ወደ ኪነጥበብ ገጽ መልሰኝ      ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

የሚስት ያለህ!

”እድሌ ሆነና ሚስት አይበረክትልኝም”

በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር (ሐመረ-ኪን)

***************************************************

እኔ ጠላቶቼን እወዳለሁ። ጠላቶቼን ”ጠላት” ማለቱ የሚያስኮንነኝ ከሆነ፤ አዎ! ሁሌም ቢሆን ጠላቶቼን እወዳለሁ።

መቼም እንደሽማግሌ የታክሲ ሹፌር፣ የጭነት መኪና እንደሚያሽከረክረው ጠብደል ጐረምሳ፣ ጋዜጣ እንደሚያዞረው ወጠጤ እና ያ በየሆቴሉ ”እዘፍናለሁ” እያለ እንደሚያንቋርረው አዝማሪ በዚህ ምድር ላይ ጠላት የለኝም። ይኑሩ! ሌላ ምን ይባላል? ጠላቶቼን እወዳለሁና ክፉ ነገር እንዲገጥማቸው አልመኝም። ሰው አፍቃሪና አክባሪ ነኝ ብዬ አስብ ነበር፤ ነገር ግን ዕድሌ ሆነና ሚስት አይበረክትልኝም። ይኸው ከላይ የጠቀስኳቸው ግለሰቦች የኔ የግሌ የሆኑ ሴቶችን የግል ንብረታቸው ያደረጉ ሕገ-ወጦች ናቸው።

አበድኩላት፣ … ከነፍኩላት፣ … ሞትኩላት፣ … እያልኩ ከእጄ እንደማትለይኝ ጃንጥላ ማደሻ ጉጠት፣ ስሟ ካፌ የማይወጣውን ባለቤቴን የራሱ አደረጋት - ያ እርኩስ ሽማግሌ ሹፌር - አውቶቡስ በቅጡ እንኳ መሳፈር የማይችለው። ”ወርቄ” ታክሲ ውስጥ ከዚህ ሰውዬ ስር ሽጉጥ ብላ ሳያት፤ ሽጉጥ ለመጠጣት ምንም አልቀረኝ። ደግሞስ ሽጉጥ ከየት አገኝና! ምን እንደሰቀላት አላውቅም። ምንስ እንዳገናኛቸው አላውቅም። ወይ ጉድ! የዘንድሮ ሴት! ምነው ተሹፌር ላይ ዓይኗን አልነቅል አለችሳ? ወርቄን ላለማጣት ስል እልህ ውስጤን እየበላው ሹፌር ለመሆን ከፍተኛ ፍላጐት ነበረኝ። … ምን ዋጋ አለው? ከቀኝ እጄ ጣቶቼ ውስጥ ትልቁ ተወገቡ በላይ የለም። ገንዘብም የለኝም። ይኸው በዚህ ልክስክስ ሽማግሌ ምክንያት ታክሲ የሚባል ነገር ጠልቼ ልሞት ነው። ተሰው መሃል ተለክቼ፣ ተጨናንቄ በአውቶቡስ እሄዳለሁ እንጂ ታክሲ የሚባል ነገር በጭራሽ! … በጭራሽ! … አታንሱብኝ። ለነገሩ ገንዘቡስ ቢገኝ አይደል?

ያም ሆነ ይህ ወርቄ ልታታልለኝ ሞክራለች። አታላኛለችም። በላዬ ላይ ሸፍታለች። በእውነቱ እኔ ሚስቴን አፍቃሪ፣ ትዳሬን አክባሪ አይደለሁምን? ይኼ ሁሉ ሸፍጥ ለምን አስፈለገ? እሷ የምትለው ”የታላቅ እህቴ ባል ነው” ነው። እኔ ግን አላምንም። ለምን ጋቢና ገብታ - ተጐኑ ትወሸቃለች? … ለምን? … እኮ ለምን እንደማንኛውም ስትር፣ ቁጥብ ባለትዳር ከኋላ ወንበር አትቀመጥም? ታዘብኳት! … ታዘብኳት! … ታዘብኳት! …

እሷ ግን ይባስ ብላ ”ላስተዋውቅህ” ብላኝ እርፍ። እኔም ፍጥጥ። ምን አጨቃጨቀኝ። ይኸው የታክሲ ሹፌርን በሙሉ እንደታላቅ ደመኛ የማይበት ምክንያት ለዚህ ነው።

የዛሬ ሁለት ዓመት ከወርቄ በኋላ ያገባኋት ትርንጐን ነበር። ተቡና ቤት ያገኘኋት … ያቺ እንኳን አጭሯ ትርንጐ … እሷን እንኳ እቤቴ አላመጣኋትም ነበር። እዛው እምትሠራበት ቡና ቤት ካለችው ጓዳ ሁለት ቀን ጐበኘኋት። ተዛ በኋላ ተውኳት። ሁለት ቀን የጐበኘኋት ”ይቅርብኝ!” ብዬ ገንዘቤን አፍስሼ ነበር። ይኸው በዝችው ቀንቶ እኔ በገባሁበት ጓዳ ያ ጠብደል ጎረምሳ ሲገባ በዓይኔ በብረቱ አየሁት። ለቤቴ ያጨኋት ትርንጐ፣ ቀን የተቆረጠላት ትርንጐን በዛው ትውት አደረኳት። እኔ’ምለው ሹፌር ሁሉ ያለእኔ ምርጫ አይስማማውም ልበል? ይኼን ስላችሁ ቅናት ነው የሚያናግረው ትሉ ይሆናል። እኔ እንኳን ልቀና ይቅርና ሲያልፍም አይነካካኝ። እሺ! … ንገሩኝ ወደ ጓዳ ምን ሊያደርግ ነው የገባው? በጉልበቱ ተማምኖ አይደል? ያው! … ይጠቅልላት! … ያግባት! … ትቼለታለሁ።

አዋቂ ናት፣ በሳል ናት፣ ብልህ ናት ብዬ ያገባኋት ማሪቱ ደግሞ ኃይለኛ ችግር ያለባት ሴት ሆና በመገኘቷ ፈታኋት። እሷ ደግሞ ካለአመሏ፣ ካለፀባይዋ ፖለቲከኛ … አጭበርባሪ … የሴቱን ጉዳይ ሁሉ ”ይመለከተኛል!” ባይ ነገር ናት። ይህን ያልኩት በየዋህነት ነው። ይመለከታት ይሆናል ምን አውቃለሁ? ብቻ በምኖርበት ቀበሌ ውስጥ የሴቶች ምንትስ ናት አሉ።

ማናቸውንም ወግ ስናወጋ ”ከመብት አንፃር” … ”ዴሞክራሲያዊ መብት” … ማለት ይቀናታል። እኔ በዚህ ባህሪዋ ተቃውሞ የለኝም። ከመብት አንፃር የፈለገችውን መናገር፣ በፈለገችው መሳተፍ ትችላለች። ግን እቤት ድረስ የምትጠራው ጋዜጣ አዟሪ አለ። ምኗ ነው ብዬ እራሴን ጠየኩ። አዎ! ውሽማዋ ነበር። ”ጋዜጣ የሚሸጥልኝ ደንበኛዬ ነው” አለችኝ - አንድ ቀን እቤት ተጐልቶ ሳየውና ስነቃባት።

እኔም ዝምተኛ ቢጤ አይደለሁ?! አዎ! ”ያልጋ ላይ ደንበኛሽ” አልኩ - በሆዴ። እንዲህ ስላችሁ ቅናት ነው ልትሉ ትችላላችሁ። እኔ ቅናት ሲያልፍም አይነካካኝ። ኧረ! ምናባቱ ሊያደርግልኝ? ግን እንደው አስቡት የ፲፬ (14) ዓመት የከተማ ጮሌ በውሽማነት መያዟ ”ከመብት አንፃር” ትክክል ናት ትላላችሁ? እኔ ጋዜጣ ስትገዛ አይቻት አላውቅም። ሃያ … ሰላሳ … ሣንቲም ትሰጠዋለች። ሰጥቷት የነበረውን ጋዜጣ መልሶ ይወስደዋል። እንግዲህ ምን ስላረገ ነው የሚከፈለው? የሌላም ነገር ደንበኛ መሆኑን ስለተረዳሁ በእሷው ቋንቋ ”ዴሞክራሲያዊ መብቴን” ተጠቅሜ ፈታኋት - ማሪቱን።

ይኸውላችሁ አፍቃሪ ልብ አጥቼ አንዷን ስፈታ አንዷን ሳገባ የወርቅውሃ ላይ ደረስኩ። ለወርቅውሃ እኔ ሦስተኛ ባሏ ነኝ። የመጀመሪያ ባሏን ንቃ ትታው ነው አሉ። ሁለተኛ ባሏ ደግሞ በመኪና አደጋ ሞተባት ሲሉ ነው የሰማሁት። እና መቼም የሕይወት ልምድ አላት፣ ኑሮ አዋቂ ናት፣ ብዙ ነገር አሳልፋለች ብዬ ባገባት ነገር አምጥታ ቁጭ አለች።

እኔ እኮ በቃ ሚስቶቼን ስከታተል አረጀሁ። የወርቅውሃማ እርቃም አልሄደች። ያ በየሆቴሉ ”እዘፍናለሁ” እያለ ማሲንቆውን ተሸክሞ ከሚዞረው ጐረቤቴ ጋር ተወዳጅታ አረፈችው። ነጋ ጠባ ሠላምታ ነው። ነጋ ጠባ ”ደህና አደርክ? … ደህና ዋልክ? …” ነው። እኔ ምን አጨቃጨቀኝ? እኔ በሌለሁበትስ ምን እንደሚሠራ አውቃለሁ? ስለዚህ በቃ! ምን አደርጋለሁ? - ፈታኋት! … ደግሞ በግጥም ሰውየው ይሰድበኛል አሉ። ይገርማል እኮ! ምን ልሁን እያለ እንደሆነ አይታወቅም። ደግሞ እሱን ብሎ አዝማሪ! ከሱ ድምፅ የውሻ ጩኸት ይሻላል። እንዲያው በጉልበት አዝማሪ ነኝ እያለ ያባወራ ሚስት ሲያባብል፣ ቆነጃጅት ላይ ዓይኑን ሲያንቀዋልል ይውላል። እንዲህ ስል ቅናት እንዳይመስላችሁ። ቅናት ሲያልፍም አይነካካኝ።

ከነዚህ አራት ዋልጌና ስርዓት አልባ ግለሰቦች ውጪ ጠላትና እንደጠላት የማየው ሰው የለም። ግን ጠላቶቼን እወዳለሁ። በመውደዴም ነው ተሰው ጋር ተፋቅሬ፣ ተዋድጄ የምኖረው። እስኪ አምስተኛዋ ባለቤቴን ደግሞ ልፈልግ … ”ይቅናህ!” አትሉኝም እንዴ?! …

ወደ ኪነጥበብ ገጽ መልሰኝ      ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

 

Hosted by www.Geocities.ws

1