ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

ሰኔ ሠላሳ (ጁላይ 7) ዓለም ዓቀፍ የተቃውሞ ሰልፍ ሊካሄድ ነው

(ንጋት ረቡዕ ሰኔ ፲፭ ቀን ፲፱፻፱፯ ዓ.ም.)

በመላው ዓለም ኢትዮጵያውያን የኢህአዴግ መንግሥትን በመቃወም በአይነቱ ልዩና ከዚህ በፊት ተካሂዶ የማያውቅ ታላቅ የተቃውሞ ሠልፍ በያሉበት አገር በመሆን ሰኔ ሠላሳ (ጁላይ 7) ቀን ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆናቸው ታወቀ።

ሠላማዊ ሰልፉ የሚካሄደው ከግንቦት ሰባቱ ምርጫ ጋር በተያያዘ ኢህአዴግ ቁጥራቸው ለጊዜው በውል ባልታወቁ ሠላማዊ ዜጎችና የፖለቲካ ሰዎች ላይ የፈፀመውን ግድያ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በእስር ቤት በማጎሩ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ኢህአዴግን እንዳልመረጠው እየታወቀ ኢህአዴግ ግን በገዛ ጉልበቱ በምርጫው አሸናፊ ነኝ በማለት በመንግሥትነት ለመዝለቅ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በመቃወም ነው።

በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ በአውሮፓና በአውስትራሊያ የሚካሄደውን ይህን ታላቅ ሠላማዊ ሰልፍ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ለየት የሚያደርገው በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአንድ ቀንና በተመሳሳይ ሰዓት ሠላማዊ ሰልፉን የሚያካሂዱ መሆናቸውና ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነቱ የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ ሰልፍ በኢትዮጵያውያን ተካሂዶ አለማቁ ነው።

የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ለሚኖሩባቸው መንግሥታት አቤቱታቸውን የሚያሰሙ ሲሆን፣ ይህንን የተቃውሞ ሰልፍ ለየት ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ የሁሉም አገር ሰልፈኞች ለመንግሥታቱ የሚያቀርቧቸው ጥያቄዎችና አቤቱታዎች አንድ አይነት እንደሆኑ ታውቋል።

"በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ለአንድ ዓላማና ግብ የነበሯቸውን ልዩነቶች አቻችለው በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘው ሊንቀሳቀሱ መቻላቸው የሚያስገርምና የሚያስደስት ነው" ይላሉ ይህንን እንቅስቃሴ እየተከታተሉ ያሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን። ለዚህም ምክንያት የሆነው የኢህአዴግ የ14 ዓመታት የግፍ አገዛዝ እንደሆነ ይስማሙበታል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ድምፅ እስካልተከበረ፣ እየጠየቃቸው ያሉት ጥያቄዎች ተገቢው ምላሽ ካልተሰጣቸው፣ ግድያው፣ እስሩና እንግልቱ እስካላበቃ ድረስ የተቃውሞ እንቅስቃሴው በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል ታውቋል።

በተለይ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ኢህአዴግ የበርካቶችን ሕይወት ካጠፋ ወዲህ በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በያሉበት አገር መሆን የተቃውሞ ድምፃቸውንና አቤቱታቸውን ማሰማታቸው ይታወቃል።

ወደ ዜና ገጽ መልሰኝ    ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

Hosted by www.Geocities.ws

1