ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

"እኛኮ የሄድነው ለድርድር አይደለም" ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ

(አዲስ ዜና ጋዜጣ ማክሰኞ ሐምሌ ፳፮ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ.ም.)

 

አዲስ ዜና፦ እርስዎ ቅንጅትን በመወከል ከጠ/ሚኒስትር መለስ ጋር ሲገናኙ ከፓርቲው ጋር መክረው ነው? ውይይቱስ አስቀድሞ የታቀደ ነበር?

ዶ/ር ብርሃኑ፦ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር የተደረገው ስብሰባ በድንገት የተደረገ ነው። እኛ የሚዲያ (የመገናኛ ብዙኀን) አጠቃቀምና በሚዲያ ዙሪያ ያሉት የስነምግባር መመሪያዎች ምን መሆን አለባቸው የሚሉ ረጅም ጊዜ የፈጀ ውይይት ስናደርግ ነበር። ውይይቱ ቀደም ብሎ የማጣራቱን ሂደት በሚመለከት ባደረግነው ስምምነት ላይ ለማጣራት ሂደቱ አስፈላጊ ናቸው ተብለው ከሚታመንባቸው ነገሮች አንዱ የተመቻቸ ከባቢ መፍጠር የሚለው ነበር። እዚህ ስምምነት ላይ ከደረስንባቸው ነገሮች አንዱ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኀን ለተለያዩ አስተያየቶች ክፍት የሚሆንበት ተቃዋሚዎችም በዚያ መጠቀም እንዲችሉ ማድረግ የሚለው ይገኝበታል። ይህን እንዴት እንጠቀም ሲባል "መስጠቱ ችግር አይደለም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህን መብት ሲያገኙ እንዴት ይጠቀሙበታል የሚለው የስነምግባር መመሪያ ያስፈልጋል ብለው ባቀረቡት መሠረት ይህ የስነምግባር መመሪያ የሚባለው በአውሮፓ ሕብረት አደራዳሪዎች ተዘጋጅቶ ቀርቦ በእኛ በኩል ተቀባይነት ካገኘ ወደ ከአንድ ወር በላይ ይሆነዋል። ከዚያ በኢህአዴግ በኩል ወደኋላ ሲጎተት ቆይቶ መጨረሻ ላይ በእሱ ላይ ለመነጋገር በኢህአዴግ በኩል ፈቃደኝነት አለ የሚል መልዕክት መጥቶ ለመወያየት ነው ስብሰባው የነበረው።

ከሦስት ቀን በፊትም ስብሰባ ተቀምጠን በዚያ ስብሰባ ላይ መስማማት ባለመቻሉ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ጉዳዩን ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እንነጋገርበታለን ብለው ከተነጋገሩበት በኋላ አንድ ነገር ላይ የደረሰ ይመስላል እና በዚያ ላይ እንወያይ የሚል ለኀሙስ በ11 ሰዓት ቀጠሮ ይይዛሉ።

አዲስ ዜና፦ እርስዎና ዶ/ር በየነ ጴጥሮስ ብቻ ለምን ተገኛችሁ? እናንተንስ ማን መረጣችሁ?

ዶ/ር ብርሃኑ፦ በዚህ ስብሰባ ላይ ሁሌም ስንገኝ የነበርነው ቅንጅቱን ወክዬ እኔ ነኝ፣ ኅብረቱን ወክሎ ዶ/ር በየነ ናቸው። ያን ዕለትም የተጠራነው እኛ ነበርን። እዛ ከመሄዳችን በፊት ወደ 9 ሰዓት ገደማ ስልክ ተደውሎ ምናልባት ይህ ስብሰባ ጠ/ሚንስትር ቢሮ ሊሆን ይችላል፤ ጠ/ሚንስትሩ በጉዳዩ ላይ መሣተፍ እንደሚፈልጉ ተነግሮኛል እና ለማንኛውም ገና እርግጠኛ አይደለንም፤ በ11 ሰዓት ኑና ከዚያ በኋላ ውይይቱ ከእርሳቸው ጋር ከሆነ እዛ ነው የምንሄደው ብለው ይነግሩናል። ስለዚህ በዚህ መሠረት በሚዲያው ጉዳይ ለመነጋገር በ11 ሰዓት ሄደናል። ያን ጊዜ ከሣቸው ጋር ያለው የውይይት ፕሮግራም ስለተረጋገጠ ወደዚያ ነው የምንሄደው ተብለን ተያይዘን ሄድን።

አዲስ ዜና፦ ምንም ዝግጅት ሳታደርጉ ከአንድ የአገር መሪ ጋር መነጋገር (ጠ/ሚንስትሩ እንደ ፓርቲ መሪ ይሁን እንደ አንድ የአገር መሪ ያናገሯችሁ አላውቅም) በዚህ ሁኔታ መሄዳችሁ በፓርቲያችሁ በኩል ችግር አይፈጥርም ወይ?

ዶ/ር ብርሃኑ፦ እኛ እኮ ለድርድር አይደለም የሄድነው። የድርድሩ ነጥብ የሚዲያ አጠቃቀምን የተመለከተ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ከፓርቲያችን ጋር ተነጋግረን ነው በአጠቃቀሙ ላይ የተነሱትን ነጥቦች ተማምነንባቸው ነው ወደዚያ የሄድነው። በዚያ ላይ ለመፈራረም እንደምንችል ተነግሮኝ ነው የሄድኩት። እና ስንሄድ አጀንዳ ነው ብለን ያሰብነው ይህን ነው። መጀመሪያም የተወያየነው በዚህ ላይ ነው። ከዚያ በኋላ የተነሳ ነገር ቢኖር ለውይይት እንጂ ለድርድር አይደለም።

አዲስ ዜና፦ ከሚዲያ ባሻገር በሌሎች ጉዳዮችም እኮ ተነጋግራችኋል? እንዲያውም እርስዎ፣ ዶ/ር በየነና ጠ/ሚንስትሩ እንዲህ ተባባሉ ተብሎ ጋዜጣ ላይ ተጽፏል እኮ?

ዶ/ር ብርሃኑ፦ አንተ መጀመሪያ የጠየቅኸኝ ከፓርቲው ጋር ስላገኘነው ፈቃድ ነው። ለዚህ ነው መልስ የሰጠሁት። ከዚያ በኋላ በተነሱት ጉዳዮች ላይ ለድርድር አይደለም የሄድነው የምንደራደረው ነገር የለም። በኢህአዴግ በኩል ያለውን የምርጫ አቋም እንንገራችሁ ብለው ነው የነገሩን። እና እሺ ወይም እምቢ የምንለው ነገር አልነበረም። እንዳልከው ድርድር ውስጥ የሚገባ ከሆነ በምንም ጥያቄ ላይ ከፓርቲው ጋር ተነጋግረን የፓርቲውን አቋም ይዘን ነው ሂደን የምንከራከረው። ስለዚህ እኛ ኃላፊነት የነበረን በሚዲያው ላይ ለመነጋገር ነው፤ ከዚያ ውጭ ግን ለመስማትና ምናልባት ለፓርቲያችን ግልፅ ማድረግ ያስፈልጋል ብለን የምናስባቸውን ጥያቄዎች ከማንሳት ውጭ ሌላ የምናደርገው ነገር አይኖርም። ያውም እንዲህ በድንገት በተጠራ ስብሰባ ላይ።

አዲስ ዜና፦ ኢህአዴግ ያቀረባቸው አቋሞች ይታውቃሉ?

ዶ/ር ብርሃኑ፦ እንዳልኩት በሚዲያው ላይ የተነሱትን ጥያቄዎች በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ከጨረስናቸው በኋላ አምባሳደር ቲም ክላርክ ይህ ስብሰባ በዋናነት በሚዲያው ላይ እንደሆነ ተናገሩ። ከዚያ በኋላ ሌሎችም ጉዳዮች ካሉ ውይይት የሚያስፈልጋቸው በእኔ በኩል እናንተ ወስናችሁ መነጋገር ትችላላችሁ ብለው ነው ውይይቱን የጀመሩት።

በዚያ ላይ በኢህአዴግ በኩል የቀረበው ይኸ ነገር በተግባር የመዋሉና ያለመዋሉ ጉዳይ በምርጫው ሂደት ላይ የተቃዋሚዎች አቋም ምን እንደሆነ ሲታወቅ ነው። እስካሁን ድረስ ተቃዋሚዎች በሂደቱ ውስጥ መኖርና አለመኖራቸውን ግልፅ እያደረጉ አይደለም። እና ግልፅነት ሊኖር ይገባል። እስካሁን ድረስ እርግጠኛ ባልሆነ ምርጫው ውስጥ መሆናችሁ በማይታወቅ መልክ እየተንቀሳቀሳችሁ ነው። አሁን ይህንን የመወሰኛችሁ ጊዜ ደርሷል። በዚህም ከሚዲያው ጋር በተያያዘ የሚወሰነው በዚህ ጉዳይ ላይ ያላችሁን አቋም ጥርት ባለ መልክ ብታቀርቡ ነው የሚል ጥርት ያለ መመሪያ ቀረበልን።

አዲስ ዜና፦ ይህ የቀረበው ጠ/ሚንስትሩ ባሉበት ነው?

ዶ/ር ብርሃኑ፦ አዎ! ጠ/ሚንስትሩ ናቸው ያቀረቡት። ይህን ካቀረቡ በኋላ ያላችሁን አስተያየት አቅርቡ ነው የተባልነው። እና በዚያ ላይ እኛም አስተያየታችንን አቀረብን። በአጠቃላይ የነበረው አስተያየት ግልፅ የሆነ ነገር መኖር ለሁሉም ይጠቅማል። ግልፅ ባልሆነ መንገድ መሄድ ሁኔታውን ወደ አስቸጋሪ መንገድ ነው የሚከተው። ለአገሪቱም አይጠቅምም። ነገሩ መዘግየቱንም እናውቃለን። ሆኖም ግልፅ መሆን ያለበት የምርጫውን ውጤት መቀበል አለመቀበል ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የጨዋታው ሂደትና ሕግ ምን እንደሆነ ለሁሉም ግልፅ መሆን አለበት።

በእኛ በኩል በአገሪቱ ውስጥ ባሉት ሕጎች (ሕገ መንግሥቱን) ጨምሮ ለመዳኘት ወደጨዋታው መግባታችን ምንም ጥያቄ የለውም። መለወጥ ያለባቸው ነገሮች በሕገ መንግሥቱ ውስጥ እንዳሉ እናምናለን። እነዚህን ግን ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ለመቀየር ብለን በማኒፌስቶአችን አስቀምጠናል። ችግሩ ያለው ኢህአዴግ ሕጎችን አላከብር እያለ በማስቸገሩ ነው። በዚህ ሁኔታ የጨዋታው ሕግ ለሁላችንም ግልፅ አይደለም። ያለአግባብ ማሰር ሕገ መንግሥቱ ክልክል ነው ይላል። ኢህአዴግ እንደፈለገ ያስራል። ሕጉ የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ መሆን አለበት ይላል። ቦርዱ ግን ገለልተኛ አልሆን ብሎ ማስቸገሩ ነው ምርጫውን ችግር ውስጥ የከተተው ብለናል። ስለዚህ አንድ መንግሥት ሕግ ሲያወጣ በቅድሚያ ራሱ መገዛት አለበት የሚል ሃሳቦች ነው በኛ በኩል የቀረበው። በነኚህ ዙሪያ ብዙ ውይይት ተካሂዷል። ግን ውይይቶች ናቸው። በርግጥ ለሁሉም አመቺ የሆኑ የመጫወቻ ሜዳዎችን ማበጀት አለብን ያለበለዚያ ዝም ብሎ ለአንዱ የሚሰራ ለሌላው የማይሠራ ሕግ ባለበት ጨዋታው በትክክል ይካሄዳል ማለት በጣም ከባድ ነው የሚል አስተያየት ነው ያቀረብነው።

አዲስ ዜና፦ አንዳንድ ወገኖች እናንተ ሳትዘጋጁ ሄዳችሁ እነሱ የፖለቲካ ድል ለማግኘት ተጠቀሙባችሁ ይላሉ። ከአጀንዳችን ውጪ አንነጋገርም ብለው መውጣት ነበረባቸው የሚሉ ወገኖችም አሉ? እርስዎ በዚህ ይስማማሉ።

ዶ/ር ብርሃኑ፦ እኛ እኮ ምንም የሚያዘጋጀን ነገር አልነበረም። እንዳልኩህ በሚዲያ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር ተጠራን። ተነጋገርን። ከዚያ በነሱ በኩል የሚያስፈልጉ ነገሮች ብለው አቀረቡ። ለዚያ ምንም የተለየ ነገር የሚፈልግ አልነበረም። ይህንን በሌላ ሰው ማድረግ ይችሉ ነበር። ጉዳዩን የጀመረው አቶ በረከትም ሲለው የነበረው ነው። ከጠ/ሚኒስትሩ እንድንሰማ ተፈልጎ ካልሆነ በቀር የተለየ ነገር አልነበረውም።

እና መወያየት እንፈልጋለን ስትባል እምቢ አትልም፤ ድርድር ውስጥ እንግባ ከተባለ ቀጠሮ ተይዞ በጉዳዩ ላይ ሁሉም አቋሙን ይዞ በዚያ ላይ ውይይት ይደረጋል። ምናልባት በአውሮፓ ሕብረት በኩል እንደበጎ ነገር የታየው ሌሎች ድርድሮችም ይኖራሉ ማለት ነው፤ ለውይይት ፍላጎቱ አለ ማለት ነው የሚል ሊሆን ይችላል።

አዲስ ዜና፦ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጦላችኋል? በጽሁፍ የደረሳችሁ ነገር አለ? በምርጫው ውስጥ መኖርና አለመኖራችሁን ታሳውቃላችሁ?

ዶ/ር ብርሃኑ፦ በመጀመሪያ ኢህአዴግ እንደፓርቲ እንዲህ አይነት ቅድመ ሁኔታ መስጠት አይችልም። እዛ ላይ ኢህአዴግ የተወከለው እንደ ፓርቲ ነው። እሱም በግልፅ ተነግሮናል።

ኢህአዴግ እንደኛ ተወዳዳሪ ፓርቲ ነው። አንድ ተወዳዳሪ ፓርቲ ለሌላ ተወዳዳሪ ፓርቲ ቅድመ ሁኔታ (ግዴታ) (Ultimatum) የሚሰጥበት ሁኔታ የለም። ጉዳዩ የሕግ ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ የፖለቲካ ድርድር ማድረግ ከሆነ በነኚህ ጉዳዮች ላይ መደራደር እንፈልጋለን ተብሎ ድርጅቶች አቋማቸውን ይዘው ነው መደራደር የሚቻለው። ለዚያ የሚሆን አዎንታዊ ምልክት አለ የለም የሚለውን ለማወቅ ከባድ ነው። በዚያ ላይ ውይይት ይኖራል አይኖርም የሚለው አይታወቅም።

ሌላው ደግሞ አንድ አገር እንዲህ አይነት የፖለቲካ አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ጊዜ በማስጠንቀቂያ መፍትሔ ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም። ይህንን በሚመለከት እዛው ውስጥ የነበርነው ሰዎች ተናግረናል፤ በእውነት እዚህ የተጠራነው ይህን ማስጠንቀቂያ ለመቀበል ከሆነ ጠቃሚ አይደለም። ችግሩን ወደ መፍታት አይወስድም። ግን ሠላማዊ የፖለቲካ መፍትሔዎች ምንድን ናቸው የሚለውን ለመነጋገር ከሆነ የገባንበትን አጣብቂኝ የምንፈታበት መንገድ ሊኖር ይችላል። በሁላችንም በኩል መተማመን ከጠፋ የእያንዳንዳችንን መጥፎ ነገር ወደ ጎን ትተን መልካም ነገሮችን ማሰብ እንችላለን። ምናልባት በኢህአዴግ በኩል ለተቃዋሚዎች ፍርሃት ይኖረው ይሆናል። ይህን ፍርሃት እኛ መረዳት አለብን። በእኛ በኩል ከሕገ-መንግሥቱ ጋር በተያያዘ ግልፅ ያላደረግነው ካለ እናደርጋለን። በኢህአዴግ በኩልስ ምን ያህል ለዲሞክራሲ ዝግጁነቱ አለ? የሚለውን ግልፅ እንዲያደርግ እንፈልጋለን። በነዚህ ፍርሃቶች ላይ መነጋገር ገንቢ ነገር ነው።

አዲስ ዜና፦ አሁን ነገሮች እየከረሩ የመጡበት ሁኔታ ያለ ይመስላል። ኢህአዴግ በፓርቲነቱ ይህን ማስጠንቀቂያ አቅርቧል። ፓርቲው ያቀረበው ስለሆነ አልተቀበላችሁትም፤ ይህንኑ ዘወር አድርጎ በምርጫ ቦርድ ወይም በመንግሥት በኩል ቢያቀርበው ትቀበሉታላችሁ?

ዶ/ር ብርሃኑ፦ ፓርቲውም ሆነ ምርጫ ቦርድ እንዲህ ብሎ የሚያስገድደን ነገር የለም። እኛ የመሰለንን ከመናገር የሚከለክለን ነገር የለም። አንዱ ችግር ምርጫ ውስጥ ነህ አይደለህም የሚለው በራሱ ግልፅ አይደለም። ውስጥ ናችሁ ወይም ውጭ ናችሁ ሲባል ምን ማለት ነው?

እኔ እስከሚገባኝ በጨዋታው ሕግ ውስጥ ነህ ማለት በአገሪቱ ሕግ መገዛት ማለት ነው። ያንን በሚመለከት በግልፅ አስቀምጠናል። ሕገ መንግሥቱ ሠላማዊ ሠልፍ ማድረግን ይፈቅዳል። ያንን ተቀብሎ ምርጫው ተጭበርብሯል ቢል ከጨዋታ ውጭ ነው የሚያስብለው ነገር የለም። እኔም ያልገባኝ በነሱ በኩልም ግልፅ ያልሆነላቸው የመሰለኝ በጨዋታው ውስጥ ማለት እነሱ በሚፈልጉት መንገድ እስከተሄደ ድረስ ብቻ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ስህተት ነው። ሕገ መንግሥቱ የተጠቀሱትን ነገሮች እስከተጠቀምክ ድረስ ጨዋታ ውስጥ ነህ፤ ግን ውጤት አንቀበልም ማለት ከጨዋታ ውጭ ነው ብሎ ማለት ትክክል አይደለም። ይልቅስ ከጨዋታ ውጭ ማለት ሕገ መንግሥቱን እያፈረሱ መሄድ ነው። በእሱ ከሆነ ከማንም በላይ ተጠያቂውና ከጨዋታው ውጭ የሆነው ኢህአዴግ ነው። የራሱን ሕገ መንግሥት የማያከብር፣ በሕጋዊ መንገድ ጨዋታ ውስጥ የገቡ ሰዎችን ማሰር፣ ማዋከብ ነው ከጨዋታ ውጭ ነው የሚያስብል።

በኢትዮጵያ የደህንነት ተቋማት በፖለቲካ ትግል ውስጥ መግባት የለበትም ይላል፤ ግን እየገቡ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን መመርመር አለብን። እየገቡ ከሆነ ከጨዋታ ውጭ ናቸው። እና እነዚህ ነገሮች ናቸው በቂ ውይይት የሚያስፈልጋቸው።

አዲስ ዜና፦ ሦስት ያክል አማራጮች ቀርበውላችኋል። አንዱ ስደት፣ ሁለተኛው አርፎ መቀመጥ፣ ሦስተኛው ጫካ መግባት ይመስለኛል። ይህ በእናንተ ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል?

ዶ/ር ብርሃኑ፦ እሱ እኛ ላይ የፈጠረው ምንም ተጽዕኖ የለም። እኛ ሕገ መንግሥቱን እናከብራለን ስንል ለቀልድ አይደለም። ሕገ መንግሥቱን አንቀበልም ካላችሁ ከጨዋታው ወጥታችኋል፣ ከወጣችሁ ደግሞ ማንም እንደሚያደርገው ወይ ወጥቶ ጠመንጃ ይያዛል፣ ወይ ተሰዶ አገር ለቆ ይሄዳል፣ ወይ አንገቱን አቀርቅሮ እዚሁ ይኖራል የሚሏቸው ሦስት አማራጮች ሕገ መንግሥቱን አንቀበልም ላሉ ኃይሎች የሚቀርብ ነው። እኛ ሕገ መንግሥቱን ተቀብለን ነው በሠላም የምንንቀሳቀሰው። የወከሉንም በሠላም ድምፃቸውን የሰጡ ናቸው። ከዚያ ስለመውጣት ከኛ ጋር ሊያወሩ አይችሉም። መሠራት ያለበት በሕገ መንግሥቱ ውስጥ መሆንና አለመሆን ሳይሆን፣ ሕገ መንግሥቱን ማክበርና አለማክበር ላይ ነው። በኛ እምነት ሕገ መንግሥቱን የማያከብረው መንግሥት ነው።

አዲስ ዜና፦ እየተካረረ የመጣውን ሁኔታ እንዴት ነው መቅረፍ የሚቻለው?

ዶ/ር ብርሃኑ፦ ሁኔታው አጣብቂኝ ውስጥ እየገባ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። ከዚያ አጣብቂኝ ውስጥ በሠላም የሚወጣበትን መንገድ መፈለግ የአገሪቱ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል ሁሉ ሊያስበውና ሊጨነቅበት የሚገባ ይመስለኛል። ከምንጊዜውም በላይ የሰከነ የፖለቲካ አመራር ትዕግስትን የተላበሰ አካሄድ፣ የፖለቲካ ውሳኔ ቁርጠኝነት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የአገርን ሠላም ከጊዜያዊ የፖለቲካ ስልጣን በላይ ቅድሚያ ሰጥተው መንቀሳቀስ የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው። ከምንጊዜውም በላይ ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ ከዚያ ውጭ ያሉት ሁሉ ከገባንበት አጣብቂኝ ለመውጣት መፍትሔ መፈለግ አለባቸው።

በእርግጥም መፃኢውን ጊዜ ጠንካራ ስርዓት ገንብተን የምንሄድበትን ጊዜ መፈለግ አለብን። በማስጠንቀቂያ በማስፈራራት የምንሄድበት ጊዜ አይደለም።

አዲስ ዜና፦ አሁን በቀጣዩ አቋማችሁ ዙሪያ ህዝቡን ለማወያየት አስባችኋል?

ዶ/ር ብርሃኑ፦ በኛ እምነት አካሄዳችን ከአሁን በኋላ ከህዝቡ ጋር በሚደረግ ሠፊ ውይይት ነው የሚመሰረተው። እንደዚሁ ቅንጅቱ ብቻ ወስኖ ይህ ነው አካሄዱ የሚልበት ሁኔታ አይፈጠርም። በዚህ ሣምንት ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እንጀምራለን። በዚህ ላይ የሕብረተሰቡን ፍላጎት ለማጤን እንፈልጋለን። በዚህ ላይ አቋም እንወስዳለን።

ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

Hosted by www.Geocities.ws

1