ወደ ኪነጥበብ ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

መፀዳጃ ቤቶቻችን

በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር

"'ዎክ' መብላት ከሰለቸህ፣ አንድ ቦታ መቀመጥ ከታከተህ፤ ጊዜን አንቆ መግደያ ኃይለኛ ቦታ አለ - እርሱም የህዝብ መፀዳጃ ቤት ነው"

 

ከአንድ የቅርብ ባልንጀራዬ ጋር ሻይ ይዘን ጨዋታ እየተጫወትን ሳለን፣ ጨዋታን ጨዋታ ጐተተውና "መፀዳጃ ቤት ስቀመጥ የሚሰማኝ ደስታ ለጉድ ነው!" ሲል አጫወተን። እኔም ነገሩ ግልጥ አልነበረልኝምና "ምኑ ነው ደግሞ እርካታ የሚሰጥህ?" ስል በግራሜ ጠየኩት። እርሱም "በቃ! መፀዳጃ ቤት ስቀመጥ አንዳች የእርካታ ስሜት ውስጤን ይሰማኛል፤ ሰውነቴም ዘና ይላል" አለኝና እርፍ። "ጉድ ሳይሰማ ሌላ መስከረም አይመጣም" አሉ። ባልንጀራዬ እውነት ምን ነካው? በጨጨ እንዴ? በሱ ቤት'ኮ እንደ ሰሞነኛው ማስታወቂያችን "እራስን ለማደስ፣ ለእርካታ መፀዳጃ ቤት መጐለት!" መባል አለበት ነው የሚለው። ... ባይባልም ብሏል። እኔ በበኩሌ የዚህን ሰው ሃሳብ በጽኑ እዋጋለሁ። ለመሆኑ እናንተስ?

ኧረ! ምን አገባኝ - ሆሆ! የዘንድሮ እርካታ መሸመቻዎቻችን አንድ ሺ አንድ ናቸውና በጥያቄ ብዛት ለምን አዕምሮዬን እነካለሁ? መልሱን እናንተው እንዳሻችሁ፣ ቢሻችሁ መልሱት፣ ካልሆነም ተዉት። እኔ ግን "በሰበቡ መምሬ ተሳቡ" ነውና ስለከተማችን አዲስ አበባ መፀዳጃ ቤቶች ትንሽ ልጠርቅ።

"'ዎክ' መብላት ከሰለቸህ፣ አንድ ቦታ መቀመጥ ከታከተህ፤ ጊዜን አንቆ መግደያ ኃይለኛ ቦታ አለ - እርሱም የህዝብ መፀዳጃ ቤት ነው" ይላሉ የመፀዳጃ ቤቶቹ የቅርብ ደንበኞች፣ የሽንት ቤት ወረፋ ጠባቂ መብዛትን ሲያነሱ። "እንዲያውም ..." ይላሉ እነዚሁ ደንበኞች "እንዲያውም አንዳንዱ ተጠቃሚ ውስጥ ቪዲዮ የተከፈተለት ይመስል ከተጐለተ የማይነሳ፣ የራሱን የግል ሃሳብ ሲቋጥር ሲፈታ መፀዳጃ ቤት ውስጥ መሆኑን የሚዘነጋና ተረኛው ባለወረፋ በሩን ካልደበደበ በጭራሽ ቦታ የማይለቅ ስለሆነ፣ መፀዳጃ ቤቶች ጊዜ ማሳለፊያ ቦታዎች ናቸው ቢባሉ አያንሳቸውም" ይላሉ ሲያሞካሹ።

የውስጥ ደንበኞችም (የቅርብ ሳይሆኑ) "በመፀዳጃ ቤቶች ፍቅር ነወለልን" ባዮች ናቸው። ስለምን? መፀዳጃ ቤት ማለት ለእነርሱ የተወጠረን ፊኛ ማስተንፈሻ ብቻ ሳይሆን፣ ሻወር መውሰጃ፣ ካልሲና ኮፍያ ማለቅለቂያ፣ በጥቅሉም የግል ንጽህና መጠበቂያ ማለት ነውና።

እዝጊሐር ይስጣቸውና ለወንደላጤውና ለአንዳንድ ችኩል አባወራ፣ "አማን አውለኝ!" መባያ፣ ያደረ ፊትን ማለቅለቂያ ማን ሆነና!? እንደውም ወንደላጤዎች "የውበት ሳሎናችን" ቢሉት የተሻለ ነው የሚሆነው።

"እንዲህ እየሆነ ብናመሰግናቸውም ቅሉ ባመሰገነው አፋችን የምናማርርበት ጊዜም አለ" ይላሉ ደንበኞች። "እዚህ ጋ መሽናት ክልክል ነው! ከመቶ ሜትር በኋላ መፀዳጃ ቤት አለ" የሚል ማስታወቂያ በአንዳንድ ቦታዎች ይለጠፍና ቀስቱን ተከትለን መቶ ሜትር ብቻ ሳይሆን ሁለት መቶ ሜትር ብንጓዝ ሽንት ቤት አይገኝም። እርግጥ ሽንት ቤቱ ተዘግቶ ሊሆን ይችላል። ይሄ ደግሞ እኛን ደንበኞች አበሳጭቶናል። ... "ኧረ! ለመሆኑ ማንን ለማጓጓት ነው?" ይላሉ ደንበኞች በምሬት።

ሌላም ደንበኞችን በኃይል የሚያስኮርፍ፣ ለንቦጭ የሚያዘረግፍ ችግር በመፀዳጃ ቤቶች አካባቢ ይታያል። "እድሳት ላይ ነው" ተብሎ በላዩ ላይ ሁለትና ሦስት ፎቅ ይቀጠልበት ይመስል ከግማሽ ዓመት እስከ ሙሉ ዓመት ከአገልግሎት መስጠት የታቀበ መፀዳጃ ቤት በየሰፈሩ ሳይገኝ አይቀርም "ውሃ የለም" ተብሎ ደጃፉ በቁልፍ የተከረቸመውም እንዲሁ እልፍ ነው። የሚገርመው በሩ ተከፍቶ አገልግሎት ሲሰጥ የበርሜሉ ሳያንስ የቧንቧው ውሃ እንዳሻው ሲፈስ፣ ያለደንቡ ልብስ ማጠቢያ ሲሆን ከልካይ የሌለው ግማሽ ቀን ውሃ ጠፋ ተብሎ ሁለትና ሦስት ቀን እንደተዘጋ ይውላል። ታዲያ ይሄን የታዘቡ ደንበኞች በኃይለኛው ቢያኮርፉ፣ ለንቦጫቸውን ቢዘረግፉ ይፈረድባቸው ይሆን?

የጐልማሳ ትምህርት ያጠናቀቀው፣ "ፊደል ይውደም!" ብሎ ከየኔታ የሸፈተው፣ ከዛም አልፎ ቀለሙን ልምጥጥ አድርጐ የጠጣና 'የቀለም ቀንድ' የተሰኘው የስዕል ፍቅሩ የሚቀሰቅሰው፣ ፖለቲከኛነቱ የሚታወሰው፣ የባልትና ሳይሆን የብልግና እውቀቱ የሚመጣው፣ ... በነዚሁ መፀዳጃ ቤቶች ውስጥ ሲሆን ነው። ፖሊስ አየኝ፣ ሲለዩ (ካድሬ፣ ሰላይ) ሾፈኝ ሳይሉ ሃሳብ እንደወረደ የሚደፋው እግዜር ይስጣቸውና በእነዚሁ መፀዳጃ ቤቶች ነው።

መናፈስ አሻኝ፣ ቀዝቀዛ አየር በወጉ ይድረሰኝ ባይ ካለ እስኪበቃው 'ጠገብኩ፣ ሰለቸሁ' እስኪል ድረስ እየተዝናና የመፀዳጃ አገልግሎት ማግኘት ይችላል። እግዚሐር ይስጣቸውና አንዳንዶቹ መቼ በራቸውስ በቅጡ ገርበብ ይልና!? እንደውስ ይሄም የሚሆነው በራቸው ተገንጥሎ ባይጠፋ አይደል?

መቼም ሁሉም ተመስግኖ አይዘለቅም እንጂ የመፀዳጃ ቤቶች ዘበኞችስ ለእውነት የሚሠሩት ሥራ አያስመሰግናቸውም እና ነው!? እዛችው በራፍ ላይ ካለችው ወንበር ላይ ወይም ተደላድላ በተቀመጠች ድንጋይ ላይ ቁጭ ብለው ሥራቸውን በወጉ መሥራት፣ ከደከማቸውም ማንቀላፋት፣ የሕይወት ጉዳይ ከገጠማቸውም ብን ብለው ይጠፉ ይሆናል እንጂ "በሩን ሰበርከው"፣ "ውሃውን ያለአግባብ አባከንከው"፣ ... አይነት ክፉና ደግ በመናገር አብዛኛዎቹ አይታሙም። ብቻ ቁጭ ብለው የተገኘችውን ነጠላም ሆነ ጋቢ መቋጨት፣ ወደ ጓሮ ሄደት ብለው ሰላጣይቱን፣ ካሮቲቱንና የተገኘውን ተክሎ የዕለት ደቋናን ለመሙላት ደፋ ቀና ማለት እንጂ መቼ ወደ መፀዳጃ ቤቱ ብቅ ይሉና። ይሄ ይሄ ነው ታዲያ ተወዳጅ የሚያደርጋቸው። "አይ የሥራ ፍቅር!" ተብለው እንደ አርኣያ የሚያስጠቅሳቸው።

ውይ! ... ውይ! ... ውይ! ... "ሞት ይርሳኝ!" አለ ሟቹ ሰውዬ፣ እኔን እርስት ያርገኝ! ለካ መፀዳጃ ቤቶች ለደንበኞቻቸው እንደንባብ ቤትም ያገለግላሉና። መጽሐፉ ወይም መጽሔቱ ወይም ጋዜጣው እዛው ውስጥም ባይገኝ አንባቢው ግን ይዞ ገብቶ ቁጭ ብሎ ማንበብ ይችላል'ኮ! ... ያውም እየተዝናኑ።

"አሜባ - የሆድ ሌባ"ን እያቀነቀነ፣ ሆዱ ከቦታው አፈትልኮ ይጠፋ ይመስል በእጁ ግጥም አድርጐ ይዞ፣ ያንጀቱን ጓጓታ ችሎ በትንሹ እያቃሰተ ገብቶ "እፎይ!" የሚልበት መፀዳጃ ቤት - ማን? እንዴ꺵? እንደተጠሰ በማይታወቅ መልኩ ለግለሰቦች መኖሪያነት ተሰጥቶ ቢያይ ምን ይል ይሆን?

እውነት ግን "እግዜር ሲቆጣ፣ በዝናብ ምንትስ ያመጣ" ይሆንና ፊኛዎ እንዳይሆን እንዳይሆን እንደአንዳች ነገር ተወጥሮ ቶሎ ለመተንፈስ የሱሪዎን ዚፕ ከፍተው ሲንደረደሩ ከላይ እንደተገለፀው የግለሰቦች መኖሪያ ሆኖ ቢያገኙት ምን ይላሉ? ተይህ በፊት የለመደ ነውና ነገርዬዎን ለመናፈጥ ያስቡ ይሆን?

እዝጊሐር ይስጣቸውና አንዳንድ የእርዳታ ድርጅቶችም አልፎ አልፎ በየመንደሩ፣ በየጉራንጉሩ ማለፊያ ማለፊያ መፀዳጃ ቤቶች አስገንብተዋል - ለህዝቡ። ነገር ግን "የመፀዳጃ ቤቱን ቁልፍ አግኝቶ ለመጠቀም ያለው ቢሮክራሲና ሙስና ለጉድ ነው" ይላሉ በሰፈር ውስጥ ያሉ ተጠቃሚዎች። ያም ሆነ ይህ የመፀዳጃ ቤቶች ማነስ ከመቅረፍ አኳያ 'ዲንቅ ነው!' የሚያሰኝ ተግባር ነው። ከምሬ ነው።

በመጨረሻ "ዘራፍ ወንዱ!" ባይ ፎካሪውን፣ "ጨዋ ያሳደገኝ ጨዋ የጨዋ ልጅ ነኝ!" ባይ፣ መገረዙን ለማሳየት የሚሻ ይመስል በየጥጋ ጥጉ የሚፀዳዳውን ዋልጌ እጁን ይዞ - መክሮ - ዘክ&##4654; ወደየመፀዳጃ ቤቶች ለመውሰድ በመጀመሪያ መፀዳጃ ቤቶቹ የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት በአግባቡ መስጠት ይኖርባቸዋል።

"በመፀዳጃ ቤቶች ማነስ መከራችንን አየን" ባይ ደንበኞችም ያሉትን መፀዳጃ ቤቶችንም ቢሆን የመንከባከብ የመጠበቅና እንደ ራስ የማየት ባህል ማዳበር ያስፈልጋል። ይህቺኑ ዘለላ ምክር ተንፍሼ ጽሁፌን በዚህ ቋጨሁ።

 

ወደ ኪነጥበብ ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

Hosted by www.Geocities.ws

1