ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

ዶ/ር ብርሃኑ ኢህአዴግ ከውንብድና ሥራው እንዲታቀብ አስጠነቀቁ

"እሳቱ አንዱን በልቶ ሌላውን የሚተው አይደለም"

ሻለቃ አድማሱ ከመኪና ግጨደት አመለጡ

የዶ/ር መረራ ጉዲና መኪና ተሰባበረች

(አዲስ ዜና ጋዜጣ ማክሰኞ መስከረም 10 ቀን 1998 ዓ.ም.)

በአርቲስት ደበበ እሸቱ ላይ የደረሰውን ድብደባ፣ በሻለቃ አድማሱ መላኩ ላይ የተደረገውን የመኪና ግጭት ሙከራና በዶ/ር መረራ ጉዲና መኪና ላይ የደረሰውን ጥፋትና በአሁኑ ጊዜ በተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ሕይወት ላይ ያንዣበበውን አደጋ አስመልክቶ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ ዶ/ር ብርሃኑ በሰጡት ሰፊ መግለጫ ኢህአዴግ ከውንብድና ተግባሩ በአስቸኳይ እንዲታቀብ አስጠንቅቀዋል።

ሰሞኑን በተቀናቃኝ ፓርቲ አመራሮች ላይ እየደረሰ ያለውን ሁኔታ እንዴት ይመለከቱታል ለተባሉት ዶ/ር ብርሃኑ ሲመልሱ "በተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ፣ በአመራሩም ሆነ በደጋፊዎች ላይ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች አንዳንዶቹን የምንሰማቸው አንዳንዶቹን ደግሞ በዓይናችን ያየናቸው ሲሆኑ፣ አገሪቱንም በጣም አደገኛ ወደ ሆነ መስመር የሚከቱ ናቸው። ይህ ምርጫ ከተካሄደ ጊዜ ጀምሮ በኢህአዴግና በመንግሥት እየተወሰደ ያሉ እርምጃዎችን በጥሞና ያየ ሰው ይህ ምርጫ አዲስ ነገርን ይዞልን መጥቷል፣ ሰብዓዊ መብቶች የበለጠ የሚከበሩበት፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈሩት የተለያዩ ድንጋጌዎች ተግባራዊ የሚሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል በሚል መንፈስ ኢህአዴግ እየተረጎመ እንዳልሆነ ይረዳል"

"ኢህአዴግ ይህን ምርጫ በማድረጉ የተፀፀተ፣ የዴሞክራሲ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓት ለዚህች አገር አይሠራም ብሎ የወሰነ እና የማያውቀውንና የለመደውን ጉልበት በመጠቀም ስልጣን ላይ ለመቆየት የወሰነ ነው የሚመስለው። በተደጋጋሚ የምናየው ራሱ የሰጠውን ሕገ መንግሥታዊ ደንቦች ራሱ እየሻረ አንድ ተራ የወንበዴ ቡድን የሚሠራውን ሥራ የሚሠራ ነው የሚመስለው፤ የተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅት ቢሮዎችን ጥቂት ያፈነገጡ ናቸው የሚባሉ ሰዎችን ይዞ፣ እነሱን መሣሪያ አስታጥቆ፣ በመሣሪያ ኃይል ቢሮዎችን እንዲይዙ አድርጎ፣ አካባቢውን በደህንነቶች እንዲከበቡና ሌሎች አባሎች ደግሞ እንዳይገቡ ወይም ከገቡም ይህንን ወገን ደግፉ ካልደገፋችሁ እርምጃ እንወስዳለን በማለት መደብደብ ማስፈራራቱን የመንግሥት ኃይል ነው የሚወስደው ሲባል ማንም የሚያምን አይኖርም። የመንግሥት ኃይሎች ይህን እየወሰዱ እንደሆነ ግን በቂና ሙሉ ማስረጃ አለን። ተቃዋሚዎችን መረጣችሁ ተብሎ በየክልሉ የሚደረገውን ወከባ ስናይ፣ ስብሰባዎች እንዳይደረጉ ሲከለክል፣ ሠላማዊ ሠልፍ መጥራት ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው ብሎ ሲናገር ይህ መንግሥት ችግሩን አደገኛ ወደሆነ ሁኔታ እየወሰደው መሆኑን ያሳያል። ይህ አገር ሠላም እንዲኖረው ካስፈለገ መፍትሔው ሕገ መንግሥቱን ማክበር ነው። ይህ ደግሞ ከማንም በፊት የሚጠበቀው ከመንግሥት ነው። ይህ መንግሥት ይህን አይደለም እያደረገ ያለው። ኅብረተሰቡን የበለጠ ማበሳጨት፣ የበለጠ መግፋት ነው የተያያዘው። ይህንንም ኅብረተሰቡ እንዲገነዘብና ይህ አደገኛ አካሄድ ለማንም የማይጠቅም መሆኑን ኢህአዴግ ተገንዝቦ ከዚህ የውንብድና ሥራ ቢታቀብ ለሁሉም ይጠቅማል። እንዲህ አይነት ነገር ሲደረግ አላየንም ብለው ዓይናቸውን ከሚጨፍኑና ጆሮአቸውን ከሚደፍኑ ይልቅ ኢህአዴግ ውስጥ ያሉ በአምክንዮ (ሎጂክ) የማይምኑ እንዲህ አይነት ነገር አደገኛ መሆኑን አውቀው በድርጅታቸው ውስጥ ያሉትን በኃይልና በአመፅ መፍታት የሚፈልጉትን ተዉ ቢሏቸው ይጠቅማል" ብለዋል።

አሁን እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች በኢህአዴግ ለመፈፀማቸው ምን ማስረጃ አላችሁ ለተባሉት ዶ/ር ብርሃኑ ሲመልሱ "በኦብኮ ቢሮ የተወሰደው እርምጃ በደህንንነት የተቀነባበረ ለመሆኑ ምንም የሚደብቀው አይደለም። የደህንነት መኪኖች የደህንነት አባሎች ቆመው እነሱን አይደግፉም ያሉትን ወገን ማስፈራራት መግደል የምናየው ነገር ነው። በአቶ ደበበ እሸቱ ላይ የተወሰደው ጥቃት የደህንነት መኪና አቁመው ወርደው ነው ይህንን ያደረጉት። ሻለቃ አድማሱ ላይ የተወሰደው እርምጃ ታርጋቸው በታወቁ መኪኖች የሚጠቀሙ የደህንነት ኃይሎች ለመፈፀማቸው መረጃዎች አሉ። ኢህአዴግ ከሌለበት ማን ሊኖርበት ነው? ከአሁን በኋላ ዓይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ አይሠራም። ይልቅስ ይህንን ነገር ከምር ወስደው እንዲህ አይነት ሥራ እንዲሠሩ ያሰማሯቸውን ሰዎችም መልሰው ያለውን ችግር በውይይት መፍታት ነው የሚሻለው። ይህ አካሄድ ለአገራችንም ለኢህአዴግም አያዋጣም" ብለዋል።

የኢህአዴግ ስጋት ምን ይመስልዎታል? ለተባሉት ዶ/ር ብርሀኑ ሲመልሱ "በፍፁም ግራ የገባን ይህ ነው። በኛ በኩል በዚህ በምርጫው ከተሳተፉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ሕገ-ወጥ የሆነ ሥራ እንሠራለን ያለ አንድም ኃይል አልነበረም። በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን መብቶች ሊከለክል አይችልም። መከልከል የሚችለው ሕገ መንግሥታዊው ስርዓት ቆሟል ብሎ ሲል ብቻ ነው። ያንን አዋጅ አውጆ ከአሁን በኋላ በሕገ መንግሥታዊው ስርዓት አይደለም የምንተዳደረው ያለ ቀን ነው። በሕገ መንግሥቱ የተሰጡ መብቶች ተግባራዊ ከሆኑ እፈራለሁ የሚል ከሆነ ይህንን ሕገ መንግሥት ለይስሙላ አስቀመጠው እንጂ አይቀበለውም ማለት ነው። እኛንም እነሱንም የሚገዛን ሕግ የትኛው ነው? ኢህአዴግ ጠዋት ማታ የሚጮኸው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አልቀበልም አሉ እያለ ነው። እኛ ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እናንተ አክብሩትና አገር ሠላም ይሆናል እያልን ነው። እና ከአሁን በኋላ ተራ ሸፍጥ አይሠራም። ለዚህ ችግር መፍትሔ እናመጣለን ብለው አስበው ከሆነ ተሳስተዋል። ያ ደግሞ አካሄዱ አደገኛ ነው። እንዲህ አይነት እሳት አንዴ ከመጣ በኋላ አንዱን ፈጅቶ አንዱን የሚተው አይደለም። እንዲህ አይነቱን እብደት አቁመህ ችግሩን በሠላም እንፍታው ነው የምንለው።"

ደህንነቶች የኦብኮን ቢሮ ሰብረው ሰነዶቹን እንደወሰዱ ተገልጿል። ቅንጅት ከዚህ ያገኘው ትምህርት አለ? ለተባሉት ዶ/ር ብርሃኑ ሲናገሩ "ከዚያ ሁኔታ የምንማረው የገጠመን ባላንጣ የሠለጠነና አምክንዮናዊ የሆነ መንገድ ብቻ ይከተላል ብለን ማሰብ እንደማንችል ነው። ማመን የሚያቅት የመንግሥት ሳይሆን የተራ ዱርዬ እርምጃ መውሰድ የሚችል አይነት መንግሥት እንደሆነ ነው ያየነው። በመንፈስ ለዛ እየተዘጋጀን ነው። ኅብረተሰቡም መዘጋጀት ያለበት ይመስለኛል። ምክንያቱም በውይይቱ፣ በሕገ አልዩት በሠላም የሚያምን መንግሥት አልሆን እያለ ነው። ለማንኛውም ነገር መዘጋጀት ነው። እኛ መሣሪያ የለንም። የምናውቀውና ያለን አስተሳሰባችን ነው፤ የምንፅፍበት እስክሪብቶ ነው። ከዚህ ሌላ ምንም የለንም። ትዕግስት የሚጠይቅ የትግል ስልት ነው። ሠላማዊ ትግል በአንድ ጊዜ ውጤት የሚታይበት አይደለም። ስለዚህ እነሱ ወደ ጥፋት ሲወስዱን ሲሞክሩ የለም ብሎ ኅብረተሰቡን ወደ ሠላምና ልማት ለመውሰድ መንገድ መቀየር አለብን። ለዚህ አይነት ሥራ ነው መዘጋጀት ያለብን።"

በእናንተ ላይ ኢህአዴግ አንድ እርምጃ ቢወስድ ከኅብረተሰቡ ምን ይጠበቃል? ለተባሉት ደግሞ "በእኛ ምክንያት ኅብረተሰቡ ወደማያባራ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ እንዲገባ አንፈልግም። በመንግሥት እየተደረገ ያለው ትንኮሣ፣ ሰውን የማበሳጨት አካሄድ ልክ መንግሥት ያንን የሚፈልግ ነው የሚያስመስለው። እና በግሌ የምለው ወደ ጥፋት ሊወስደን የተነሳ ኃይል ሲኖር መልሳችን ተያይዘን ወደ ገደል የሚወስድ መሆን የለበትም። ያንን የምንመልስበትን መንገድ ማመቻቸት አለብን። እና ከግብታዊነት እርምጃ ኅብረተሰቡ እንዲታቀብ እንፈልጋለን። የሰው ልጅ የሚሸከመው በደል ወሰን ይኖረዋል። ኢትዮጵያውያን በደልንና ግፍን የመሸከም ጫንቃ ወሰን የለውም ብሎ የሚያስብ ካለ ሞኝነት ይመስለኛል። የኢትዮጵያ ህዝብ ከነፃነት በስተቀር በጉልበት ከአሁን በኋላ አልኖርም ብሎ ተናግሯል። የለም ይህን ነፃነት አንሰጥህም፣ ሞተህ ተዋግተህ ነው የምታገኘው ከሆነ ይህ መንግሥት እየሰጠ ያለው መልስ፣ እንዲህ አይነቱ መልስ ጥሩ አይደለም። እሳቱ ማንን በልቶ ማንን እንደሚተው አይታወቅም ልንለው ይገባል።" ሲሉ አጠቃለዋል።

በተያያዘ ዜና ዶ/ር መረራ መኪናቸው በደህንነቶች መሰበሩን አመልክተው ለአዲስ ዜና ዘጋቢ የሚከተለውን ተናግረዋል። "ከዚህ በፊት (የኛ ሰዎች አይነቷን መለየት የቻሉ) ነጭ መኪና ኮድ 2፣ 08563 አ.አ. መኪና በሄድኩበት ትከተለኛለች። ቅዳሜ በግምት ከቀኑ በ7 ሰዓት አካባቢ ምሣ ለመብላት ወደ ጓደኛዬ ቤት አመራሁ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ መኪናዬ መሰበሯን ሰዎች ነገሩኝ። ከላይ የተጠቀሰችው መኪና እኔ መኪናዬን ያቆምኪበት ግቢ ውስጥ ገብታ ዞራ መውጣቷን በስፍራው የነበሩ ዘበኞች አረጋግጠዋል" ዶ/ር መረራ ጨምረው እንደገለፁት፤ "ማን ምን እንደሚሠራ የማይታወቅበት ሀገር እየሆነ መምጣቱን ሕዝቡ እንዲገነዘብልን" ሲሉ ጠይቀው፤ "መኪና ተሰበረ፣ ሰው ታሰረ ብለን ትግሉን የምናቆምበት ምክንያት የለም፡ ብለዋል።

ኢህአዴግ ሲፈልግ የጫካ ሕግ፣ ሲፈልግ ደግሞ የሰለጠነ የከተማ ሕግ እየተጠቀመ ነው ያሉት ዶ/ር መረራ፤ "በሕዝቡ ብሶት የተጨነቀው ኢህአዴግ ጭንቀቱን በተቃዋሚዎች ላይ ለመጫንና ከሕጋዊና ከሠላማዊ ትግሉ ገፍትሮ ለማውጣት እየተፍጨረጨረ ነው" ብለዋል።

እስካሁን በግሌ የደረሰብኝ ሕገ-ወጥ ድርጊት አልነበረም ያሉት ዶ/ር መረራ፤ አሁን ግን የአፈናው መረብ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያሳያል ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን የአውሮፓ የአምባሳደሮች ቡድን ተቃዋሚዎች ፓርላማ እንዲገቡ መጠየቃቸው ችግሩን በውል ያለመረዳታቸውን ያሳያል ያሉት ዶ/ር መረራ፤ ፓርላማ በመግባትና ባለመግባት የሀገራችን ፖለቲካዊ ቀውስ አይፈታም። እነሱ የሚያዩበት መነጽርና እኛና ሕዝቡ የምናይበት መነጽር የተለያየ ነው ብለዋል።

ለመሸነፍ ላልተዘጋጀው ኢህአዴግም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠቅመው በሔራዊ የአንድነትና የመግባባት መንግሥት ነው ያሉት ዶ/ር መረራ፤ "ተቃዋሚዎች ፓርላማ በመግባታቸው ብቻ ዘላቂ የፖለቲካ አየር ሊኖር አይችልም። ስለዚህ በአምባሳደሮችና በኛ መካከል የመናበብ ችግር አለ። ስለዚህ ፈረንጆቹ የቀውሱን መጠንና አቅጣጫ በቅጡ የተገነዘቡ አይመስለኝም" ሲሉ ተናግረዋል።

የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ የድርጅት ጉዳይ ምክትል ኃላፊ አቶ ኦልባና ሌሊሳ በበኩላቸው የሕገ-ወጦች ክትትል መቀጠሉን ተናግረዋል።

የቅንጅት ከፍተኛ አመራርና የቀድሞው ፓርላማ አባል ሻለቃ አድማሴ መላኩ በበኩላቸው ከአንድ ሣምንት ወዲህ ደህንነቶች እየተከታተሏቸው መሆኑን ለአዲስ ዜና ዘጋቢ ገልፀዋል። ሻለቃ እንደሚሉት፤ ለፖለቲካ ሥራ፣ ለለቅሶ፣ ለተስካር በተንቀሳቀስኩባቸው አካባቢዎች እየተከታተሉኝ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ምን እንዳዩብኝ የማውቀው ነገር የለም የሚሉት ሻለቃ አድማሴ "ዛሬ ደግሞ የመኪናቸውን ጡሩምባ እየነፉ፣ ሌባ ጣታቸውን እያውለበለቡ እየዛቱብኝ ነው። መኪናዬንም ለመግጨት ሙከራ አድርገው ለጥቂት አምልጬአቸዋለሁ። ዛሬ ጠዋት (መስከረም 9 ቀን) ከቤቴ ቅንጅት ቢሮ ድረስ ሦስት መኪኖች አጅበውኝ ተመልሰዋል። ከትንሽ ቆይታ በኋላ ወደ መኢአድ ጽ/ቤት ስመለስ ደግሞ አንድ መኪና ሲከታተለኝ እዚህ አድርሶኛል። አንተ እስከመጣህበት ድረስ ጽ/ቤቱ ዙሪያ ቆመው እየጠበቁኝ ነበር" ብለዋል።

መኪኖቹ ዘመናዊ መሆናቸውን የገለጡት ሻለቃ አድማሴ "መንግሥት ይሄን የመሰለ ሕገ-ወጥ እርምጃ ለመውሰድ የተገደደው ከስጋትና ከፍርሃት ተነስቶ ነው" ብለዋል።

ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

Hosted by www.Geocities.ws

1