ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

ብአዴን አፈነገጠ

ኢህአዴግ ባልተረጋገጠ ስልጣን ተከፋፈለ

- የአቶ በረከት ስልጣን አልታወቀም

(አዲስ ዜና ጋዜጣ ማክሰኞ መስከረም ፫ ቀን ፲፱፻፺፰ ዓ.ም.)

የህወሓት ተቀጥላ መሆኑ በስፋት በሚታወቀው ብአዴን ውስጥ ድርጅቱን ከሞት ለመታደግ በሚል "ትግል ለኢህዴን ትንሣዔ" የተሰኘ አስኳል መፈጠሩን ውስጥ አዋቂ ምንጮች ገለፁ።

ይህ "ትግል ለኢህዴን ትንሣዔ" የተሰኘው እና የኢህዴንን ትንሣዔ ለመመለስ በሚል እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው አስኳል፣ በብሔራዊ የሥልጣን ክፍፍል ዙሪያ የህወሓት የበላይነት ወደ ፍፁም አምባገነንነት መሸጋገሩን በመቃወም ላይ ያነጣጠረ ዓላማ እንዳለው ውስጥ አዋቂ ምንጮች አመልክተዋል።

ኢህአዴግ የግንቦት/97ቱን ምርጫ አሸንፌአለሁ፣ መንግሥት መመስረት እችላለሁ ብሎ ካሳወቀ በኋላ፤ በመንግሥት ምስረታው ወቅት በአባል ድርጅቶች መሃል የስልጣን ድልድል ለማድረግ ከነኀሴ መጨረሻ ጀምሮ ዝግ ስብሰባ ተቀምጧል ተብሏል። በዚህ ዝግ ስብሰባ ቁልፍ፣ ቁልፍ የሆኑ የመንግሥት ስልጣንን የህወሓት ሰዎች እንዲይዙ መታሰቡ የብአዴን ሰዎችን አበሳጭቷቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለስልጣናቸው ፍፁም ታማኝ የሆኑ ሰዎችን በዙሪያቸው ለማሰባሰብ የሞከሩ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ አቶ አርከበ እቁባይ፣ አቶ አባይ ፀሐዬ፣ አቶ ስዩም መስፍን ከፍተኛውን ስልጣን ያገኛሉ ተብሏል። እንዲህ ካለው ቁልፍ ስልጣን የብአዴን እና የሌላ ብሔር ተወላጆች እንዲገለሉ መደረጋቸው ብአዴኖችን ለድርጅታቸው የትንሣዔ ትግል አነሳስቷቸዋል ሲሉ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ገልፀዋል።

የአማራውን ድርጅት በመወከል ከፍተኛ ስልጣን እንደሚያገኙ ሲነገርላቸው የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን የአፈ ጉባዔነት ስልጣን ታስቦላቸው እንደነበር፣ ነገር ግን ከነኀሴ መጨረሻ ጀምሮ እየተደረገ ባለው ዝግ ስብሰባ አቶ መለስ "በግል የምንፈታው ነገር አለ" በሚል ለጊዜው ከስልጣን ክፍፍል ውጭ እንዳደረጓቸው ምንጮቻችን ጠቁመዋል።

"የስልጣን ክፍፍል በብሔር ተዋፅኦ የሚሰጥ ከሆነ ከፍተኛውን ሥፍራ ማግኘት ያለበት ኦሮሞ ነው፤ ከዚያ ቀጥሎ አማራ ነው፤ የህወሓት ሰዎች ቁልፍ ስልጣን መያዝ የለባቸውም" የሚሉ "ትግል ለኢህዴን ትንሣዔ" አባላቶች ድርጅታቸውን ከአደጋ ለመታደግ የተጠናከረ እንቅስቃሴ መቀጠላቸውን ምንጮቻችን አብራርተዋል።

የብአዴን መገለል ያልተዋጠላቸው የድርጅቱ አባሎች ቢቻል የድርጅታቸውን ሕልውና እዛው ሆነው መታገልና ማስከበር፣ ካልተቻለ ተነጥለው መውጣት እንደሚፈልጉ የጠቆሙት ምንጮቻችን፣ በመጪው ዘመን የአማራ ክልል ሁለተኛ ሰው ሊሆን ይችላሉ ተብለው የተገመቱት (ስማቸውን ለደህንነት በመስጋት መጥቀስ ያልፈለጉት ግለሰብ) በምንም አይነት ከድርጅቱ ጋር ላለመቀጠል ወስነው እራሳቸውን ማግለላቸውን አክለው ጠቁመዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚህ የብአዴን ውስጣዊ ፍትጊያ ዙሪያ የዘገበው የኢትኦጵ ጋዜጠኞች ሕይወታቸው አደጋ ውስጥ እንደሚገኝ ከደህንነት የስልክ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው።

የደህንነት ሰዎች ወደ ኢትኦጵ ቢሮ ደውለው ለፀሐፊዋ ጋዜጠኞቹ በዚህ ዙሪያ እጃቸውን እንዲሰበስቡ፣ ካልሰበሰቡ በሕይወታቸው አደጋ እንደሚገጥማቸው እንድትነግራቸው አዘዋታል። የአዲስ ዜና ጋዜጣ ዝግጅት ክፍሉ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ዛቻው መፈፀሙን ከኢትኦጵ ቢሮ አረጋግጧል።

ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

Hosted by www.Geocities.ws

1