትችላለህ - ዕድሜ ለኢንተርኔት! ከነፃው ፕሬስ፣ ከኢህአዴግ ሚዲያዎች፣ በውጭ አገር ከሚገኙ የኢትዮጵያውያን ሚዲያዎች፣ ከውጭ ሚዲያዎች፣ … ከተገኘው ሁሉ ወሬ እለቃቅማለሁ። ሁሉንም ከኢንተርኔት ነው የማገኘው። ቢቢሲ ቴሌቭዥንንም አልፎ አልፎ ለዓለም ወሬ እከታተላለሁ። ሠላምታዬን ሳልጨርስ ወሬዬ ላይ ተዘረፈጥኩማ። ኧረ! ወዳጆቻችንና ጓዶቻችን እንዴት ናቸው ባክህ? አዲስ አበባ ሬስቶራንት፣ ጊዮርጊስ፣ ካዛንችስ፣ ዑራዔል፣ ፒኮክ ጀርባ፣ ኦሎምፒያ፣ ፍላሚንጎ፣ ቦሌ - ብርሐንና 땨ላም - አርቲክራፍት - ... ማተሚያ ቤቶች፣ አራት ኪሎ፣ … ያሉቱን ለአንዳቸውም ሳታዳላ የከበረ ሠላምታዬን አድርስልኝ - እባክህ!

ጌታው! ሥራ እንዴት ነው? የቢሮህ ሰዎችስ ሠላም ናቸው? አንተ ቢሮ እየመጣሁ የምጠጣው ቡና እንዴት ናፍቆኛል መሰለህ! እዚህ ከመጣሁ አፌን ሞልቼ ”ቡና ጠጣሁ!” ያልኩበት ቀን የለም። ጎረቤትህ የእሙዬ እናት የሚያፈሉት ቡና ሦስተኛው እዚህ ስዊድን ካሉት ካፌዎች አንዱ ጋር ገብተህ በ፲፰ (18) ክሮነር ገዝተህ ከምትጠጣው ይሻላል። (አንድ የስዊድን ክሮነር ከኢትዮጵያው አንድ ብር ጋር ተቀራራቢ ነው)። እዚህ ያለውን ኑሮ ከኢትዮጵያ ጋር ካወዳደርከው ቢያንስ ከኢትዮጵያ በስምንት እጥፍ ይወደዳል። አማካኙን ከወሰድከው በአስር እጥፍ ማለት ትችላለህ። አብዛኛው ነገር ከኢትዮጵያ ይወደዳል። ከኢትዮጵያ የሚቀንስም፣ እኩል የሆነም ነገር አለ፤ ግን ብዙ አይደለም። የኑሮው ውድነት የሚካካሰው በሰዉ ገቢ ነው። ገቢው የዚያኑ ያህል ዳጎስ ያለና ከኢትዮጵያ ጋር ስታወዳድረው በትንሹ ፲፭ (15) እጥፍ ይበልጣል። ከ፳፭ (25) እጥፍ የሚበልጥበት ጊዜም አለ። ሥራ-አጥ ስዊድናዊ ወይም ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ካለህ መንግሥት እየደጎመህ ትኖራለህ። በስዊድንኛ ”ቢድራግ” ይባላል። እንዲያም ሆኖ ሰዉ የሥራ ፍቅሩን ልነግርህ አልችልም። ቁጭ ብሎ ቢድራግ እየበላ የሚኖር ከስንት አንድ ነው። ይህ ገንዘብ (ቢድራጉ) የሚመጣው ከህዝብ ላይ ከሚቆረጥ ቀረጥ ነው። ብዙ ከሠራህና ደምወዝህ ከፍ ካለ፤ የምትከፍለው ግብር (ቀረጥ) የዚያኑ ያህል ይጨምራል።

ሥራ ምን ማለት እንደሆነ አገር ቤት እንደማናውቅ ያወቅሁት እዚህ ከመጣሁ ነው። ሰዉ እንደጉድ ነው የሚሠራው። በሥራ የተጨበጨበለት፣ የሠራተኛ ባንዲራ ያዥ ህዝብ ነው። የኛን አገር ሰው እዚህ ብታየው ትደነቃለህ። አገር ቤት (ኢትዮጵያ) እያለ የገዛ ቡታንቲውን የማያጥበው ሁሉ እዚህ በሥራ እንደአያቶቻችን እንዝርት ሲሾር ስታየው ይገርምሃል። አገር ቤት እያለ ከውጭ እህቱ/ወንድሙ/እናቱ/አባቱ በምትልክለት/በሚልክለት ገንዘብ እየኖረ ፓንክ አበጥሮ፣ ሌዘር ጃኬት ደርቦ፣ ትልቅ ጫማ ተጫምቶ፣ ክንፏን እንደተመታች አሞራ እጆቹን ዘርግቶ መንገድ ዘግቶ ገፍትሮህ የሚያልፍ፤ እዚህ ሲመጣ ወገቡ እስኪንቀጠቀጥ ይፈጋል። ከልቡ ሥራ ይሠራል። ወንድምህ ቢሆን እንኳ ሊያጫውትህ ወይም ጊዜውን ሊሰጥህ አይችልም - ጊዜ የለውማ - ሥራ ይበዛበታላ። እዚህ የመጣሁ ሰሞን ያገኘኋቸውን ኢትዮጵያውያን በድጋሚ ሳላገኛቸው ፬ ወር ያለፈኝ አሉ። ምክንያቱም ጊዜ የላቸውም።

ጌታው! ስለስደቴ የምነግርህ በዝቶብኛል። በጊዜ ባቃልለው የተሻለ ነው። እስኪሰለችህ እፅፍልሃለሁ። የምፅፍልህ ከተሰደድህ እንድትዘጋጅ፤ ካልተሰደድህም ስደት ምን እንደምትመስል በትንሹም ቢሆን ግንዛቤ እንዲኖርህ ይረዳሃል ብዬ ነው። ከአገርህ ስትወጣ ሁሉም ነገር አንድ አይደለም። ቋንቋው፣ ባህሉ፣ የኅብረተሰቡ አስተሳሰብ፣ ቴክኖሎጂው፣ ትራንስፖርቱ፣ ሕጉ፣ ኃይማኖቱ፣ ወጉ፣ አየር ንብረቱ፣ አለባበሱ፣ አመጋገቡና ምግቡ፣ የኅብረተሰቡ ፍላጎት፣ ሥራው፣ ፖለቲካው፣ የገዛ አገርህ ሰው፣ … ምን አለፋህ ሁሉም ነገር ከአገርህ ጋር አይመሳሰልም። ትንሽ ስትቆይ አካሄድህ ሁሉ ይቀየራል። ለመኖር - የማትፈልገውን ልታደርግ ትገደዳለህ። የማትፈልገውን አይነት አለባበስ ልትለብስ፣ የማትፈልገውን አይነት ሥራ ልትሠራ፣ የማትፈልገውን ምግብ ልትመገብ፣ … ትገደዳለህ። መኖር አለብሃ! አልያ ...

ጌታው! ከምግብ ምን እንዳማረኝ ታውቃለህ? የበቄ ቤትና የሠላም ልኳንዳ ጥሬ ሥጋና ጥብስ - በጉደር። እባክህ በራስህ ኪሣራም ቢሆን ከወዳጆቻችን ጋር ሰብሰብ ብላችሁ በእኔ ስም ብሉልኝ። እዚህ ስለአገርህ ምግብ ጠይቀውህ (ስዊድኖቹ፣ ፈረንጆቹ ወይም ስደተኞቹ) ”ጥሬ ሥጋ” ብለህ ብትላቸው ይሸሹሃል። የሚሸሹህ ”እንስሳ ነውና! የኔንም ሥጋ ቢያገኝ አይምረኝም” ብለው በማሰብ ነው። አፍ አውጥተው ባይነግሩህም ከደፈሩና ከተቀራረቡህ ”እንዴት ያልበሰለ ሥጋ ይበላል?” ይሉሃል። … ስላልቀመሱት ነው’ይ! ቢቀምሱት ምን ሊሉ ነው? በሌላ በኩል ደግሞ እነሱ ክርስቲያን ሆነው የአሣማ ሥጋ ሲበሉ ”እንዴ! እንዴት የአሣማ ሥጋ ትበላላችሁ? … በመጽሐፍ ቅዱስ የተከለከለ ነው” ስትላቸው፤ ”ሙስሊሞች ናቸው የማይበሉት። በመጽሐፍ ቅዱስ አልተከለከለም” ይሉሃል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳን ’ኦሪት ዘሌዋውያን፣ ምዕራፍ ፲፩’ን (11'ን) ገለጥ አድርገህ ስታነብላቸው ”ኧረ! …” ይላሉ በመገረም፤ መብላታቸውን ግን አይተዉም። እንዲያውም አሪፍ ምግብ እንደሆነ ይነግሩሃል። በስዊድንኛው መጽሐፍ ቅዱስ ላይም በዚሁ ምዕራፍ ላይ ተጽፏል። እነሱ ግን ከነጭራሹ መጻፉን እንኳ አያውቁም።

የምግብ አይነቱ አበዛዙን ልነግርህ አልችልም። ሁሉም ነገር ፋብሪካ ውስጥ ገብቶ አምሮበት በተለያየ መልክ የወጣ ባይሆንም ቢያንስ ይታሸጋል። አንድ ግብዳ ድቡልቡል ቢጫ ቃሪያ ለብቻዋ በላስቲክ ግጥም ተደርጋ በቅርጿ ታሽጋ ሱፐር ማርኬት ውስጥ ታገኛታለህ። አገር ቤት ቃሪያ ሲበላሽ ያለውን አይነት ቢጫነት ሳይሆን፤ ትክክለኛውን ሙሉ ቢጫ የሆነና የኢትፍሩትን ተለቅ ያለ ብርቱካን የሚያህል ቃሪያ ነው የምልህ። ቀይም፣ አረንጓዴም የሷ አይነት ቃሪያዎች አሉልህ። "ፓፕሪካ" ይባላል። ሠላጣ ሲያሳምሩ ልነግርህ አልችልም። ቃሪያ መሆናቸው ስለተነገረኝ እንጂ አይቻቸውም ቀምሼአቸውም ”ቃሪያ ናቸው” ብዬ ማለት አልችልም ነበር። አገር ቤት ያለው የፈረንጅ ቃሪያ በስንት ጣዕሙ! ይሄኛው ከውሃም በላይ ነው፤ አያቃጥል - ምን አይል። በቃ! የሥራ ድርሻውና ተፈላጊነቱ ለጌጥ ነው! ምግብ ሲቀርብ ውበቱ ከፍ እንዲል፤ ”ብሉኝ! ብሉኝ!” እንዲል - አፒታይት ለመክፈት። አለቀ ይኸው ነው የሱ ድርሻ - ለኢትዮጵያውያን። ለፈረንጆቹ ግን ተጨማሪ ግልጋሎት አለው፤ ለእነሱ ቃሪያም ጭምር ነው። ለእነሱ ከልቡ ቃሪያ ነው። የኛን ቃሪያ በምላሳቸው ብታስነካቸው ”ሊገድለኝ ሞከረ” ብለው ሊከሱህ ይችላሉ። ቁርስ ወይም መክሰስ ላይ ዳቦህን በቅቤ ቀብተህ ስታበቃ በቀጫጭኑ የተቆራረጠ ፓፕሪካ እላዩ ላይ ጣል ጣል አድርገህበት ትበላዋለህ። ቀልዴን እንዳይመስልህ - ከምሬ ነው። ... የምግብ ፍላጎትህን ከፈትሁልህ ወይስ ጠረቀምሁልህ? ...

ጌታው! ሽንኩርትን እርሻ ላይ አይተኸዋል አይደል? የሽንኩርቱ ራስ መሬት ውስጥ ነው። ከላይ ደግሞ ውስጡ ባዶ (ቀዳዳ) የሆነ ረዘም ያለ ሣር መሳይ ቅጠል ቢጤ አለው አይደል! እኔ የማውቀው የሽንኩርቱ ራስ ገበያ ሲወጣ እንጂ ቅጠሉን አይቸው አላውቅም። እዚህ ታዲያ ቅጠሏም ገበያ ላይ ወጥታ ትሰጣለች። ተገዝታ ቤት ትወሰድና ደቅቃ ትከተፍና በሣህን ትቀርባለች። ከዚያ ልትበላው እሣህን ላይ ያወጠኸው ምግብ ላይ ባናቱ ትነሰንሳታለህ። እንዴት ምግቡን እንደምታጣፍጥ ልነግርህ አልችልም። በስሱ ሽንኩርት ሽንኩርት ትላለች። ከሱጎ ጋርም ትዋሃዳለች።

”ቅመማ-ቅመም” ሲባል ሁሌም ትዝ የሚለኝ የሻይ ቅመም ነው። ከበዛ የቅቤ ማንጠሪያ። ወንድሜ ሆይ! እዚህ ያለውን አይነትና ብዛት ልነግርህ አልችልም። የምናውቃቸውና አገር ቤት ያሉቱ (ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸውና የውጭ ምንዛሪ የምታገኝባቸው) እፋብሪካ ገብተው በሚገባ ተቀምመው፣ ታሽገው፣ ስማቸው - ለምን ለምን እንደምትጠቀምባቸው - ከምን ከምን እንደተቀመሙ - የንግድ ምልክታቸው - የፋብሪካው አድራሻ - … ተለጥፎባቸው እገበያ ይወጣሉ። ዋጋቸው ቀላል እንዳይመስልህ። ውድነታቸውን የምትረሳው እምግብ ላይ ነስነስ አድርገህ ስታጣጥማቸው ነው። የምታውቀው ፓስታና መኮረኒ ላይ የፓስታ ቅመም ነስነስ አድርገህ ስትበላው እጅ ያስቆረጥማል።

ኡዞ - ኡዞ የሚሸተውን ተክል ታውቀዋለህ? የሱ ቅጠል ደርቆ - ተወቅጦ - ታሽጎ እገበያ ይቀርባል። ሃሪፍ ሻይ ነው! - ቅመሰው! የፈለግኸው አይነት የፍራፍሬ ሻይ አለ። የባህር ዛፍ ሻይ ሁሉ አለ። እኔን የገረመኝ ደግሞ የአበባ ሻይ ነው። አንተ መስሪያ ቤት ካፌ ገብተህ ”አንድ የሬሣ አበባ ሻይ አምጭልኝ” ብለህ አስተናጋጅዋን ስትላት ይታይህ። ጉመሮ - ውሽ ውሽ - አንበሣ - … ብለን ከማማረጥ (አልሸሹም ዞር) አልተላቀቅንም። መላቀቅ መቻላችንንም እንጃ!

ጌታው! በቆሎ ተጠብሶ - ተቀቅሎ - ተፈልፍሎ ተቆልቶ - ፖፕኮርን - አልያም ለጠላ መሆኑን ነበር የማውቀው። እዚህ አንድ ቀን የሆንኩትን ልንገርህማ። ጣፋጭዋ - ቢጫዋና ባለትንንሽ ፍሬዋን በቆሎ ታውቃታለህ አይደል? እስዋ ተቀቅላ ከነቆረቆንዳዋ ቀረበችልኝ። እኔ ወንድምህ አንስቼ ልግጣት እጄን ስሰነዝር፤ ገበታ አብሬአቸው የቀረብኳቸው ሰዎች የሆነች የፕላስቲክ ብሎን አንስተው በሁለቱም የበቆሏቸው ቆሮቆንዳ ጫፎች ላይ ማስገባት (ማሰር) ጀመሩ። እኔም እንደሌላው ጊዜዬ ሰረቅ አድርጌ አየኋቸውና ብሎኖቹን እበቆሎዬ ላይ እየጠመዘዝሁ አሰርኳቸው። ብሎኖቹ እስከመጨረሻ ገብተው ሲያልቁ የአውራ ጣቴን አንድ አንጓ የሚያህል ትርፈት አላቸው። ለካስ ጥቅሙ በቆሎው እንዳያቃጥልህ መያዣ መሆኑ ነው። አሁንም እንደለመድኩት ሰረቅ አድርጌ ስመለከት ሰዎቹ በቆሎአቸውን የገበታ ቅቤ ይቀቡታል። ቅቤው በቆሎው ላይ ሲያርፍ እየቀለጠ ይጠፋል። በእያንዳንዳቸው የበቆሎ ፍሬዎች ክፍተትና መገጣጠሚያ ውስጥ ይገባል። እኔ ኩረጃዬን በተግባር አዋልኩ። ቀጠሉና ባለቅመም ጨው (ከላይ የነገርሁህን የቅመም ታሪክ አስታውስ) ነሰነሱበት። ’ማ ከማ ያንሳል!?’ አልኩና - እኔም ነስነስ። እነሱ መብላት ሲጀምሩ እኔ ዓይኔን ጨፍግጌ በቆሊትን ገመጥ አድርጌ አጣጣምኳት - አይ መጣፈጧ! ልነግርህ አልችልም። የተቀቀለ በቆሎ - በቅቤ፣ በጨውና በቅመም። ወንድሜ ሆይ! እባክህ ሠርተህ ቅመሰው! ብታጣ ብታጣ ባለቅመሙን ጨው ነው፣ በሱ ፈንታ ጨው ብቻ ተጠቀም።

የጣፋጭዋ በቆሎ ታሪክ በዚህ አያበቃም። ተፈልፍላ ተቀቅላ በቆርቆሮ ታሽጋ ገበያ ትወጣለች። ሠላጣ ላይ ደባልቀህ ስትበላት መጣፈጧን ልነግርህ አልችልም። የፓስታና የመኮረኒ ሱጐ ስትሠራም ትደባልቃታለህ - እሳት ግን አታስነካትም። ፒሳ መሥሪያም ትሆናለች። ዳቦህን ቅቤ ቀብተህ እላዩ ላይ በተን ታደርጋታለህ። ከፈለገህ ነገር ጋር ልትበላት ትችላለህ - በቆልዬን። እንጭጭ - ገና ማሸት የጀመረ ወይም ምንም ፍሬ ያልያዘ የበቆሎ ቆሮቆንዳ አገር ቤት አይቆረጥም አይደል! እምልህ ልጆች እያለን ለጨዋታ ብለን ስንቆርጠው ወላጆቻችን በኩርኩም የሚያጦዙን ትዝ ይልሃል? እንደሱ አይነቷ በቆሎ ተመርጣ ታሽጋ ገበያ ትወጣለች። እሷም ከሠላጣ፣ ከፓስታ፣ ከመኮረኒ፣ ከሩዝ፣ … ጋር ትበላለች - ቆረቆንዲቷ። ”በቆሊት ነፍሷ! ክብር የሌላት እኛ አገር ነው!” ብዬ ስል ተቃዋሚ ከሆንክ ምርጫ ቦርድ ጋሽ አሴ ጋር ሄደህ ተመዝገብ። በነገራችን ላይ ተፈልፍላ የታሸገችዋ በቆሊት አዲስ አበባ ሱፐር ማርኬቶች ውስጥ አለችና ቅመሳት።

ጌታው! እኛ ይበላል ብለን የማናስበው ነገር ሁሉ እዚህ ይበላል። የምናውቃቸው ለምግብ የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎች በተለያየ መልክና አይነት ተከትፈው - ተበጫጭቀው - ተጠብሰው - ተቀቅለው - ጥሬአቸውን (ሥጋን አይጨምርም) - ለብ ለብ ተደርገው - ተከሽነው - ተዋህደው - ተሠርተው - … ይበላሉ። <

ሱፐር ማርኬት ሄደህ የወርህን ወይ የሣምንትህን ትሸምትና ፍሪጅህን፣ ዲፕፍሪዘርህንና የወጥ ቤት ቁምሣጥንህን ትሞላለህ። ዲፕፍሪዘር የሚባለው የበረዶ መሥሪያው አይነት ነው። እዚህ ካለእሱ መኖር አትችልም። ቤት ስትከራይ ፍሪጁንም፣ ዲፕፍሪዘሩንም፣ ስቶቩንም፣ ዕቃ መደርደሪያውንም፣ የልብስና የዕቃ ቁምሣጥኑንም፣ … መግዛት አያስፈልግህም፤ የምትከራየው ቤት እነኝህን ሁሉ ያሟላ ነው። ትልቁን ፍሪጅ የሚያህል ዲፕፍሪዘር ሁሉ አለልህ። ተሠርተው ያለቁ ምግቦችን፣ ዶሮን፣ ሥጋን፣ ዳቦን፣ … እዚያ ውስጥ ትከታለህ። ዳቦ በፌስታል ተጠቅልሎ በረዶ ቤት ውስጥ (ዲፕፍሪዘር) ይገባል። እዚህ ከመጣሁ ይኸው ወደ አምስት ወሬ ነው ትኩስ ዳቦ የበላሁት አንድ ቀን ነው። ዳቦ መጋገሪያ ያላቸው ሱፐር ማርኬቶች ውስጥ ካልሆነ ትኩሱን አታገኝም። እሱንም በአጋጣሚ ነው። እንዳገር ቤት እንጀራ በወጥ ካማረህ ሠርተህ ትበላለህ። እንጀራው የጤፍ ሳይሆን የስንዴ ዱቄት ነው። እኔ ስም አውጥቼለታለሁ - ”ላስቲኩ” ብዬ። ልትቆርሰው ስትል እንደላስቲክ ይሳባል። ሥጋ ወጥ ሁሉ መሥራት ትችላለህ። ጮማ አምሮህ አምሮህ ይወጣልሃል እንጂ አታገኝም፤ ባጋጣሚ ካልሆነ በቀር። እነሱ ጮማ አይበሉም - ”ያወፍራል” ይላሉ።

ጌታው! እዚህ እንዳገርህ የምግብ አበላል ካሰብክ ዋጋ የለህም። ላስቲኩን እንጀራ በመጥበሻ እየጋገርክ ካገርህ ያመጣኸው ወይ የተላከልህ ቅቤና በርበሬ እስኪያልቅ ልትበላ ትችላለህ። እሱን ስትጨርስ ”ባልበላ ይቀራታል እንጂ ይሄን የፈረንጅ ምናምን አልበላም” የማለት ዴሞክራጢያዊ መብት አለህ። ችጋርና ጠኔ አዙሮ ሲጥልህ ሱፐር ማርኬት ገብተህ የድመትና የውሻ ምግብ ገዝተህ ልትበላም ትችላለህ - ቋንቋውን ካላወቅህና የሚረዳህ ከሌለ። ከኤቢሲዲ ያልዘለለችዋን የኛን አገርዋን የትምህርት ቤት እንግሊዝኛ አወቅሃት አላወቅሃት ጥቅምዋ ከዜሮ በታች ነው። እንደሰማሁት እዚህ አገር ካሉ ኢትዮጵያውያን ውስጥ አንዲት ሴት ብቻ ነች ”አሉ” ሁሌም እንጀራ በወጥ የምትመገብ። ያለህ አማራጭ በተቻለህ መጠን ወኔህን ሰብሰብ አድርገህ ምግብን መድፈር ነው። እናትህ ወይ አባትህ ”ልጄ! የገባ ያገለግላል!” አላሉህም - እንጀራ አልበላ ስትላቸው? እውነታቸውን ነው! ካልሆነም የተፈጨ ጤፍ እናትህ እንዲልኩልህ እያደረግህ የጤፍ እንጀራ እየበላህ መኖር ትችላለህ። ግን እስከመቼ? እንደምታውቀው እኔ እንዳንተ ስላይደለሁ ባይሆን ቀምሼ ካጣጣምሁ በኋላ ያልተስማማኝንና ያልጣመኝን እተወዋለሁ። የተስማማኝንና የጣመኝን ግን አልምረውም።

ሱፐር ማርኬቶች ብዙ ጊዜ አዲስ አይነት የምግብ አሠራር ’ሪሴፕት’ በወረቀት አትመው በነፃ ያድሉሃል። ብዙ ጊዜ ይህን የሚያደርጉት አዲስ ያስገቡት የምግብ መሥሪያ ጥሬ ዕቃ ሲኖር ነው። ያላቸው እንዲሸጥላቸውም እንደማስታወቂያ ይገለገሉበታል። ኢንተርኔት ላይ ወጥተህ የምትፈልገውን ወይም በልተኸው የማታውቀውን የምግብ አሠራር ሪሴፕት ማግኘት ትችላለህ። እጅግ በርካታ መጻሕፍትም አሉልህ። ማርቆስ ሣሙኤልሰን የሚባል በዘር ኢትዮጵያዊ በዜግነት ስዊድናዊ የሆነ ግለሰብ በስዊድንኛ ቋንቋ የምግብ አሠራር መጽሐፍ  ጽፏል። የመጽሐፉ ርዕስ በቀጥታ ወደ አማርኛ ሲተረጎም "አንድ የቅምሻ ጉዞ" የሚል ትርጓሜ ሲኖረው፣ ባለመቶ ዘጠና ገጾች ነው። ለኢትዮጵያ የባህል ምግብ አሠራር አስራ ስድስት ገጾች ሰጥቶአል። ከፈለግህም ቲቪ ከፍተህ የምግብ አሠራር ትከታተላለህ። ቋንቋውን ካልቻልክና ያቺን የኛን አገርዋን እንግዚዝኛ ከቻልክም በእንግዚዝኛ የሚተላለፉትን የምግብ አሠራር ፕሮግራሞች ትከታተላለህ።

’ኢቲቪ’ እሁድ እሁድ የሚያሳያትን አትናቃት። ለውጥ ፈላጊ ከሆንክ እሷ ከምታስባት በላይ ጠቃሚ ናት። የግድ የሼራተኑ አይነት ወጥ ቤት ሊኖርህ አይገባም። ያቺ በ፶፭ (55) ብር የገዛናት የቻይና ማንደጃን፣ እነኛን ሁለቱን ድስቶችህን፣ አንዱን መጥበሻህን፣ ያንን አያትህ ያወረሱህን የዋንዛ እንጨት መክተፊያህን፣ እጀተ እንጨት ቢላዋህን፣ … የሚጎልህ ካለ ከቤት አከራይህ ተውሰህ በዚህ ሣምንት እሁድ ኢቲቪ የሚያሳየውን ምግብ ለምሣህ ሠርተህ ብላ። ከተፈጠርን ጀምሮ ሦስት አይነት ምግብ ብቻ እየበላን ሞታችንን ስናቀርብ ኖረናል። ስዊድኖቹ የሚሞቱት በመቶ ምናምን ዓመታቸው ነው። ”በሰባ ዘጠኝ ዓመቱ እገሌ ሞተ” ሲባል ከሰሙ ”ምን አገኘውና?” ብለው አጥብቀው ይጠይቃሉ። አጠያየቃቸው ”እንዴት በዚህ በለጋ ዕድሜው ሞተ?” የሚል አዘኔታ ያዘለ ነው። አንዲት ኢትዮጵያዊት አንድ ከተማ ያለ ቤተስኪያን ሄዳ የመቃብር ኃውልቶች ላይ የተፃፈውን እየተዘዋወረች ስትጎበኝ አንድ ልጅ ብቻ በ፳፮ (26) ዓመቱ ሲሞት ሌሎቹ ግን በሰማኒያዎቹና ከዚያ በላይ ናቸው። እሱም የሞተው በመኪና አደጋ ነው። እኛ ግን ጤፊቱን ብቻ የሙጥኝ ብለን ዕድሜአችንን እንገዘግዛለን። ጤፍ ውስጥ ስለተገኘው አዲሱ ንጥረ ነገር ታውቃለህ? … እሱን ሌላ ጊዜ አጫውትሃለሁ።

ወንድሜ ሆይ! እስከማውቅህ ለውጥ ፈላጊ ነህ። አገራችንም ተለውጣ ማየት እንደምትወድ አውቃለሁ። አንተና እኔ ሳንለወጥ አገራችን እንድትለወጥ የምንሻ ከሆነ የቂሎች ቂል ነን። ለውጥ የሚጀምረው ከራስ ነው። በሌላው ሁሉ ነገር ለማደግና ለመለወጥ ከፈለግን የዕለት ተዕለት ተግባራችን በለውጥ የተሞላ መሆን አለበት። ምግብ ከደላህ በቀን ሦስቴ ካልሆነም አንዴ ትገናኘዋለህ። እናም እስቲ ከሱ ለውጥ እንጀምር። የኢቲቪን ፕሮግራም ልብ ካልነው ማግኘት የማንችለው የምግብ ጥሬ ዕቃ የለም። በሣምንትም ሆነ በወር አንዴ የስሙኒ ቃሪያ፣ የሽልንግ ቲማቲም፣ … መግዛት ከቻልን፤ ስንፍና ከሌለብን መሥራቱ ምን ያዳግታል? ስንፍና ነፍሷ እላያችን ላይ እንደዛር ሠፍራ ከሆነ ግን መቼም አንለወጥምና ”እየኖርን ነው!”ን ትተን ”እየሞትን ነው!”ን እንዝፈን። እስቲ ከወዳጆቻችን ጋር ምከርበት። ተመካከሩ። እንመካከር። ጊዜም እንስጠው። ከሌሎች ጋርም እንምከር። የምናውቀውን እናሳውቅ፣ የማናውቀውንም እንወቅ - ለማወቅ እንጣር።

ጌታው! ሁሉም በየፊናው ”ለውጥ! … ለውጥ! … ለውጥ! ...” እያለ ይጮኻል። አንተም - እኔም - ጓደኞቻችንም - ወዳጆቻችንም - ኅብረተሰቡም - መንግሥትም - ተቃዋሚዎችም - …። ነገር ግን ሁላችንም ራሳችንን ያልጠየቅነው ጥያቄ እንዳለ ይሰማኛል። ”እውነት! እያንዳንዳችን ለለውጥ ተዘጋጅተናል?”፣ ”እውነት - ለውጥ እንዲመጣ ያበረከትነው አስተዋፅኦ አለን?” … እነኝህን ጥያቄዎች ዘለናቸዋል። የዘለልናቸው ዘንግተናቸው አይደለም - በስምምነት እንጂ። የተስማማነው ሳንነጋገር ነው። ሳንነጋገር ሁላችንም ኃላፊነትን መሸከም ስለማንፈልግ ጥያቄዎቹን ዘለልናቸው። አሪፎች ነን! ራሳችንን በማቄል ተወዳዳሪ የሌለን አራዶች። ከቶ ማንም ሊወዳደረን አይችልም።

ስለምግብ እንዲህ የዘላበድኩትና ጊዜ የፈጀሁት እውነት ለውጥ ፈላጊ ከሆንን ለለውጥ ከመሮጣችን በፊት ለመንደርደሪያ - ዱብ ዱብ ለማያና ራሳችንን ለማሟሟቅ ሳይረዳን አይቀርም ብዬ ነው። በመግቢያዬም ”… ብትሰደድ እንድትዘጋጅ፣ ካልተሰደድህም …” ማለቴንም አትዘንጋ።

ወንድሜ ሆይ! እዚህ ከመጣሁ ያልነደድሁበት - ያልተቃጠልኩበት - ያላረርኩበት - ያልበገንኩበት - … ነገር የለም። የዚህ ሁሉ ምክንያቴ ሁሉንም ነገር ከእምዬ ኢትዮጵያ ጋር ማወዳደሬ ነው። ማወዳደሬንና ማስተያየቴን መተው አልቻልኩም - አልችልማ! ንዴቴን ማብረጃዬ አንተው ነህና ዛሬ ”ሀ” ብያለሁ። ንዴቴ ትንሽ በረድ እስኪልልኝ ስድቤን አላቋርጥም። ዛሬ እንደምፈልገው አልሰደብሁህም። በሚቀጥለው ስድቤ ማደጉ አይቀርምና ተዘጋጅ። ስድቤ ሲያንገሸግሽህ ”አቁም!” በለኝ። የምሳደበው፣ የምወቅሰው፣ የምወነጅለው፣ … አንተን ብቻ መስሎህ ከሆነ ተሳስተሃል፤ እኔንም ጭምር ነውና - ቻለኝ።

ጌትዬ! ለዛሬ ይብቃህ! ”ሄዶ!” (በስዊድንኛ ”ቻዎ!” ማለት ነው)

ወደ ስደት ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

 

Hosted by www.Geocities.ws

1