ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

"ስልጣን በቃኝ፤ ይህ የመጨረሻ የስልጣን ዘመኔ ነው" - አቶ መለስ ዜናዊ

(አዲስ ዜና ጋዜጣ ማክሰኞ መስከረም ፫ ቀን ፲፱፻፺፰ ዓ.ም.)

ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከመጪው አምስት ዓመት በኋላ ስልጣናቸውን እንደሚለቁ አስታወቁ።

ጠ/ሚኒስትሩ ያለፈው ቅዳሜ ከሲ.ኤን.ኤን. ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ላይ እንደገለፁት መጪዎቹን አምስት ዓመታት በስልጣን ላይ ከቆዩ በኋላ ስልጣን መልቀቅ እንዳለባቸው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

የሲ.ኤን.ኤን. ጋዜጠኛ ስልጣንዎን መች ይለቃሉ የሚል ጥያቄ ያቀረበላቸው ሲሆን ጠ/ሚኒስትር መለስ "ፓርቲዬ ይበቃሃል ሲለኝ ያን ጊዜ እለቃለሁ" ቢሉም ጋዜጠኛው ሪቻርድ ኮስተር ግን "እኔ እያወራሁ ያለሁት ስለፓርቲዎ ሳይሆን ስለራስዎ ስልጣን ነው፤ እና መች ስልጣንዎን ይለቃሉ?" በሚል በድጋሚ ጥያቄ አቅርቦላቸዋል። ጠ/ሚኒስትሩም በጥያቄው የተበሳጩ በመምሰል "ፓርቲዬ ነው ይህን የሚወስነው" የሚል መልስ እንደገና ሰጥተዋል። ጋዜጠኛው በድጋሚ "አሁን የማወራው ስለእርስዎ ነው፤ ስልጣንዎን መች መልቀቅ ያስባሉ?" በማለት በአቋሙ ሲፀናባቸው "እኔ ከመጪው የስልጣን ጊዜ በኋላ እንደሚበቃኝ ይሰማኛል፤ ይህንን የስልጣን ዘመን ጨርሼ ስልጣኔን እለቃለሁ" ብለዋል።

ከምርጫው በኋላ የተፈፀመው አመጽ አስፈላጊ ነበር ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ ደግሞ "አመጹ አስፈላጊ አልነበረም፣ እስከምርጫው ዕለት በማንኛውም መስፈርት ቢለካ የምርጫው አካሄድ ምሣሌ የሚሆን ነው፤ በዚያን ጊዜ በምርጫው የታዩት ችግሮች በመርማሪዎች በግልፅ ይጣራል ብለን ተናግረን ነበር። እናም ለአመጽ የሚያነሳሳ ምክንያት አልነበረም" ብለዋል። አቶ መለስ ከመጠን በላይ ኃይል ስለመጠቀማቸው በገለልተኛ አካል ተጣርቶ የሚወሰን መሆኑን ተናግረዋል።

"ሕዝቡ አገሪቱ ለዴሞክራሲ አዲስ መሆኗን፣ ገና በማደግ ላይ ያለ ዴሞክራሲ እንደሆነ መረዳት አለበት" ያሉት አቶ መለስ በተፈጠሩት ችግሮች መደነቅ እንደሌለበት እና ችግሮችን ማሸነፉ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነገር መሆኑን ገልፀዋል።

አንድ የቅንጅት ከፍተኛ የአመራር አካል አቶ መለስ ከአምስት ዓመት በኋላ ስላላቸው ስልጣን ያስባሉ፤ ጉዳዩ መጪውን አምስት ዓመት በስልጣን የሚያቆያቸውን ድምፅ መች አገኙና የሚለው መሆን አለበት ብለዋል።

ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

Hosted by www.Geocities.ws

1