ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

የአቶ መለስና የዲፕሎማቶች ፍጥጫ

(መዝናኛ ጋዜጣ ቅዳሜ ነኀሴ ፯ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ.ም.)

ረቡዕ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን አነጋግረው የወጡት የአውሮፓ ሕብረት ተወካዮች ፊት ላይ ድንጋጤና ብስጭት ይነበብ ነበር።

አቶ መለስ ዲፕሎማቶቹን የጠሯቸው ከአራት ቀናት በፊት ሕብረትና ቅንጅት ባቀረቡት የአንድነት መንግሥት ጥያቄ ላይ ወኪሎች የወሰዱት አቋም ረቂቅ ሪፖርት ላይ ለመወያየት ነበር። ዲፕሎማቶቹ አቶ መለስን ሲያገኙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍፁም ተቆጥተው ነበር። አቶ መለስ መጀመሪያ የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ ለተደረገው ምርጫ መሳካት ላደረገው አስተዋጽዖ አመስግነው፤ እስከ አሁን ያደረጉት በቂ እንደሆነና ከዚህ በኋላ ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጣልቃ መግባት እንደሌለባቸው ሳያወላውሉ ገልፀውላቸዋል። በዚህ የአቶ መለስ ንግግር ለተገረሙት ዲፕሎማቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጣይ ግርምት ፈጣሪ ንግግሮች ነበሯቸው።

አቶ መለስ ለሕብረቱ ተወካዮች ረቂቅ ሪፖርት ፍፁም እንደተበሳጩ ከገለፁ በኋላ የአውሮፓ ሕብረት የታዛቢዎች ቡድንም ታማኝ የምርጫ ታዛቢ እንዳልሆነ ለአውሮፓ ሕብረት ተወካዮች አስረዱ። በፖርቹጋላዊቷ አና ጐሜዝ የሚመራው የሕብረቱ ታዛቢዎች ቡድን በቅርቡ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ባሳወቀው (Leak) ባደረገው የውስጥ ዶክመንት ቡድኑ በሠራው የናሙና ጥናት ተቃዋሚዎች ማሸነፋቸው ተጠቅሷል። አቶ መለስ ይህ ናሙና ጥናት የተሳሳተና ሪፖርቱም በሀሰት የተሞላ መሆኑን ለዲፕሎማቶቹ ተናግረዋል። ወኪሎቹ የአቶ መለስን ንግግር "ክው" ብለው አድምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጠሉና የታዛቢዎች ቡድኑ ተቀባይነትና ታማኝነት (Credible observer) ያለው እንዳልሆነና ለአፍሪካ አጋር አገሮችም ይህን እንደሚገልፁ በቁጣ ገለፁ። የአውሮፓ ሕብረት ወኪል አምባሳደር ቲሞቲ ረዳቶች በቅርቡ የታዛቢዎቹ ቡድኑ ለሕዝብ ይፋ የሚያደርገው ሪፖርት መንግሥትን ክፉኛ የሚወቅስ ሊሆን እንደሚችል ይገልፃሉ። "It will Be a Damning Report" ይላሉ ረዳት።

የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎች ይህን ሁኔታ ተረድተውታል። የቅንጅቱ ሊቀመንበር ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ከሁለት ቀናት በፊት በአይቤክስ ሆቴል ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሰጡት መግለጫ ላይ "አሸናፊው ፓርቲ ማን እንደሆነ የውጭ ታዛቢዎች በሚያወጡት ሪፖርት ታውቁታላችሁ" ብለዋል።

የግጭት ተንታኝ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሠር መድኅኔ ታደሰም ከመዝናኛ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ "የአውሮፓ ሕብረት በሠራው የናሙና ጥናት አሸናፊው ማን እንደሆነ ታውቋል" ሲሉ ተናግረዋል። የመንግሥት ባለሥልጣናትም ሪፖርቱ እንዲለሳለስ ጥረት ማድረጋቸውን ምንጮቻችን ገልፀዋል።

ዲፕሎማቶቹ በማስጠንቀቂያ የተሞላውን የአቶ መለስን ንግግር ከሰሙ በኋላ ቁጣቸውን መግለፃቸውንና ረቂቅ ሪፖርታቸውን እንደሚያሳትሙት መዛታቸውን ምንጮቻችን ገልፀዋል። ኀሙስ ለዕረፍት ወደ አገራቸው የተመለሱት አምባሳደር ቲሞቲ ክላርክም ሠራተኞቻቸውን ሰብስበው ከአቶ መለስ ጋር ስለነበረው ንግግር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

Hosted by www.Geocities.ws

1