ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

በብአዴን ለኢሕዴኢን ትንሣኤ ትግል ተጅምሯል

(ልሳነ ሕዝብ ጋዜጣ ዓርብ ነኀሴ ፮ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ.ም.)

በደርግማ በህወሓት ወታደራዊ ኃይል ከተመታ በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) ተብሎ ተመሥርቶ የነበረበት ሁኔታ ተቀልብሶ ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የተሳሳተ አካሄድ ለማረም በብአዴን ታጋዮች ውስጥ ሁለት ዓይነት እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን የድርጅቱ ውስጥ አዋቂ ምንጮች አስታወቁ።

ምንጮቹ እንደሚሉት "ትግል ለኢሕዴን ትንሣኤ"፣ "የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ" የተባሉ ቡድኖች በተናጠልና በቅንጅት በድርጅቱ፣ በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ ባሉ የብአዴን ታጋዮችና በኅብረተሰቡ ውስጥ እንቅስቃሴ ጀምረዋል። የሁለቱም እንቅስቃሴዎች የጋራ ሃሳብም የኢሕዴንና የብአዴን ታጋዮች አሁን ላለው አምባገነናዊና የአማራውን ሕዝብ ላገለለ እንቅስቃሴ አልታገልንምና በአካሄዳችን እርምት መደረግ አለበት" የሚል ነው።

"ትግል ለኢሕዴን ትንሣኤ" የተሰኘው እንቅስቃሴ አራማጆች "የኢሕአፓ ትክክለኛ ወራሾች መሆን አልቻልንም፡ የወያኔ ልጅ ሆነናል። ኢሕዴን ይዞት የተነሳው ዓላማ ሙሉ ለሙሉ መክኗል" የሚል ሲሆን " በአሁኑ ጊዜ ብአዴንን እያንቀሳቀሱ ያሉት መሪ ካድሬዎች በኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅምና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ለቆሙለት ዓላማ እየሠሩ መሆናቸውን እንጠራጠራለን" የሚል ነው።

በዚህ በኩል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቅሱት የማስታወቂያ ሚኒስትሩን አቶ በረከት ስምዖንን ሲሆን "የድርጅቱን ዓላማ አሳልፈው ሰጥተዋል። ከኤርትራ ተወላጅነታቸውም አንፃር አናምናቸውም" እያሉ ናቸው።

ከሦስት ዓመት በፊት ባሕር ዳር ላይ ከመከላከያ ሠራዊቱ የብአዴን ታጋዮች ጋር በተደረገ ስብሰባ "ድርጅታችን በህወኃት ስር ወድቋል። ስለአማራ ጥቅም አራማጅነትህ ማረጋገጫ እንፈልጋለን" በሚል ለአቶ በረከት ጥያቄ ቀርቦላቸው "ለመሆኑ ማነው ኢትዮጵያዊ አይደለህም ብሎ ማረጋገጫ ሊሰጥ የሚችል?" ብለው በንዴት ጥያቄውን በጥያቄ መመለሳቸውና ስብሰባውም መበተኑ ታውቋል።

"የአዲሱ ትውልድ ታጋዮች እንቅስቃሴ" የጀመሩት ደግሞ ከ1983 ወዲህ ብአዴንን በታጋይነት የተቀላቀሉ ሲሆኑ "አሁን ያለው የድርጅቱ እንቅስቃሴ ወደ አምባገነንነት አዘንብሏል። የሕዝብ ተቃውሞን በወታደራዊ ኃይል፣ በማሰርና በመግደል ለማፈን እየተንቀሳቀሰ ነው። የአሁኑን ወጣት ትውልድ እንቅስቃሴ በዴሞክራሲያዊ አግባብ ማስተናገድ አልቻለም። ለዚህ ደግሞ በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ የተወሰደው እርምጃ ማስረጃ ነው። የአሁኑ አካሄድ የዘመነ ዴሞክራሲ አካሄድ አይደለም" የሚሉ ናቸው። ኢህአዴግ የሕዝቡን ተቃውሞ "ጥቅማቸው የተነካባቸው የቀድሞው ሥርዓት ሰዎች ተቃውሞ ነው" ከማለት ውጭ ለሕዝብ ጥያቄዎች መልስ መስጠት አልቻለም ብለዋል።

የሁለቱም እንቅስቃሴዎች አባላት አምባገነንነትን እንዲገታ ቢቻል በብአዴንና በጠቅላላውም በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ካልተቻለ ደግሞ ድርጅቶቹን እለቀቁ በመውጣት የአገሪቱን ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ለማጠናከር ቆርጠው መነሳታቸውን ምንጮቹ ገልጠዋል።

በአሁኒ ጊዜ በብአዴን ውስጥ የለውጥ ሃሳብ የሚያነሳ እየታፈነ ሆለታ እስር ቤት እንደሚታጐር ለማወቅ ተችሏል።

ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

Hosted by www.Geocities.ws

1