ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

"የተለወጡ መሪዎች እንዲኖሩን እንፈልጋለን" አቶ ታምሩ ከበደ

(ጦቢያ ጋዜጣ ኀሙስ ነኀሴ ፭ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ.ም.)

በግንቦት ሰባቱ ምርጫ በአዲስ አበባ መስተዳድር ለክልልና ለተወካዮች ም/ቤት ተወዳድረው ያሸነዱ ተመራጮች ሥራቸውን በብቃት መወጣት ይችሉ ዘንድ የሚረዳ ሥልጠና በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት እየተሰጠ ነው።

ሥልጠናውን ያዘጋጁት ኢም ፐርቴክ ኢትዮጵያና ኢኒሽየቲቭ አፍሪካ ሲሆኑ የገንዘብ ድጋፍ የተገኘውም ከስዊድን የልማት ድርጅት ነው። የሥልጠናውን ዓላማ አስመልክቶ አስተባባሪው አቶ ታምሩ ከበደ ሲገልጹ "ከተማችን የተለወጡ መሪዎች እንዲኖርዋት ትፈልጋለች። በተለይ የመዲናይቱን ችግሮች በመለየት የመፍትሔ ሃሳቦችን በማመንጨት እና ለተግባራዊነቱም መንቀሳቀስ የሚችሉ መሆን አለባቸው። ለዚህ ዝግጁነት ይረዳቸው ዘንድም ይህ ሥልጠና ተዘጋጅቷል" ብለዋል።

በተለይ የሥራ ፈጠራን በተመለከተ በምሁራን የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሑፎችና ተሞክሮዎች ለተሳታፊዎች ይቀርባሉ። የችግሮችን መንስዔ በማወቅና መፍትሔ በማፍለቅ በኩል የመሪዎች ሚና በሥልጠናው ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል።

በአጠቃላይ ከነኀሴ 2 እስከ 7 በሚዘልቀው በዚህ ሥልጠና በአዲስ አበባ ቻርተር፣ በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ልማት ችግሮች፣ የአዲስ አበባ የገቢ ምንጮች፣ ዴሞክራሲያዊ አመራርና መልካም አስተዳደር በአዲስ አበባ፣ የስትራቴጂ አነዳደፍና ውሳኔ ሰጪነት፣ የኢንተርፕሪነሪያል እውቀት ለፖለቲካ መሪዎች፣ የአዲስ አበባ መስተዳድር ድርጅታዊ መዋቅር፣ ሴቶች በፖለቲካ አመራርና በሌሎችም ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ግንዛቤ እንዲይዙና ለኃላፊነታቸው ዝግጁ እንዲሆኑ ያግዛል።

ለሦስተኛ ጊዜ እየተሰጠ ባለው በዚህ ሥልጠና እንዲሳተፉ ጥሪ የተደረገው ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲሆን በስፍራው በመገኘት ተሳታፊ የሆኑት ግን የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ናቸው።

ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

Hosted by www.Geocities.ws

1