ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

ተቃዋሚዎችን ለመበተን ኢሕአዴግ ዕቅድ ዘርግቷል

• ቅንጅትና ኦብኮ ዒላማ ሆነዋል

(ልሳነ ሕዝብ ጋዜጣ ዓርብ ነኀሴ ፮ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ.ም.)

በአሁኑ ጊዜ ዋነኛ ተቃዋሚ ሆነው የወጡትንና በ1997 ምርጫም ሠፊ የሕዝብ ድምፅ ያገኙትን ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ (ቅንጅት) እና በኅብረቱ ውስጥ ያለውን የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስን (ኦብኮን) አዳክሞ ለመበተን መታቀዱንና ለዚህም ገንዘብ መመደቡን ውስጥ አዋቂ ምንጮች በተለይ ለልሳነ ሕዝብ ጋዜጣ ገለጡ።

ምንጮቹ እንደሚሉት ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ የአማሮች፣ የቀድሞ ሥርዓት ሰዎች (ደርግ - ኢሠፓዎች) እና የጉራጌዎች ስብስብ ድርጅት ስለሆነ፣ እነዚህ ወገኖች ለፖለቲካ ሥርዓቱ ሥልጣንና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ተፃራሪ አቋም ያላቸው በመሆኑ "ቅንጅት መፍረስ ያለበት ድርጅት ነው" የሚል አቋም ተወስዶበታል።

እነዚህን ጠንካራ ተቀናቃኝ የሚባሉ ፖርቲዎችን አዳክሞ ለመበተን ከፍተኛ ገንዘብ (አንዳንዶች እስከ 5 ሚሊዮን ብር ይላሉ) መመደቡ የተጠቆመ ሲሆን፣ ሰሞኑን በሁለቱም ፓርቲዎች ላይ የሚነዛው ፕሮፓጋንዳ የዚሁ ዕቅድ አካል እንደሆነ ይገመታል።

ቅንጅትን የመከፋፈልና የማዳከሙ የቅርብ ጊዜ ግብ፣ ቅንጅት አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ ያሸነፈ ድርጅት በመሆኑ "የተከፋፈለና የማይረባ፣ ከተማይቱን ለመምራት ችሎታ የሌለው ድርጅት" አድርጐ ለማቅረብና ከተቻለም ከተማዋን በዚሁ አሳብቦ ወደ ጊዜያዊ አስተዳደር ለመመለስ መሆኑን ብዙዎች ይገምታሉ።

ኦብኮ የጥቃት ዒላማ የሆነው ደግሞ የኅብረቱ አባል በመሆኑ "ከነፍጠኞች ጋር የወገነ ድርጅት ነው" በሚል ነው። ይህም ሃሳብ ሰሞኑን ከኦብኮ ወጣት ክንፍ ወጣን ባሉ ግለሰቦች ተንፀባርቋል። ኦብኮ ከአንዳንድ በኦሮሞ ሕዝብ ስም ከተደራጁ ድርጅቶች ጋር "ፀረ-ነፍጠኛ ኅብረት" እንዲፈጥር ብዙ ግፊት ተደርጐበት ሊቀመንበሩ ዶ/ር መረራ ጉዲና ጥያቄውን ባለመቀበላቸው ሳይሳካ መቅረቱን ለማወቅ ተችሏል። የኦብኮ ቋሚ ዓላማ "ለሁላችንም የምትሆን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በጋራ እንፍጠር" የሚል ነው።

የ'ነፍጠኘ' ጥያቄን በተመለከተ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሳይቀር "የቀድሞ የነፍጠኛ ሥርዓት በአዲስ የወያኔ ነፍጠኞች ተተክቷል" የሚል አቋም እየያዙ መጥተዋል።

ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

Hosted by www.Geocities.ws

1