ወደ ኪነጥበብ ገጽ መልሰኝ      ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

ዓይኔን ምች መታው

”የተማረ ሣሙና አጥቦ ይግደለኝ!”

በኃይሉ ገብረእግዚአብሔር (ከሐመረ-ኪን)

***********************************

ይሄን በሽታዬን ስንዴነሽ ጥጋቡ የሰማች እንደሆነ አልጋው ጦሙን ማደሩ ነው። ስታኮርፍ እንዲህ ነው የሚያደርጋት። እኔን ታልጋው ላይ ጥላኝ እሷ ተመሬት ስትንደባለል ማደር። የበሽታዬን ሲቃ የማሰማው በሆዴ ነው። እህህ … እህህ … እህህ … እሷ እንዳትሰማኝ ማለቴ ነው።

”እዝጊሐር ይማርህ!” የማያሰኝ ትልቅ በሽታ ይዞኛል። እህህህ … እህህህ … ህህ … ህ … ህ … ለሰው አይነግሩት ነገር የቸገረ፣ ለአዋቂ አያማክሩት የከበደ መጥፎ ተንከሲስ በሽታ። እህህህ … እህህህ … ጐበዝ! ከዓይን ምች ይሰውራችሁ!!

አበው የዓይንን ጥቅም፣ የዓይንን አስፈላጊነት ሲቀምሙና ዓይን ጉዳት እንደማይችል ሲገልፁ ”ለዓይንና ለወዳጅ ትንሽ ይበቃል” ብለዋል። የዓይን አገልግሎት ምኑ ተወግቶ? የዓይን ጥቅም ይሄ ይሄ ነው ብለው ቢጀምሩት ማለቂያ ስለሌለው አፍ ማበላሸት ነው የሚሆነው።

ይኸውና ዛሬ ምች ዓይኔን ጠንብሶ ጥሎኝ ”እህህ …” እያልኩ በሽታዬን እያስታመምኩ ነው። ይሄን የኔን በሽታ እንኳን ለወዳጄ ለጠላቴም አልመኘው። ምን በወጣውና! ሲያቀብጠኝ ’ዘመዴ’ የምለው ባልንጀራዬ ቤት ሄጄ እኮ ነው ለዚህ በሽታ የተዳረኩት። ጉድ! እኮ ነው ጐበዝ! ካሣ አልጠይቅ ነገር ማን እይ አለኝ? እሱስ ምን አደረገኝ? በገዛ እጄ እተከፈተው ቴሌቭዥን ላይ አፍጥጬ ነው የምች በሽታ ጠልዞ የጣለኝ - አንዳች ነገር ጠልዞ ይጣለውና። ”ዕዳ፣ ከሜዳ” ይሏችኋል ይሄ ነው።

ነገሩ እንዲህ ነው። የአማርኛ ፕሮግራም ደረሰና ቴሌቭዥኑ ተከፈተ። ቡና ተፈልቷል። ቡናው እየተጠጣ የሰዉ ዓይን ሁሉ ያለው እተከፈተው ቴሌቭዥን ላይ ነው። እኔም እንደሰዉ ዓይኔን ላኩት። ዜናው ተነበበ፤ የአገር ውስጥና የውጪውን ዜና አየን፣ ሰማን። ለሚያስደንቀው እየተደነቅን፣ ለሚያሳዝነው ከንፈር እየመጠጥን (ማድረግ የምንችለው ይሄን ብቻ ስለሆነ) ቀጣዩን ነገር ማየት ተያያዝነው። ባንድ እጃችን ቡናችንን እንደያዝን ማለት ነው። ቀጠለ ማስታወቂያው። አስታውሱ እስከዚህ ሰዓት ድረስ ብርድም ሆነ ወበቅ የማይሰማኝ ጤነኛ ነበርኩ። የዘይቱ፣ የቅባቱ፣ የእርሻው፣ የቆርቆሮው፣ የልብሱ፣ የሚስማሩ፣ የላስቲኩ፣ ’ለሕይወትህ ዋጋ ስጠው’፣ የቤተሰብ ምጣኔው፣ የደብተሩ፣ የጫማው፣ የጫማ ቀለሙ፣ የግድግዳ ቀለሙ፣ የብስኩቱ፣ የሰንደሉ፣ … ማስታወቂያ እስክንጠግብ፣ ”አልበዛም እንዴ?!” ብለን እስክናጉተመትም ድረስ ’ነፍ’ አየን። በድጋሚ እላችኃለሁ - ስንዴነሽ ትሙት! እስከዚህ ሰዓት ድረስ ጤናዬ ዝንፍ አላለም። ደነኛ ነበርኩ።

ቡና የሚጠጡ አሽሟጣጭ ባልንጀራዬና ባልንጀሮቹ እያንዳንዱን ነገር እየተነተኑ ሲያሽሟጥጡ እኔ ጆሮዬን አልሰጠኋቸውም። ስለምን? - ቀልቤ ያለው ቴሌቭዥኑ ላይ ነበርና። አልፎ አልፎ ግን የሚሉት ነገር ይሰማኝ ነበር። ”ልጅቷን ነው ወይስ ቅባት ነው የሚያስተዋውቁት?”፣ ”አቤት! ግነት”፣ ”ሙሽሪት ቦሌ ሄዶ ሣሙና ማምጣት የጫጉላ ሽርሽር አደረገችው እንዴ!?”፣ ”የተማረ ሣሙና አጥቦ ይግደለኝ፤ … ቦሌ ድረስ የሚመጣ ጀግና”፣ … ጥፍር ቀለም የምታስተዋውቀዋን ሴት ”አቤት ዓይኗ ሲያምር!?” እያሉ ሲተቹ አልፎ አልፎ አድምጫለሁ። ይሄ ሁሉ ሲነገር ”የስንዴነሽን እናት ቀን ይስጠኝ!” ትንፍሽ አላልኩም። ኮስተር ብዬ፣ ቅንድቤን ሰብሰብ አድርጌ ቴሌቭዥኑን እየተከታተልኩ ነበር። ይህን ያልኳችሁ፣ ደጋግሜ የምገልጽላችሁ፣ ”ምላስህ ግፍ ጠርቶ፣ ጡር ተናግረህ ነው ለምች በሽታ የተዳረከው” እንዳትሉኝ ስለሰጋሁ ነው።

እናላችሁ የሣሙና ማስታወቂያ መጣላችኋ። ማንትስ ሣሙና፣ ቅብርጥስ ሣሙና፣ ዙጴቁልቋል ሣሙና፣ … ”ልብሶችን ዳንኪራ የሚያስረግጥ ሣሙና” … መቼስ ለጉድ ነው። እንደማስታወቂያው ከሆነ፣ ”ማንትስ ሣሙና አጥቦ ይግደለኝ!”ን ያስተርታል። ”ባልታጠብበት አይቼው ልሙት!” ያስብላል። እንደኔና እንደስንዴነሽ አይነቱማ ሲመኘው ውሎ፣ ሲመኘው ያድራል እንጂ ወየት ያገኘዋል?! ስንዴነሽ ይሄን ማስታወቂያ ብታይና የመግዛት አቅሙ ቢኖራት ”እንዶድ ማናባቱንስና!” ብላ ከነዘር ማንዘሩ ሰዳድባ ታባርረው ነበር። ግና ያዱኛው ነገር ሆኖ፣ አምሃው አልሞላ ብሎ …

ነገረኛው ዓይኔ ሳላዘው፣ ሂድልኝ ሳልለው፣ ሌላ ሌላውን ሲያይ ውሎ መጨረሻ ላይ ሣሙና ለማስተዋወቅ ልብስ የምታጥብ ልጅ ላይ ሂዶ ተዘረረላችኋ። እወቁት ይኸው ነው በሽታዬ። ለማጠብ (ለማጥባት አይደለም፤ ልብስ ለማጠብ እንጂ) ጐንበስ ቀና እምትለዋ ሴት ጡቶች መሃል ዓይኔ ስንቅር … ቅርቅር … ተዚያማ በምች በሽታ ልክፍ … ወዲያው ሰውነቴ ዝልፍልፍ። ”ጡት ነው ሣሙና የሚያስተዋውቁት?” ብዬ ለመተቸት ሳልታደል ዓይኔ ደክሞብኝ እርፍ። በሹክሹክታ ያወሩበታል ወይም ያወሩለታል እንጂ አደባባይ የማያወጡት ነበር። የሴት ነውር ላይ ዓይኔ አፍሮ በምች በሽታ ተጠብሶ ቁጭ። እዝጊዎ! ማማሩ፣ እዝጊዎ! አተላለቁ - አንድስ እኮ ነው የሚያህለው! … አክ እንቱፍ … ምን አይነት ነውረኛ ነገር ተናገርኩ እቴ! … ”ውሾን ያነሳ፣ ውሾ ይሁን!”

መጀመሪያ ነገሩ ግራው ቢገባኝ፣ የበሽታዬ ምህኛት ቢጠፋኝ፣ በምጠጣው ቡና አመሃኝቼ እርፍ። ”የቡናው ቆሌ ተቆጥቶኝ ነው” ብዬ ደመደምኩ። ”የሱ ነገር እየጠጡ መጥፎ ነገር ሲያዩበት፣ ቡናውን አቋርጠው ሲሄዱበት፣ … አይወድም” አልኩ።፡የስንዴነሽ ጥጋቡ አድባር ቆሌ ይለመነኝ! ይቅር ይበለኝ! እንጂ ምህኛቴስ ከንቱ ነበር። የታመምኩት እንደእንቧይ የሚነጥር ጡት ላይ ዓይኔ በማረፉ ብቻ ነው። ሌላ ነገር የለም። ይኸው ዛሬ በሽታን ባሰብኩ ቁጥር ዓይኔን እየጠዘጠዘ፣ ልቤን እየሰወረ ያሰቃየኛል። ውይ! ውይ! ውይ! … ይኼን በሽታ እንኳን ለወዳጄ ለጠላቴም አይስጠው!! ሆሆ! ምን በወጣውና። ለስንዴነሽ ዓይኔን መታመሜን እንጂ የበሽታውን ምህኛት አላወራኋትም። ሆሆ! ትግደለኝ ብላችሁ ነው? ምን እሴት ጡት ላይ ዓይንህን ሰደደው? ብላ በቅናት ቋንጣ ነው የምታደርገኝ። ስለምን? - እኔና ስንዴነሽ የምናውቀው የጐረቤታችን አንድ ታሪክ አለና።

ጐረቤቶቻችን የሆኑት ባልና ሚስት አብረው ቁጭ ብለው ቴሌቭዥን ሲመለከቱ ባል በሆነ ማስታወቂያ ላይ የተመለከታትን ሴት ውበት ሲያደንቅ ሚስቲት ሰምት እንደተጣሉ ሰምተናል። እና ይሄን እያወኩ ”በቴሌቭዥን ያንዲት ኮረዲትን ጡት ስመለከት ዓይኔን ምች መታኝ” ብዬ ብነግራት ስንዴነሽ የምትለቀኝ ይመስላችኋል? ሆሆ!! ”በለፈለፉ ይጠፉ” አሉ! በሉ ”እዝጊሐር ይማርህ!” በሉኝና በዚህ እንለያይ። ኧረግ! … ኧረግ! … ኧረግ! … ዓይኔን እኮ አመመኝ ጐበዝ! እህህህ … እህህህ … እህህ … ህህ … ህህ … ህ … ህ … ህ … ህ …

ወደ ኪነጥበብ ገጽ መልሰኝ      ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

 

Hosted by www.Geocities.ws

1