ወደ ኪነጥበብ ገጽ መልሰኝ      ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

ነገር ይገንብኛል

በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር (ከሐመረ-ኪን)

***************************************************

እኔ በጣም በጣም ነገር ይገንብኛል። የሆነች አንዲት ትንሽ ነገር ትንፍሽ ካልኩ ነገሩ ተካብዶ ተካብዶ ግራ ተታኮ ቁጭ ይላል። ምን ታደርጉታላችሁ? … በቃ! የዘወትር ልማዴ ነዋ! አንዳንዴ ቁጭ ብዬ ሳስበው እንኳን ንግግሬ ትንፋሼም ሰው የሚያስቀይም ይመስለኛል። በግል ውይይት አልያም ስብሰባ ላይ ”ዝምታ ወርቅ ነው”፣ ”ዝም አይነቅዝም” ብዬ አደብ ብገዛ ”ምን በሆድህ ነገር ትይዛለህ? ተንፍሰው እንጂ!” ባይ አሽሟጣጭ አላጣም። ስለምን? በቃ ዝም ብሎ ነገር ይገንብኛልና ነው። አስተውሉ ዝምታው የኔ የግሌ ብቻ ላይሆን ይችላል።

’መቼም በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የሞተን መቅበር፣ የታመመን መጠየቅ የመሰለ ነገር የለም’ አልኩና አንድ ቀን ለቅሶ ቤት ኀዘንተኛ ለማስተዛዘን ሄድኩ። እናም ገብቼ ቁጭ እንዳልኩ ጉሮሮዬን ጠራርጌ ”ኀዘንን በልክ ማድረግ ነው። መቼስ ምን ይደረጋል? ሟችንም ነብሳቸውን ይማር!” ብዬ ለማስተዛዘን ያህል ተነፈስኩ። ኀዘንተኛዋ እሳት ለብሳ፣ እሳት ጐርሳ፣ ከለበሰችው ጋቢ አንገትዋን አስግጋ ዓይኗን አፈጠጠችብኝ። ’ምን ክፉ ነገር ተናግሬ ይሆን?’ ብዬ በድንጋጤ ራሴን መዝለፍ ያዝኩ። ”የትኛው የሠራችው ኃጢያት ነው ’ነብስ ይማር!’ የሚያሰኛት? … ምነው? ምን ነካህ?” ስትለኝ ተቆጥታ፤ ጠላታችሁ አመድ ይምሰል፣ በድንጋጤ አመድ መሰልኩላችሁ። ይኸዋ! ነገር ይገንብኛል አላልኳችሁም?! ይኸዋ! ኀዘንተኛ ለማስተዛዘን ሄጄ አበሳጭቼ ቁጭ አልኩላችሁ። እኔን ብሎ አስተዛዛኝ’ቴ! እውነት ግን ይህ አባባል ማንኛውም ሰው የሚናገረው አይደለም?

ምን ማስተዛዘን ብቻ መች ቀልጄስ ያምርብኝና? ይልቁንስ አንዴ የሆንኩትን ላጫውታችሁ። አንድ ቀን አስታውሳለሁ … የሆነ ካፍቴሪያ ገባሁና ወተት አዘዝኩ። ከዚያም ከዚህ በፊት የሰማኋትን ቀልድ ቀልጄ … አስተናጋጇን ላስፈግጋት ላስደስታት አልኩና ”ለመሆኑ ወተታችሁ የላም ወተት ነው ወይስ የናት ጡት ወተት?” ብዬ ጥያቄን ያዘለ ቀልድ ቀለድኩ። አጅሪት እንኳን ልትስቅ እቴ! ፊቷን ቅጭም አድርጋ፣ ”ይህን ያህል መውለድ ያሰድባል? … ወልደሻል ለማለት ነው አይደል?” ብላኝ እርፍ። ኧረ! በስመአብ እቴ! ምኑን አመጣችብኝ ”በእውነት! ለቀልድ የተናገርኩት ነው። ደግሞ አንቺን የት አውቅሽና?” በማለት ይቅርታ ለመጠየቅ ሞከርኩ። እሷ ግን በኃይለኛው ገላምጣኝ ፊቷን እንደቋጠረች ጥላኝ ውልቅ አለች። ምነው የማልችልበትን ባልቀልድስ? ተናግሬ የማያምርብኝ፣ ከቶም ቀልጄ ሊሳካልኝ!? ኡኡቴ! ”ወግ አይቀርም ሲዳሩ ማልቀስ” አሉ። ምነው አፌን በሰበረው ኖሮ!

አንዴም እንዲሁ አይነት ተመሳሳይ ነገር ገጥሞኛል። ”ሰዓት ስንት ነው?” ብላ አንዲት ማለፊያ ልጅ ስትጠይቀኝ፣ ሲያቀብጠኝ ”አይሸጥም” ብዬ የጨረታ ቀልድ ቀለድኩ። ልጅቷ ምን እንዳለችኝ ታውቃላችሁ? ከንፈሯን በኃይለኛው መጠጠችና ”ውይ ስታሳዝን! ምስኪን! የቀልድ ደሃ” ብላኝ እርፍ። እውነትም ሳሳዝን! ለማሳቅ ቀልዶ፤ ሰው ከማሳዘን ይሰውራችሁ እቴ!

”የሠራተኛው መብት ይረጋገጣል! … የላብ አደሩ መብት ይረጋገጣል! … የሴቶች መብት ይረጋገጣል! …” የሚል መፈክር ያነገበ ህዝብ መፈክሩን እያሰማ በመንገዱ ይተማል። እኔም ከህዝቡ እንደአንዱ ነኝ አልኩና ከሰልፈኛው ጋር ተቀላቅዬ ”ይረጋገጣል! … ይረጋገጣል! … ይረጋገጣል! …” ስል አንዱ ”ምኑ ነው የሚረገጠው? አንተ አድርባይ! ምኑ ነው የሚረገጠው? አንተ ያለፈ ስርዓት ናፋቂ! ምኑ ነው የሚረገጠው?” በማለት ሰደበኝ። በሰው መሃል አሳጣኝ። አሳቀለኝ። ”አንተን ማስቀፍደድ ነበር! አስኮናኝ!” ሲልም አስፈራራኝ። አስተውሉ እኔ ብቻ እኮ አይደለሁም ”ይረጋገጣል! ያልኩት። ህዝቡ በሙሉ ነው። አንዱ ድምፁን ከፍ አድርጐ ”የሴቶች መብት ይረጋገጣል!” ካለ እኔና ህዝቡ ባንድ ላይ ”ይረጋገጣል!” እንላለን። ግን ይኼ እግረ ነጭነቴ፣ ደመ መራራነቴ እየተከተለ ጥርስ ውስጥ የሚያስገባኝ እኔን ብቻ ነው። … ነገር ይገንብኛል አላልኳችሁም? ይኸዋ!

ጨዋነትን ተገንዝቤ፣ ትህትናን ቀለቤ አደረኩ አልኩና ለተሰሩልኝ ጥቃቅን ውለታዎች በሙሉ ”እግዜር ይስጥልኝ!” ብዬ ያመሰገንኩ እንደሆነ፤ ”አሁን ለዚህ ምን ’እግዜር ይስጥልኝ!’ ያስፈልገዋል?’ ብሎ ምርቃቴን እንደ እርግማን እየቆጠረ የማይገላምጠኝ፣ የማያሽሟጥጠኝ የለም።

ከጐረቤት አልያም ከቅርብ ሰው አንዱ ውጭ አገር የመሄድ ዕድል አጋጥሞት የሽኝት ፕሮግራሙ ላይ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ያልተገኘሁ እንደሆነ ”እዩት ምቀኝነቱን፣ አሁን በሰው ዕድል ምን አስቀናው? አዬ ምቀኝነት!? …” የሚል ዘለፋ ምሳ እና እራቴ ይሆናል። ይታያችሁ ወደ ውጭ የሚሄደውን ልጅ ያልጠየቀው ’ደህና ሰንብት!’ ያላለው አንድ ሺህ አንድ ሰው ሊኖር ይችላል። ግን ነገር በእኔ ላይ ብቻ ስለሚገን የስድብ ናዳው እኔ ላይ ብቻ ይከነበላል። ደግሞስ የእኔ ”ደህና ክረም! …” ማለት ምን ሊፈይድላቸው ይሆን? ብቻ ነገሮች ሁሉ በኔ ላይ በጣም ይገናሉ።

እኔም ይሄን ይሄን እያየሁ ነገሮችን ተወት ካላደረኳቸው በቀር የእኔ ነገር አያልቅም መቼም። በመጨረሻ ግን ይቺን ብቻ አጫውቻችሁ ወጌን ላብቃ።

አንድ ጊዜ ለሆነች አነስተኛ ዝግጅት ማለፊያ የሱፍ ኮትና ሱሪ አስፈለገኝ። ሰዉን ለመምሰል፣ በቃ! የግድ አስፈለገኝ። ግን ያለኝ ብር እንኳን ሱፍ ሊገዛልኝ ቄንጠኛ ኮፍያ አይገዛም ነበር። ስለዚህ ልባሽ ተራ ጎራ አልኩ። መቼም የሰልባጅ ነጋዴዎች የሚሸጡት ከፖሊስ ጋር እየተሯሯጡ፣ እየተፋጠጡ፣ እየተጋጩ ስለሆነ ለገበያ ያቀረቡትን ልብስ ለብሰው ነው ከገዢ ጋር የሚዋዋሉት።

የኔም ዓይን ከተለበሱ ኮቶች ላይ ይንቀዋለላል። እንደአቅሜ ቀበቶ መሳይ ከረባት መግዣ እንድትተርፈኝ ልብስ አመራረጤ ከዋጋው አንፃር ነው። በዚህ መሃል አንዲት ኮት ላይ ዓይኔ አረፈ። ቀልቤ ወደዳት። ኮቷን የለበሰውን ሰውዬ እያሽከረከርኩ አዟዙሬ በመመልከት፣ ”ይቺ ስንት ናት? መበያህን ንገረኝ፤ ያለኝ ብር በጣም ትንሽ ነው፣ ከፖሊስ ገር ከምትሯሯጥ …” ተናግሬ ሳልጨርስ ባለ በሌለ ኃይሉ ገፍትሮ ከሆነ መንገደኛ ጋር አጋጨኝ። እንደምንም ተንገዳግጄ ቆምኩ። ”ሌባ! እኔ ልብስ ስሸጥ አይተኸኛል? ቀን በቀን ልትዘርፈኝ ነው? ሌባ!! …” እዝጊዎ! ምኑን አጋጠመኝ!? ግብግብ አልገጥም ነገር ጥፋተኛው እኔ። በቃ ማድረግ ያለብኝ እንደሁልጊዜ ይቅርታ እሱንም መጠየቅ ነው። ይቅርታ! … ይቅርታ! … ይቅርታ! … ግን እኮ ሰውየው ”የኔ ወንድም ይቅርታ እኔ ነጋዴ አይደለሁም” ማለት ይችል ነበር’ኮ! አይ ተዉት ግንባሬ ነው። ዕድል ሆኖ ነገር በጣም እንደሚገንብኝ አጫውቼአችሁ የለ?!

በዚሁ ነገሬን ልቋጭ። አሃ! ድንገት’ኮ በዚህ ጨዋታዬ ያስቀየምኩት ሰው ሊኖር ይችላል። በቃ! ዝም ብሎ ነገር ይገንብኝ የለ?! - ይቅርታ! በጣም ይቅርታ!

ወደ ኪነጥበብ ገጽ መልሰኝ      ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

 

 

 

Hosted by www.Geocities.ws

1