ወደ ኪነጥበብ ገጽ መልሰኝ      ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

እነቀልጣፊት ምግብ ቤቶች

ለጤና ጤና ጣቢያ ያስብበት

በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር

***********************************

እነ እንቶኔ አድናቆታቸውን ሲገልፁ “ለፕሮቶኮል የማይመቹ፤ ግን አሪፎች” ይሏቸዋል - እነቀልጣፊት ምግብ ቤቶችን። አዎ! ቢበሉት ሆድ የማይጐረብጥ፣ ጠዋት ቀምሰው ቀኑን ሙሉ ተቆልፈው የሚውሉበት ምግብ የሚዘጋጅባቸውና “ቀን የሠራኸውን ባንክ ክተት፣ እራት በእንቅልፍ ያልፋል” ተረትን ለሚተርቱ አባሃናዎች የሚመቹ ምርጥ ምግብ ቤቶች - እነቀልጣፊት ምግብ ቤቶች።

“ለመኖር እንጂ፤ ለመጥገብ አልበላም” ባይ ተረቶቻቸውን ይዘው የሚጓዙ ግን እንብርት እስኪጠፋ ድረስ የሚያጠግቡ፣ ለብዛት እንጂ ለጥራት ፊት የማይሰጡ ማለፊያ ምግብ ቤቶች ናቸው - እነቀልጣፊት ምግብ ቤቶች።

በነቀልጣፊት ዘንድ “ስምን መልዓክ ያወጣዋል” አይነት ንግግር ቦታ የለውም። “ስምን አጋጣሚና ደንቦች ያወጡታል” ነው ትክክለኛ አባባል። ከአጋጣሚ መካከል “ፀኃይ ግባት ምግብ ቤት”ን በዋቢነት መጥቀስ በቂ ሲሆን፣ ደንበኛ የሚያወጣቸው ስያሜዎች ግን እልፍ ናቸው። “የተቀመመች ምግብ ቤት” (በዚህ ስም የሚጠሩ ምግብ ቤቶች በየሰፈሩ የሚገኙ ይመስላል)፣ “ጣመኝ ድገመኝ ምግብ ቤት”፣ “የናት ጓዳ ምግብ ቤት”፣ “ቀልጣፊት ምግብ ቤት”፣ … ወዘተ ስያሜዎችን ይዘዋል - እነቀልጣፊት ምግብ ቤቶች።

ለጤና ጣጣ ፈንጣጣ የላቸውም። ምን አገባቸውና!? ለጤና ጤና ጣቢያ ያስብበት። የእነርሱ ድርሻ ደንበኞችን ማስደሰት ብቻ - “ደንበኛ ንጉሥ ነው” ስለሆነም እንክብካቤ ይሻል። እንደፈለገው፣ በፈለገው መንገድ የፈለገውን ነገር ማቅረብ ይሄ ነው የነቀልጣፊት የዘወትር መርኅ።

“የሽሮ ወጡ ቅጥነት ውሃን ያስንቃል” ብሎ ማሳጣት፣ “የዘንድሮ በግ እግር የለውም እንዴ?!” በማለት ቅልጥሙ የት ሄደ? አይነት ትችት መተቸት፣ “የዘንድሮ ስጐ ምስር ወጥ ሆነ እንዴ?” ብሎ ማሽሟጠጥ፣ “ፓስታ ነው ገንፎ?” ሲሉ ማሳጣት እነቀልጣፊትን ያስኮርፋል። “ስለምን?” - ደንበኞች የዋጋ ቅናሽን እንጂ ሌላ ነገር ማየት የለባቸውምና። እንደውም ለዚህ ታላቅ ውለታቸው ከደንበኞች የሚጠበቅ ውለታ አለ። ለምሳሌ የቦታ ጥበት ሊኖር ስለሚችል ተጠጋግቶ፣ ተቻችሎ መመገብ፣ ቶሎ በልቶ በመውጣት፣ ባገኘው ቦታ ላይ ተቀምጦ አጣና ወይም ቆርቆሮ አልያም ወለል ላይ ቁጭ ብሎ በመመገብ፣ መፀዳጃ ቤት ባለመጠየቅ፣ ውሀ ከሌለ ሳይጠጡና እጅን ሳይታጠቡ በመሄድ ደንበኞች መተባበር አለባቸው። ደንበኛ ለነቀልጣፊት ምግብ ቤቶች ፍቅሩን የመግለጫ መንገዶቹ እነዚህ ብቻ ናቸውና።

እነቀልጣፊት ጋር ሁሉ ነገር በሽ ነው። “ከሳር ምን ጉዳይ አለኝ?! ከወጡ በዛ አድርገው” ብሎ እንጀራን የሚያናንቅ ደንበኛ ቢኖር እንኳ፣ ያንጀቱ ሳይደርስ ከዛች ቤት አይወጣም። ሳህን ላይ እንጀራ ይነጠፍና ወጡ ጣና ኃይቅ መስሎ ይመጣለታል። ጐረድ ጐረድ ተደርገው እንደነገሩ ጣልጣል የተደረጉት ሽንኩርቶች እንደ አሳ ወጡ ውስጥ እየዋኙ ይቀርቡለታል። ኧረ ምን ጠፍቶ!

አንጀት ለራቀው፣ ጠኔ ላንጠራወዘው፣ እንብርቱን ለተተኮሰው፣ … እነቀልጣፊት እናት ናቸው። እናት። ረሃብ ቆራጭ መድኃኒቶች። ለጽድቅ እንጂ ለትርፍ ይነግዳሉ ተብለው የማይጠረጠሩ አፍቃሪ ህዝቦች። ባቅማቸው እንደ አቅማቸው ደንበኞችን የሚያስተናግዱ፣ ለደንበኛ የቆሙ ረሃብ አስወጋጆች።

ደንበኛ ገና ወደነቀልጣፊት ምግብ ቤት ሲመጣ የውዴታ ግዴታውን አውቆ መሆን አለበት ሲሉ የነቀልጣፊት ተወካዮች ያሳስባሉ። የፈለገው ነገር ቀርቦለት ተፈላጊው ቦታ ተቀምጦ ሲመገብ “በናትህ አጉርሰኝ?” በሚል ስሜት ጆሮ ግንዱ ላይ ከሚራወጡት፣ ከምግቡ ሳህን ላይ ከሚርመሰመሱት ዝንቦች ጋር ተቻችሎ ተመግቦ መውጣት አለበት። ስለምን? ቤቱ ለዝንቦቹ ቀፎአቸው ነውና። ዝንቦቹ እምግቡ ላይ ቢያርፉበት፣ የሚጠጣው ውሃ ላይ ቢንሳፈፉበት፣ “ስለፍቅር ሁሉ ነገር ይቅር!” ብሎ ቶሎ ተመግቦ መውጣት አለበት። ይህ የውስጥና የውጭ የነቀልጣፊት ደንብ ነውና። ከዚህም አልፎ “ምስሩ አልተለቀመም፣ እንጀራው ዓይን የለውም፣ ቂጣ ወይስ እንጀራ?” ብሎ ማጉተምተም፣ “ወጡ የዛሬ ሣምንት ነው?” ብሎ ቅሬታ ማሰማት ከደንበኝነት ያስፍቃል፤ ሆድም ያስሻክራል። አንድ ደንበኛ “ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባም”ን ሳይሆን (ሊገባ ይችላልና) “ዝም አይነቅዝም”ን ተርቶ ቶሎ ተመግቦ መውጣት ብቻ ነው ያለበት። ይኸው ነው ደንቡ።

በርካሹ ዘመን አልያም በውዱ ጊዜ የማይቀየር፣ የማይሻሻል፣ የማይጣል፣ የማይገነጠል የምግብ ዋጋ ዝርዝር የያዘ ወረቀት ደንበኞች ያዩት ዘንድ ከግርግዳ ላይ ይለጠፋል። የምግብ ሸቀጦች ሲወደዱ የዋጋው ወረቀት ባለበት ድልዝልዝ፤ የምግብ ሸቀጦች ከረከሱ ባሉበት ትውት ማድረግ የነቀልጣፊት የዘወትር አሰራር ነው። ይሄ ታዲያ የደንበኞችን ሆድ የሚያሻክር ጉዳይ አይደለም። “ስለምን?” - መጀመሪያውኑ እና መጨረሻውኑ የእያንዳንዱ ምግብ የዋጋ አተማመን የደንበኞችን አቅም ያገናዘበ ነውና።

“ቅሬታ ካለ ለእኛ፣ በመስተንግዶ ከረኩ ለጓደኛ ይንገሩ” የሚሉት እነቀልጣፊት ምግብ ቤቶች ሲያጠፉ - “አቤት!”፣ ሲታዘዙ - ”ምን” እያሉ ሰበር ቀንጠስ ሲሉ መቼም ለጉድ ነው። ለዚህም ቤቱ ጭር ባለበት፣ ገበያ በቀዘቀዘበት ሰዓት “ደንበኛ ያልሆነ ቤት ይበጣጠስ”ን ተርተው ለጫት መቃሚያና ለሲጋራ ማጨሻ ቤታቸውን መፍቀዳቸው ምስክር ነው።

መቼም የምግብ ሙያተኞቹ ነገር አይነሳ፤ የጣት ብቻ ሳይሆን “እግር ሲያስቆረጥም” የሚያሰኘውን ምግብ የሚያዘጋጀው ማን ሆነና!? “ከኛ ወዲያ ሙያ!” ብሎ መንቀባረር በእውነቱ አያንሳቸውም። አብሶ የዶሮ ብልት ለደንበኞች የማዳረስ ፖሊሲያቸው ከሁሉም በላይ ተደናቂ ያደርጋቸዋል።

እቤት ውስጥ የምናውቃት ዶሮ አትመስልም እነቀልጣፊት ጓዳ የምትታረደው። የነቀልጣፊት ዶሮ ልዩ ናት። እንደማንኛውም ዶሮ፣ የነቀልጣፊት ዶሮ አስራ ሁለት ብልት አላት ብሎ የሚናገር ካለ፣ በእውነት እርሱ አላዋቂ ነው። የነቀልጣፊት ዶሮ ብልት ሃያ አራት እና ከዚያም በላይ ያላት ናት። “ይሄ የሆነው ትርፍን ለማጋበስ ተብሎ የተደረገ ነው” የሚል ካለ አሁንም እርሱ ተሳስቷል። “ስለምን?” - ይህ ይሆን ዘንድ የሚያስገድደው የነቀልጣፊት የዶሮ ብልትን ለብዙ ደንበኞች የማዳረስ ፖሊሲ ነዋ! ምን አዲስ ነገር አለው!? ሙያ ይሏችኋል ይሄ ነው። “ይባረኩ እቴ! ለዘላለም ይኑሩ!” ያንድ ደንበኛ ውዳሴ ነበር።

ስለነቀልጣፊት መስተንግዶ፣ ምግብና አጠቃላይ ሁኔታ ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል። ነገር ግን ለዛሬ በዚህ ቢበቃን የተሻለ ይሆናል። “ለመጥገብና ለመዝናናት፣ ወደነቀልጣፊት ብቅ ማለት!”፣ “ወደነቀልጣፊት ሲሄዱ፣ ቀና ነው መንገዱ!” - ጨረስኩ።

ወደ ኪነጥበብ ገጽ መልሰኝ      ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

Hosted by www.Geocities.ws

1