ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

ቅንጅትና ኅብረት የመሸጋገሪያ መንግሥት እንዲቋቋም ጠየቁ

• የማጣራቱ ውጤት ተቀባይነት የለውም አሉ

(ልሳነ ሕዝብ ጋዜጣ ዓርብ ነኀሴ ፮ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ.ም.)

በሕዝባችንና በአገራችን ላይ የሰፈነውን መጥፎ ፍርሃት ለማስወገድ፣ አሁን በአገራችን በተፈጠረው የፖለቲካ ልዩነት ምክንያት የፈጠረውን ውጥረት በማላላት መጨውን ጊዜ ለልጆቻችንና ለራሳችንም ብሩህ ለማድረግ አዲስ ፖለቲካዊ አሰላለፍ የሚጠይቅ የድርድር አማራጭ ሃሳብ አቅርበናል ሲሉ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት አመራር አባላት አስታወቁ።

አመራር አባላቱ ትናንት ማምሻውን በአይቤክስ ሆቴል በጋራ በሰጡት መግለጫ "የግንቦት 7/97 ምርጫን ተከትሎ የተከሰቱትን የምርጫ ችግሮች ለመፍታት የተወሰዱ እርምጃዎች ችግሮቹን በተገቢው መንገድ ሊቀርፉ አልቻሉም። በቅርቡ እነዚህን ከምርጫ ጋር በተያያዘ የተከሰቱትን ቅራኔዎች የማጣራት ሂደትንም ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ባለመሆኑ ተቀባይነት እንዳይኖረው አድርጐታል" ብለዋል።

ለአገራችን ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማምጣት ዋነኛው ችግር በተቀናቃኝ ፓርቲዎች መካከል መተማመን አለመኖሩ መሆኑን ጠቁመው "እያንዳንዱ ፓርቲ ሌላውን ሊጠፋ እንደሚገባ ጠላት ሳይሆን በአገሪቷ ውስጥ የሚገነባውን የዴሞክራሲ ሂደት እንደሚያጠናክር ጠቃሚና አወንታዊ ኃይል መቁጠር ይኖርበታል" ብለዋል። በተቀናቃኝ ፓርቲዎችና በሕዝቡ መካከል መተማመን እንዲፈጠርም ጠይቀዋል።

አዲስ ፖለቲካዊ አሰላለፍ ማስፈለጉን በማስመልከትም ባሰፈሩት ሃሳብ ለብሔራዊ አንድነት መንግሥት አጽንኦት ሰጥተው "በሁሉም ዓይነት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ለተዘፈቀች ለእኛ ዓይነት አገር በእውነተኛ ዴሞክራሲ ላይ የተገነባና የተረጋጋ ፖለቲካዊ አየር መስፈን አገሪቱ ለተረጋገጡባት በርካታ ማኅበራዊ ችግሮች ምላሽ ለመስጠት አስፈላጊነቱ የተረጋገጠ ነው" ብለዋል።

አዲሱ የፖለቲካ አሰላለፍ የሚኖሩትንም ባህርያት "አዲሱ አሰላለፍ ዕድሜው የተገደበ መሆን፣ በተቃዋሚዎችና በሕዝቡ ላይ የተከፈተውን ጥቃት ማቆምና ሕግን ማክበር፣ ፍትሐዊ የሥልጣን ክፍፍልን ባገናዘበ መልኩ የመንግሥት መዋቅር መፍጠር" በማለት ገልጠዋቸዋል።

"በሚመሠረተው አዲስ መንግሥትም ሦስቱ የፖለቲካ ድርጅቶች በግንቦቱ ምርጫ ባገኙት ድምፅ መሠረት የሚኒስቴርነት ኃላፊነቶችና ሌሎች ከፍተኛ የሥልጣን ቦታዎችን ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ በሚያገኙበት በልኩ ሊዋቀር ይገባል። የሚመሠረተው መንግሥት ገለልተኛ የሆነ የመገናኛ ብዙኀን ኮሚሽን፣ አዲስና ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ ያቋቋማል" ብለዋል።

እነዚህ የድርድር ሃሳቦች ተቀባይነት እንዲያገኙ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ የበኩላቸውን ግፊትና አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አድርገዋል።

አማራጩ የድርድር ሃሳብ "በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን የፖለቲካ ቀውስ በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ሌሎች ከፍተኛ የሆኑ የአገሪቱ ችግሮችን ማለትም የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር፣ እንዲሁም የዘላቂ ልማት ችግሮችን ለመፍታት ወሳኝነት አለው" ሲሉ መግለጫቸውን አጠቃለዋል።

ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

Hosted by www.Geocities.ws

1