ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

«ከእንግዲህ ለጋዜጠኞች መግለጫ አልሰጥም» አቶ ልደቱ አያሌው

"መግለጫ አለመስጠቱ ጥሩ ነው" ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ

(ጦቢያ ጋዜጣ ኀሙስ ነኀሴ ፭ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ.ም.)

የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ የምክር ቤት አባልና የኢዴፓ መድህን ዋና ፀሀፊ የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው አስፈላጊ ነው ብለው የሚያምኑበት ወቅትና ሁኔት እስኪፈጠር ድረስ ለማንኛውም ጋዜጠኛ ቃለ መጠይቅም ሆነ ማንኛውንም ዓይነት መግለጫ ላለመስጠት መወሰናቸውን ገለጹ።

አቶ ልደቱ ነሀሴ 4 ቀን 1997 ዓ.ም. ለሁለትም የመገናኛ ብዙኃን በፃፉት ደብዳቤ እንደጠቀሱት ለግላቸው ሳይሆን ለህዝብ ትግል መጠናከር ይጠቅማል ብለው በሚያራምዱት አቋም በአንድ በኩል ህወሓት/ ኢሕአዴግ ለርሱ የከፋፋይነት ዓላማ ሊጠቀምበት እየሞከረ እንደሆነ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ እውነተኛውን መረጃ አግኝቶ የትግል ውጤቱን በአግባቡ ለመጠበቅ የሚችልበትን ሁኔታ እንደሌለ መረዳታቸው ለዚህ ውሳኔ አብቅቷቸዋል፣ የመግለጫው ሙሉ ቃል ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ለሁሉም የመገናኛ ብዙኃን አካላት

ከቅንጅቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊነቱ የለቀኩበትን የአቋም ልዩነት አስመልክቶ በእኔ ፍላጎት ሳይሆን በጋዜጠኞች ፍላጐት ለሚቀርቡልኝ ጥያቄዎች የግል አቋሜን ልዩነት አስመልክቶ እስካሁን ለህዝብ ያስተላለፍኳቸው ሀሳቦች እውነተኛን ትክክለኛ ስለመሆናቸው በእኔ በኩል አሁንም ጥርጥር የለኝም። ያለ አግባብ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብቴን አጥቼና በየቀኑ በብዙ የደህንነት ሠራተኞች ተከብቤ እየተንቀሳቀስኩ ባለሁበት በአሁኑ ወቅትም ያለምንም ፍርሃትና መሸማቀቅ ለሕዝቡ ጥቅምና ፍላጐት ይበጃሉ ብዬ ያመንኩባቸውን አቋሞች አራምጃለሁ።

በአሁኑ ወቅት ተቃዋሚዎች የህዝባችንን ጥቅምን ፍላጐት በሚያስጠብቅ ሳይሆን የወቅቱን የትግል ደረጃ ለብዙ ዓመታት ወደኋላ በሚመልስ አደገኛ አቅጣጫ እየተጓዝን መሆኑን በድፍረት ለመጠቆም ሞክሬያለሁ።

ነገር ግን ይህንን ለግሌ ሳይሆን ለህዝቡ ትግል መጠናከር ይጠቅማል ብዬ ያራመድኩትን አቋም በአንድ በኩል ህወሃት/ ኢሕአዴግ ለራሱ የከፋ ፋይነት ዒላማ ሊቀጠቀምበት እየሞከረ እንደሆነና በሌላ በኩል ደግሞ ህዝቡ እውነተኛውን መረጃ አግኝቶ የትግል ውጤቱን በአግባቡ ለመጠበቅ የሚችልበት ሁኔታ በአሁኑ ወቅት እንደሌለ ተረድቻለሁ። ስለሆነም አስፈላጊ ነው ብዬ የማንበት ወቅትና ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ ከዛሬ ጀምሮ በእኔ በኩል ለማንኛውም ጋዜጠኛ ቃለመጠይቅም ሆነ ማንኛውንም ዓይነት መግለጫ ላለመስጠት የወሰንኩ መሆኔን ህዝቡ እንዲያውቅልኝ በአክብሮት አሳስባለሁ።

ከዚህ መግለጫዬ በኋላ በጋዜጦችና በመጽሄቶች የሚወጡ ቃለመጠይቆችም ይህ መግለጫ ከመውጣቱ በፊት የተሰጡ መሆናቸንው አንባቢ እንዲረዳልን በዚህ አጋጣሚ አሳውቃለሁ።

ልደቱ አያሌው ነኀሴ 4/1997 ዓ.ም.

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቀደም ሲል በቅንጅቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው አቶ ልደቱ ከእንግዲህ መግለጫ አልሰጥም ማለቱ ጥሩ ነው፣ ወደ ቅንጅቱ አመራር ተመልሶ መብትና ግዴታውን መወጣትና ተግባራዊ ማድረጉን ይቀጥላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ሲሉ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ ገለጹ።

የቅንጅቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በትናንትናው ዕለት ከጦቢያ ሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ «ልደቱ ሁለት ችግር ነው ያለበት፣ አንደኛ የብዙኃኑን አቋም ባለመቀበል አላስፈላጊ የሆኑ መግለጫዎች ማውጣቱ በህዝብ ዘንድ ውዥንብር መፍጠሩ ችግር ፈጥሯል። ከቅንጅት ስብሰባ ከቀረም ወራት አልፎታል። በስብሰባ ተገኝቶ ሀሳቡን በመግለጽ ነግሮች የሚስተካከሉበትን መንገድ መፍጠር አለበት»ብለዋል።

ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

Hosted by www.Geocities.ws

1