ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

"ሥልጣን ቢኖረኝ ኖሮ ይሄ ሁሉ አይከሰትም ነበር፣ እንዳሻንጉሊት ነው ለማለት ይቻላል" የጋምቤላ ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ኦኬሎ አኳዬ

በስቶክሆልም ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ድምፅ ራዲዮ (ኢድራ) ሜይ 9 ቀን 2004 (ግንቦት 1 ቀን 1996 ዓ.ም.) የጋምቤላ ፕሬዝዳንት የነበሩትን አቶ ኦኬሎ አኳዬን በጋምቤላ ክልል ስለተከሰተው ችግርና በዚያ ዙሪያ በስልክ ቃለምልልስ አድርጓቸዋል። የራዲዮ ጣቢያው የስርጭት ፕሮግራም ዘወትር ረቡዕ ከምሽቱ 1 ሰዓት ተኩል እስከ 2 ሰዓት ተኩል እንዲሁም ዘወትር እሁድ ከቀኑ 4 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት በ88.90 ኤፍ ኤም ሜጋ ኸርዝ ሲሆን፣ የስርጭቱ ቋንቋ አማርኛ ነው። ጣቢያው ከመንግሥት ያልወገነና ነፃ ነው። አቶ ኦኬሎን ቃለምልልስ ያደረገላቸው ጋዜጠኛ አህመድ ነበር። እኛም ቃለምልልሱን ምንም ሳንጨምርና ሳንቀንስ እንደወረደ እንደሚከተለው አቅርበነዋል። (ቃለምልልሱን ማድመጥ ለምትሹ http://www.ethiopiancenter.com በሚለው የድኅረ-ገጽ አድራሻ ላይ ታገኙታላችሁ)

ኢድራ፦ ጤና ይስጠልኝ አቶ ኦኬሎ!

አቶ ኦኬሎ ደህና ነኝ አዎ!

ኢድራ፦ እስቲ ራስዎትን ለአድማጮቻችን ያስተዋውቁ አጠር አድርገው

አቶ ኦኬሎ እኔ የምባለው ኦኬሎ አኳዬ ነው የምባለው። በቅርብ ጊዜ የጋምቤላ ክልል ፕሬዝዳንት የነበርኩ ነኝ።

ኢድራ፦ የት ይገኛሉ? ለምንስ አሁን ያሉበት ቦታ ለመሆን ተገደዱ?

አቶ ኦኬሎ አሁን ያለሁት ኖርዌይ ነው። ያስገደደኝ ደግሞ እንደምታውቁት በጋምቤላ የተከሰተው ችግር ነበር። እና ችግሩ ሲከሰት መፍትሔ ከመፈለግና አንድ ደረጃ ላይ ደርሰን ካለው መንግሥት ጋር ከመድረስ ይልቅ መልሰው እኔን ለማጥቃትና በሕይወቴ ላይ ችግር ሊያስከትል በሚደርስበት ሁኔታ ላይ ነው። እና የምንሠራው ሥራ በሙሉ በዚያን ወቅት ከማረጋጋት ይልቅ ሌሎች ሥራ ውስጥ እንድንገባና ችግሩ እንዲባባስ ነበር እየተደረገ ያለው። መጨረሻ ላይ ደግሞ ችግሩ እንዲበርድ ለማድረግ በጀርመን ራዲዮ በምጠቀምበት ጊዜ ችግሩ ለጊዜው ቢቆምም እነሱ ደግሞ እንደጠላት አድርገው ነው የቆጠሩኝ። በዚያ ላይ ደግሞ ሕይወቴን ለማጥፋት ጥረት ሁሉ አድርገው ያው እንደምንም ብዬ እያረጋጋን ከቆየን በኋላ እስከ 27 ድረስ ቆይቼ መጨረሻ ላይ ለመሄድ ወስኛለሁ። እንዲያውም ደግሞ በስብሰባ ላይ "እኛ እዚህ የምንሠራው ችግሩ እንዲባባስ ነው" ብዬ ተቃውሞ አቅርቤ ነው ታህሳስ 29 ማታ ስንሰበሰብ እንደዛ ብዬ ነው ከዚያ በነጋታው በ30 ጉዞ የቀጠልኩት። ተቃውሞ አቅርቤ ነው። በጣም ሁኔታው ደስ ስለማይል - የነበረው ሁኔታ። እና ሕይወቴ ላይ የመጡ ስለሆነ ነው።

ኢድራ፦ በሕይወቴ ላይ አደጋ ሊያደርሱ የመጡብኝ ስለሆነ ለመሰደድ ተገደድሁ ነው የሚሉት?

አቶ ኦኬሎ አዎ!

ኢድራ፦ ምንድን ነው ችግሩ? የችግሩ መንስዔ ምንድን ነው? ለምን ተነሳ ችግሩ?

አቶ ኦኬሎ ቅዳሜ ዕለት ነበር ታህሳስ 13። ያው እንዳጋጣሚ የክልሉን ፀጥታ በሚመለከት ስብሰባ ላይ ነበርን - እዚያው ምክር ቤት ውስጥ። ስብሰባ ላይ እያለን በመንገድ ላይ 27 ኪሎ ሜትር ከከተማው ስምንት ሰዎች - የዩኤን እና የአራ ሠራተኞች እና አንድ ያጅባቸው የነበረ ፖሊስ ባልታወቁ ሰዎች በጥይት ይመታሉ። ሰዎቹ ይሞታሉ። ሬሳቸውን ለመውሰድ ከከተማው ፖሊስና የተወሰነ የመከላከያ ሠራዊት ወደቦታው ይሄዱና እሬሳውን ይዘው እየመጡ እያሉ በቀጥታ ደግሞ ወደ ምክር ቤት ነው ሬሳውን ያመጡት - አጅበውት። ከዚያ ምክር ቤት እንደደረሱ የከተማው ህዝብ እንዳለ የት መጡ - ምክር ቤት አካባቢ። ከዚያ እንደገና እሬሳውን ይዘው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱት። ከፖሊስ ጣቢያ ደግሞ የስምንቱን ሰዎች ሬሳ እንደገና ወደ ሆስፒታል ወሰዱት። ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ እነዚህ በመከላከያ ሠራዊት እየታጀቡ የከተማው ደገኞች የሆኑትን አብረው በየሰዉ ቤት እየሮጡ በጥይት፣ በገጀራ፣ ... በምናምን እያሉ ሰው መግደል ጀመሩ። ይሄ ደግሞ ምንድን ነው - ወዲያውኑ መንገድ ላይ ሰዎች ሞቱ ወዲያውኑ እሬሳዎቹን እንዳስቀመጡ ይሄን ሁሉ ግድያ በየሠፈሩ ሲፈፅሙ እንደከረሙት ነው። እና ይሄ ነው ዋናው የችግሩ መንስዔ ተብሎ ሊጠራ የሚችለው። ሪቬንጅ (ብቀላ) ማለት ነው። እነዚያ ሰዎች ሞቱ አሁን ደግሞ ከተማ መጥተው ደግሞ ሰዎች መግደል ተጀመረ። እና ለሦስት ቀን በተከታታይ ከተማ ውስጥ ከፍተኛ ግድያ እንደነበረ ነው። ይሄ ወዲያውኑ ነው።

ሌላው ደግሞ መፍትሔ ሲፈለግለት የቆየ ችግር ነበር። የነዳጅ ሁኔታ አለ እዚያ አካባቢ። የአሁኑ መንግሥት ያለው ነዳጁ ካለበት ቦታ ኤክስፕሎር ለማድረግ ሰዎቹን መጨረስ አለበት የሚል ዓላማ ይዞ ነው ያለው እስካሁን ድረስ። በዚያ አካባቢ ሰዎች እንዲኖሩ አይፈልግም። በተለይ ወዲህ ያሉትን አኝዋኮችና ወደ ማዶ ያሉትን አኝዋኮች እዚያ አካባቢ እንዲኖሩ አይፈልግም። እና ስለዚህ ግድያውን የፈፀመው ስለዚህ ነው። ሰው እየተመረጠ ነበር ያኔ። ስለዚህ ኢሚዲየት ኮዙ ያው ሪቬንድ ነው። እንግዲህ መንግሥት ሪቬንጅ ሲያደርግ አላየንም። በዚህኛው መንግሥት ብቻ አይተናል። መከላከያ ሠራዊት እየታጀበ። ሌሎቹ ደግሞ ገብተውበት ሪቬንጅ የማድረግ ሁኔታ ነው። የቆየው ግን ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዘ ነው። የነዳጁ ጉዳይ ነው።

ኢድራ፦ ለምንድን ነው የተገደሉትን እነዛን ሰዎች ወደ ምክር ቤቱ በቀጥታ የወሰዷቸው? ለምን በቀጥታ ወደ ሆስፒታል አልወሰዷቸውም? ወይም ሬሳ የሚቀመጥበት ቦታ? ምንድን ነው ወደ ምክር ቤት የወሰዱበት ምክንያት?

አቶ ኦኬሎ ይሄማ (እየሳቁ) በቀጥታ የተፈለገው እኔ ነኝ። እኔ ደግሞ በኋላ ነው ... እንዲያውም የመከላከያው አዛዥ ፀጋዬ የሚባል "ያንተ መኪና በሚታይበት ጊዜ ደም ደም ያሰኛቸዋል" ይላሉ። እና ከዚያ በኋላ ምንድነው የተፈለገው እዚያ አካባቢ እኔ መኖሬ ነው። እንዲያውም ጠይቀዋል የሚል ኢንፎርሜሽን ነበረ። እንዲያውም እንዳጋጣሚ ቅዳሜ ስለነበረ እኔ ደግሞ ከቤቴ ወጥቼ እንዲያውም ይህቺን ችግር መንገድ ላይ የተከሰተውን እንዴት እንደሆነ ስንት ሰው እንደሄደ ከመከላከያ ሠራዊቱ ግቢ አካባቢ ነበርኩ። እና ያቺ ቀጣዩ ... እንጃ አይ ዶኖ ... ወይ ደግሞ ምክር ቤቱ ውስጥ ሰው መንገድ ላይ እየገደለ ነው የሚል ሃሳብ ኖሯቸው ይሁን አይሁን። እና ይሄንን ለምን እንዳመጡት ከዛ ተነስተው ነው። የኔን ስም እያሉ ነበር። "ኦኬሎ የት አለ?" ሲሉ የነበሩት። ዘበኞቹም ሌሎቹም እንደዚያ ሲናገሩ ነበር አሉ።

ኢድራ፦ ለምንድን ነው ከእርስዎ ጋራ ቅራኔ ውስጥ የገቡት? ለምንድን ነው እርስዎን የፈለጉዎት? ምንድን ነው የእርስዎና የመንግሥት ልዩነታችሁ? ቅራኔአችሁ በምን የተነሳ ነው?

አቶ ኦኬሎ ዌል አይዶኖ ... ቅራኔ እንኳ ሳይሆን በእኔና በመንግሥት መሃከል ቅራኔ ውስጥ የገባንበት ነገር በግልፅ የለኝም። ግን እንደምታውቀው ከምርጫው ጋር ነው። ወደው አይደለም ያስቀመጡኝ እነሱ - መንግሥቶች የሚሻለው አጥተው ነው። በ92 ዓ.ም. በነበረው ምርጫ ተመርጬ ነው። ከዚያ በኋላ ሥልጣኑንም ሌላውንም ትቼ ነው ወደ ደጋ መሃል አገር መጥቼ ሥራ የጀመርኩት። ትምህርት ቤት እያለሁ አማራጭ ሲያጡ ሌሎቹን ሁሉ ሲያፈናቅሉ ሲያፈናቅሉ መጨረሻ ላይ አስቀመጡኝ። ያስቀመጡኝ ወደው ሳይሆን ሌላ የሚፈልጉት ሰው ነበር። ከዚህ ሌላ ያልተመረጠ ሰው ፈልገው ነበር። ሰውዬው እንዲመረጥ ለማድረግ ብዙ ጥረቶች ሲያደርጉ ነበር። እኔ እንጃ ... አይ ዶኖ ... ለምን እንደማይፈልጉኝ ... ምርጫ ነው ብዬ ገብቼበት አመኜበት ነው - ከዚያ በኋላ ተመርጬ የመጣሁት። ስልጣኑንም ስይዝ ደግሞ የግድ ይዤ አይደለም። እነሱ ደግሞ በፍላጎታቸው ነው። ምክንያቱም እነሱ ባይፈልጉም ህዝቡ መርጦኛል። ግን ያን ጊዜ የምክር ቤቱ አባል ሆኜ አይደለም የሠራሁት። ከትምህርት ቤት ነው የወሰዱኝ። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው የወሰዱኝና ፕሬዝዳንት ያደረጉኝ። አሁን የጠሉኝ ለምን እንደሆነ ግራ ገባኝ።

ኢድራ፦ አቶ ኦኬሎ እርስዎ የጋምቤላ ተወላጅ ነዎት ...

አቶ ኦኬሎ አዎ!

ኢድራ፦ እርስዎ ፕሬዝዳንት ነበሩ?

አቶ ኦኬሎ አዎ!

ኢድራ፦ ስልጣን ነበረዎት ወይ? የሚፈልጉትን በትክክል ለመሥራት የመወሰን መብት ነበረዎት ወይ?

አቶ ኦኬሎ የለኝም (እየሳቁ) ... እሱማ ከባዱ ነገር እዚያ ላይ ነው። እንግዲህ ብችል ኖሮ ይሄንን ነገር ወዲያውኑ ማቆም እችል ነበር። ምክንያቱም የመከላከያ ሠራዊት ያለበትን ነገር መወሰን ብችል ኖሮ ወዲያውኑ የመከላከያ ሠራዊት ይሄንን እንዲያቆም ማድረግ እችል ነበር። ግን የኔ ሥልጣን አልነበረም። ይሄ ደግሞ ሥልጣኑ የመከላከያ ሚኒስቴር ነው፤ የክልሎች አይደለም። ሁለተኛ ደግሞ እየሠራሁ እያለሁ ከጎን ደግሞ እነሱ የሚያምኑባቸው ሰዎች አሉ። ይሄ ደግሞ ከሕገ-መንግሥት ውጪ ነው። እና በተወሰነ ደረጃ ላይ ነው ስንቀሳቀስ የነበረው እንጂ ሙሉ ሥልጣን ኖሮኝ የመወሰን፣ አንዳንድ ነገር በኃላፊነት ተረክቦ እስከመጨረሻው የመድረስ አልነበረም። የለም ደግሞ። እንጃ በሌሎች ክልሎች ይኖር እንደሆነ እንጂ፤ በጋምቤላ አልነበረም። እና ስለዚህ ...

ኢድራ፦ ስለዚህ እርስዎ ዝም ብለው እንደ አሻንጉሊት አስቀመጡዎትና እነሱ የሚፈልጉትን ይሠራሉ እንጂ እርስዎ በሕገ-መንግሥቱ የተፈቀደለዎትን ሥራ በሕጉ መሥራት አይችሉም ማለት ነው?

አቶ ኦኬሎ ታዲያስ ይሄ ሁሉ ሰው እኮ አይሞትም ነበር። ተገድጄ ነው በራዲዮ እንኳ ... በጀርመን ራዲዮ የተናገርኩት የሰው ሕይወት መጥፋትን ለማቆም ብዬ ነው። ሥልጣን ቢኖረኝ ኖሮ ይሄ ሁሉ አይከሰትም ነበር። እንዳሻንጉሊት ነው ለማለት ይቻላል።

ኢድራ፦ እንደገና ልመለስና ከኢህአዴግ ጋር የነበረዎት ግንኙነት ምን ይመስል ነበር? በሥራ ላይ በነበሩበት ጊዜ እንዴት ነበር ግንኙነታችሁ? ትዕዛዝ ያስተላልፋል የኢህአዴግ መንግሥት "ይሄንን ሥሩ!" ብሎ? ወይስ እናንተ ለአካባቢው ህዝብ እድገት፣ ብልፅግና የሚመስላችሁን በሃሳብ ታቀርቡና ሥራ ላይ ታውሉታላችሁ?

አቶ ኦኬሎ ዌል እዚያ ላይ ነው ችግር ሊኖር የሚችለው። ምክንያቱም እንግዲህ ከኢህአዴግ ጋር መሥራት ቀላል አይደለም። ሁል ጊዜ የምትሠራውን በሙሉ መጀመሪያ አሳውቀህ መሆን አለበት። ኢንፎርሜሽን ማስተላለፍ መቻል አለብህ - መጀመሪያ። በራሴ እሠራለሁ እወጣለሁ ካልክ ደግሞ ትጠመዳለህ። ለምሳሌ አሁን የተጠመድኩበት አለ። ብሔረሰቦች እርስ በእርሳቸው ሲጋጩ ነበር። ኑዌርና አኝዋክ፣ መዠሚና አኝዋክ ... እንደዚሁ እነሱው ራሳቸው ሲያጋጩ ቆይተው - መጨረሻ ላይ እርቅ እንዲደረግ ጥረት አድርገን ህዝባችንን ስናስማማ። ችግሩንም ተረድተዋል፣ ማን እንዳስቸገረ፣ እንዴት እንደሆነ። ይህቺን ደግሞ በራሳችን ብቻ እስቲ እንይ - በባህል ስለሆነ ሽማግሌዎቻችንንና አባቶቻችንን ጠርተን ይህቺን ነገር እንጨርስ ብለን ሳንጠራቸው በሽምግልና በመጨረሳችን ችግር ሆነብኝ። ለምን እስከዚያ ድረስ (ለብቻቸው) ቻሉ የሚል ነገር ነበር። እና ይሄ ሁሉ መንግሥትን አነጋግረህ ጨርሰህ በየቀኑ የምታደርገውን ሪፖርት አድርገህ። ትንሽ እንኳ ቢሆን። ግን በራስህ ተንቀሳቅሰህ፣ ተዝናንተህ፣ ውሳኔ ሰጥተህ እራስህ ኮንፊደንስ (በራስ መተማመን) ኖሮህ የምትሄድበት ሁኔታ አይደለም አሁን ያለው። አልነበረም ደግሞ። እኔም ብዙ ጊዜ ቆይቻለሁ ከ86 ጀምሮ እንደዚያው ነው። ጥሩ ብትሠራም ትጠረጠርበታለህ። መጥፎ ሥትሠራም የባሰ ነው የሚሆነው። መጥፎም ጥሩም የሚሆንበት ጊዜ አለ። ኢት ኢዝ ኤ ኮምፕሌክስ ... በጣም የሚዛባ ነገር አለ እዚያ አካባቢ። አሠራሩና ሌላው በሙሉ ነፃ አያደርግህም።

ለልማትም ደግሞ አንተ ብቻህን እሄዳለሁ ብትልም ለልማት ገንዘብ ቢሰጥህ፣ የምትፈልገው ካፒታል ቢኖርህም፣ ቢሰጥህም እንቅፋት ያሳድሩብሃል። ወይ ደግሞ ኮምፕሌክስ በሌሎች አካባቢ እንዲፈጠር ያደርጋል። ስለዚህ በዚህ መሃከል ላይ የመሥራትና ወደፊት መሄድና የማደግ ሁኔታ ኢህአዴግ ከአመራሩ ነው። ሁሉ ነገር። ... እኔ የኢህአዴግ አባል አይደለሁም። ከኋላ ሆነው የሚያምንባቸው አሉ። እኔ ፕሬዝዳንት ሆኜ ከኋላ የሆነው ደግሞ የበለጠ የሚያምኑባቸው አሉ። ስለዚህ ... ለምሳሌ ትልቁ ነገር የተገነዘብኩት ምንድን ነው - ሰዎቹ ሞተው፣ እየተገደሉ እያሉ እኔ ሪፖርት በማደርግበት ጊዜ "ሰዉ ችግር ላይ ነውና አንድ ቡድን ከላይ ይላክና ይሄንን ጉዳይ ያስፈፅም" ብዬ ለነዶክተር ገብረአብ በማስተላልፍበት ጊዜ፤ ገና ለገና ደግሞ ምንም ነገር ሳይሆን "ችግሩ የተከሰተው በኑዌርና በአኝዋክ ነው። እና ችግሩን ለማቃለል እናንተ ጥረት አድርጉ" እዚያ አካባቢ ይሄን ሁሉ ደግሞ በራዲዮ በምናምን ሁሉ እስከማጋባት ደረሰ። በነጋታው ደግሞ እኔ ይሄንን ሁሉ አይቼ በቃ እነዚህ ሰዎች ሌላ ችግር እየፈጠሩ ነው አልኩኝ። ችግሩ የተፈጠረው በመከላከያ ሠራዊት እና በተወሰኑ ደገኞች አካባቢ ሆኖ አኝዋኮች ሲጨፈጨፉ፤ አሁን ደግሞ በአኝዋክና በኙዌር ሲባል ይቺን መጀመሪያ ዲፌንድ ለማድረግ መሆኑን ደርሼበት በጀርመን የለቀቅሁበት ጊዜ አለ። ስለዚህ ነፃ አይደለም። እነሱ ፎርሙላ አስቀምጠው ነው የሚሠሩት ማለት ነው። 

ኢድራ፦ ገብረአብ የሚሏቸው ማን ናቸው?

አቶ ኦኬሎ ገብረአብ በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆኖ የክልሎች ጉዳዮች ኃላፊ ነው።

ኢድራ፦ አንድ ነገር አልዋጥልህ አለኝ። ሕገ-መንግሥቱ የክልሎችን የአስተዳደር መብት ለክልሎች ሰጥቷል።

አቶ ኦኬሎ አዎ!

ኢድራ፦ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት የክልል ኃላፊዎች ለምሳሌ እርስዎ እንደፕሬዝዳንትነትዎ መሥራት በሚፈልጉበት ጊዜ ኢህአዴግ ካልተስማማው ይቃወማል ማለት ነው?

አቶ ኦኬሎ መንቀሳቀስ አይቻልም እኮ። አሁን'ኮ እየነገርኩህ አይደለሁ። "ይሄን አደርጋለሁ፣ እንደዚህ አደርጋለሁ፣ ..." ብትል በቃ ዞሮ ዞሮ ትጠመዳለህ እንጂ የትም ቦታ የምትደርስበት ሁኔታ አይደለም።

ኢድራ፦ ምን አይነት ሰዎችን ነው ከእርስዎ ታማኝ አድርገው የሚያስቀምጧቸው? ምን አይነት እምነት ያላቸውን ሰዎች ነው?

አቶ ኦኬሎ አንትን ሊቆጣጠሩ የሚችሉ ሰዎች ነው ከኋላህ የሚያስቀምጡት።

ኢድራ፦ ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ የኢህአዴግ መንግሥት ወታደሮችም ግድያው ላይ እጃቸውን አስገብተዋል የሚባለው ምን ያህል እውነት ነው?

አቶ ኦኬሎ ይሄማ በጣም በጣም እውነት ነው። ነበርኩ እዚያ ቦታ። ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ አሁንም ቢሆን ነበሩበት። ምክንያቱም ሌት አስ ሴይ ... አሁን እንትና ማነው እኔ የማስታውሰው አለ - በትክክል ነው የሆነው። ከዚያ በፊት በሚሆንበት ጊዜ ጠርበምቦ አካባቢ መንጥቅ ቀበሌ ነው። እና 5 ሰዎች ቡና እየጠጡ እያሉ በአንድ አኝዋክ እየተመሩ መንደር ውስጥ ይገቡና ሰዎቹን ይገሏቸዋል። ይሄ ኖቬምበር 25 አካባቢ ነው የሆነው። እንደገና ደግሞ ጋምቤላ ከተማ የተከሰተው ችግር እነሱ እየመሩ ናቸው። በዩኒፎርም ይለያሉ። ይሄን'ኮ መንግሥት ራሱ የሚያውቀው ነው። የመከላከያ ሠራዊትም የሚያውቀው ነው። ምክንያቱም ሰዎቹ ከሞቱ ሰዎቹ ከተገደሉ በኋላ በከተማው መሃከል በ13 በተከሰተው ችግር 13፣ 14፣ 15 ወደ 9 እና 10 ሰዎች እነ ዶ/ር ገብረአብ፣ እነ አልማው፣ ... የሚባሉትም መጥተዋል - ከላይ። ይህቺን ኢንቨስትጌት ለማድረግ። ከጅማ ደግሞ ኮሎኔል ኢትዮጵያ የሚባሉ ነበሩ። መጡ - አብረን እየዞርን ስናይ ነበር። በምንሄድበት ቦታ እየተናገርን ነበር - በአክሽን ነበር ህዝቡ የሚነገረው። ዩኒፎርም የለበሱ ወንዱም ሴቱም ለእነሱ ይናገራል። መካነየሱስ አካባቢ ስብሰባ አድርገናል። በፎቶግራፍ፣ በቪዲዮ ቀርፀው ነው የሄዱት። በእጃቸው ነው ያለው። በመንግሥት እጅ ነው ያለው። መካነየሱስ የተፈናቀሉ ሰዎች ነበሩ በአስተርጓሚ እንዲሁም አንዳንዴ ራሳቸውም ሲናገሩ ነበር። ይሄ ደግሞ እውነት ነው።

እንደገና በ15 ደግሞ ሁለት ሰው መርጠው ነው ሰው ተሰብስቦ እያለ ዲፖ ነዳጅ ማደያ አለ። እንደማጠራቀሚያ ቦታ በአዲሱ ነዳጅ - አሁን ይወጣል ተብሎ የታሰበው - እዚያ ካምፕ ላይ የተወሰኑ ወታደሮች አሉ። ከላይ እዚያ ሮጠው ኡሚኒጋ የሚባል ሰፈር ይመጡና ሁለት ሆነው - ሁለት አኝዋኮች ይመርጣሉ እዚያ አካባቢ። የሚመረጡት ደግሞ መርጠው ከዚያ በኋላ ደግሞ አንደኛው በፊት መርጦ ሁለተኛው ደግሞ ፈርጥጦ እንደሄደ መልሶ ሁለተኛውን ገደለው። ይደወልልኛል፣ እኔ ደግሞ ለሻለቃው እነግረዋለሁ። "ምንድን ነው ይሄንን ... ምን እየተደረገ ነው?" ለሻለቃው ብዬ ስደውልለት "አይ እኔ አልሰማሁም" አለኝ። ያው ሠራዊቱ ከዲፖ ወጥቶ ሰው እየገደለ ነው። ምንድነው ትናነትናም ዛሬም ይሄ ሁሉ እንደዚህ ነበረ። ወሮኪዲን በጥይት ነው የመቱት፣ እነቄሱኬር በጥይት ነው፣ ዲዲሞ ሞዲም በጥይት ነው፣ ፒተር ዴኒም በጥይት ነው፣ ... እና እንደዚህ አይነት ኢንፎርሜሽን እየደረሰን ነው። አሁን ደግሞ ሂድና ከአሁን በኋላ አቁመው። በ15 ደግሞ እንደዚሁ ዶ/ር ገብረአብ መግለጫ ሰጠ። በኙዌርና በአኝዋክ አለ። የኢትዮጵያን ህዝብ ለማወናበድ ነው። እኔ ደግሞ በ16 ነገርኩት - የመከላከያ ሠራዊት እጁ እንዳለበት። እና የተወሰኑ ኃይላት እንዳሉበት። ይሄ ግልፅ ነው። ማንም ሰው ቢሄድ የሚያየው ነው። ግን መረጃን የማጥፋት ሥራ ሌሎችም ሌሎችም ቢደረግም አኝዋኩ በቀላሉ ... የሚሆን አይደለም። ምክንያቱም ችግሩን ያውቃል። ከዚያ በፊትም ፈነዳ እንጂ ይላሉ ሲናገሩም። ይሄን ሁሉ የአካባቢው ህዝብ በሙሉ የሚያውቀው ነው። የአደባባይ ምስጢር ነው በጋምቤላ ውስጥ ያለው። መንግሥት ራሱ እጁ ሳይኖርበት አይቀርም የሚል እምነት ያላቸው ይጠይቃሉ። ዶ/ር ገብረአብ ራሱ ተጠይቋል። መንግሥት አዞ ይሆናል ብለን እየተጠራጠርን ነበር የሚሉ አኝዋኮች አሉ። እና ስለዚህ ሰዎቹም አሉ። ማንም ይሄንን እዚያ አካባቢ የሚያገኘው ነው።

ኢድራ፦ አቶ ኦኬሎ እርስዎ የኢህአዴግ አባል አልነበሩም ...

አቶ ኦኬሎ አባል አይደልሁም።

ኢድራ፦ ለህዝቡ ምን አደርጋለሁ ብለው ቃል ገብተው ነው ሊመረጡ የቻሉት? ኢህአዴግስ እንዴት እርስዎን አባል እስካልሆኑ ድረስ እንዴት ሊመርጥዎት ቻለ? ምን ብለው ቃል ስለገቡ ነው?

አቶ ኦኬሎ በ86 አካባቢ የቢሮ ኃላፊ ተደርጌ ተሹሜ ነበር። እና እየሠራሁ እያለሁ እንጃ ... አይ ዶኖ ... እንግዲህ ጥፋት ተሰራም አልተሠራም ካልተፈለግህ ትወጣለህ። ኢህአዴግ ካልፈለገህ ትወጣለህ። ጥሩ ብትሠራም። ተመረጥህም አልተመረጥህም። ብትመረጥም ደግሞ ኢህአዴግ ካልፈለገህ ሥልጣኑን አትይዝም። ያለው ሁኔታ ይሄ ነው - እኔ በዚያ ዓመታት ውስጥ የተማርሁት። እና በዚህ መሃከል ላይ ሥልጣን ላይ ከወጣሁ በኋላ እኔም እራሴ ምርጫ ወስጄ ትምህርት ቤት አካባቢ ሄድሁ። እዛ ቆይቼ እንደገና ስመጣ ምርጫ ነበር። ተወዳደርሁና አለፍኩ። የተወዳደርሁትም ፓርቲ ነበረኝ። ዲሞ ኮንግረስ ፓርቲ የሚባል ነው። ካሉት ፓርቲዎች ግን ኢህአዴግ የሚወደውና ደጋፊዬ ነው ብሎ የሚጠራው ግንባር የሚል አለ።

ግንባር የኢህአዴግ ፓርቲ ነው። ኮንግረስ ግን ከዚህኛው ጋር በዴሞክራሲያዊ መንገድ እሄዳለሁ ብሎ ተፎካክሬ አልፋለሁ በሚል ነው። በእውነትም እዚያ ውስጥ ተፎካክረን ብናልፍም ሁለት ወረዳ ነው ያን ግዚ በወቅቱ ጐክ እና ጆር የሚሉትን ወረዳዎች ነው ኮንግረስ ያሸነፈበት። ሌላውን በሙሉ አድበስብሶ የፈለገውን አድርጎት ኮሮጆ አቃጥሎ እዚያ ውስጥ የነበረ ነው። እኔ ከዚህ በኋላ ነው ተስፋ የቆረጥኩት። ምክንያቱም ባልፍም እዚያ ውስጥ ከገባሁ ያው እሳት ውስ  ነው የምገባው እንጂ። እነዚያ በትክክል ባላላፉት ሰዎች ላይ በማጭበርበር አለፉ የተባሉትን የግንባርን ቡድኑም ወረዳ አለፉ የተባሉት ከእነሱ ጋር መሥራት ሌላ ችግር ስለሚሆን እኔ በቀጥታ ወደ ትምህርት ቤት ሄድኩ። የራሴን ትምህርትም ልቀጥል ብዬ ተወዳድሬም ተፈትኜም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ገባሁ። እንግዲህ ከዚያ በኋላ ደግሞ ትምህርት ቤት እያለሁ እንደገና እነሱ መጥተው ሰው ሲያጡ መልምለው የወሰዱኝ። ቃል ኪዳን የገባሁት ዴሞክራሲ አመጣለሁ የሚል እምነት ነው ያለኝ እንጂ ሰው ፊት ቆሜ "ይሄ ይሄንን እሠራለሁ ..." ብዬ ቃል የገባሁት አይደለም። ...

ኢድራ፦ የጋምቤላ ህዝብ ፍላጐት ምንድን ነው? ምንድን ነው የጋምቤላ ህዝብ የሚፈልገው? ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህ ጋምቤላ ውስጥ ያለው ችግር እንዲጠፋ ምን ማድረግ አለበት? ችግሩ እንዲፈታ የጋምቤላ ህዝብስ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ምን እንዲያደርግ ይፈልጋል?

አቶ ኦኬሎ ይሄ ጥሩ ጥያቄ ነው። እንግዲህ በአሁኑ ጊዜ የጋምቤላ ህዝብ ችግር ላይ ነው ያለው። ማለት ግልፁን ለመናገር ከሆነ ከ13 በፊትና በኋላ እስካሁን ድረስ ችግር ላይ ነው ያለው። ሌላው ተሰዷል። ሌላው ደግሞ የመደፈር ሁኔታዎች አሉ። ቤት የማቃጠል አለ። ሌላም የመደብደብ፣ ከእስር ቤት የመሰወር፣ ... ሌላም መአት መአት ነገር አለ። ተሠርቷል። በጣም ከወንጀል ጋር የተያያዙ ሥራዎችም ተሠርተዋል። ከግድያ ጋር የተያያዙም ተሠርተዋል። ስለዚህ ምን መደረግ አለበት የሚለው አሁን መንግሥት ለመከላከል ብሎ ለዲፌንስ ብሎ የጀመረው ነገር አለ። በጣም መጥፎ የሆነ። መሣሪያ አስፈታለሁ ብሎ ዲስአርም አደርጋለሁ ብሎ ጀምሯል አሁን። በዚህ ሰበብ ነው አሁን ሰው እየተገደለ ያለው። አበቦ ላይ ቁጭ አድርጓል ወታደሮቹን፣ ሰኙር ላይ አስቀምጧል፣ ዲማ ላይ አስቀምጧል፣ ጆር ላይም አስቀምጧል። እንዲያውም የጆር ላይ በኋላ እመለስበታለሁ። አሁን በእነዚህ ቦታዎች በሙሉ በየፓኬት ፓኬት አስቀምጦ እና ግንባር ድረስ የመዝለል የማሻገር ሁኔታ እስከተሄደ ድረስ እዚያው ቦታ ድረስ አስቀምጧል። እንደገና ደግሞ መሄጃ መንገድ አካባቢ ሰውም አስቀምጧል። ይሄ ሁሉ አለ። ስለዚህ ምንድን ነው አሁን ለዚህ መፍትሔ የሚሆነው እነዚህ በየቦታው ደግሞ ኦፕሬሽን ብሎ ያስቀመጡትንም ሌላ ከተማ ለነፃ መስሎ በየቦታው ደግሞ ኦፕሬሽን የሚያደርግባቸው ቦታዎች በሙሉ ጠቅላላ ወታደሮቹ ከዚያ አልፈው ወደ መሃል አገር የሚመለሱበት ሁኔታ ...። ውስጥ ያለውም መሃል አገር ያለውም ሊሲሌት ሆኗል። እኔ እኖራለሁ ብሎ እኔ እነዚህን በሙሉ አልናገርም፣ ቁጭ ብዬ ሠርቼ እኖራለሁ ብሎ የወሰነ ሰው አለ። እሱ ደግሞ ከቦታው ተረስቷል። እዚያ ሪፊውጂ ካምፕ እስከመሄድ ድረስና መድፈር ሁኔታ ደግሞ አለ። ይሄ ሁሉ እንዲቆምና ከዚያ በኋላ ወታደሮቹ ወደ መሃል አገር እንዲሄዱ ማድረግ አንዱ መፍትሔ ሊሆን ይችላል።

ሁለተኛው መፍትሔ ደግሞ መሆን የሚችለው፣ ሰዉ ተቸግሯል አሁን። ቤት የለውም። ረሃብ ነው። ... ተቃጥሏል ከዚህ በፊትም። ስለዚህ ሂዩማኒተሪያን በጐ አድራጐት ሰጪ የሆኑ ድርጅቶች በሙሉ ይግቡና የተቸገረውን በሙሉ በዚህም በጋምቤላው በክልሉ የሚገኙትና ከክልሉ አልፈው ያሉትን በሪፊውጂ ካምፕ የሚገኙትን እርዳታ የሚያገኙበትን መንገድ አሰሳ አድርጐ እዚያ ላይ እንትን ማድረግ ያስፈልጋል።

ሌላው ደግሞ መሆን ያለበት አሁን ላለው ችግር የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ማድረግ ያለበት ከዚሁ ችግር በፊትና በኋላ ሰዎች ታስረዋል፣ ተደብድበዋል። በየቦታው ነው ሰዎች እስር ቤቶች እያስቀመጡ ያለው። የሚጠፉትም አሉ። ይሄን ሁሉ ትቶ ያለአግባብ ... አሁን ምንም መረጃ የለም። አሁን ለምሳሌ ስልጣን ከመያዜ በፊት ከኦኬሎ ነጌሎ ጋር የታሰሩ ሰዎች አሉ። ዊትነስ (ምስክር) ይሆናሉ ብለው ሰዎቹን ዝም ብሎ ቁጭ እንዳሉ ናቸው። ወይ አዲስ አበባ መጥተው አልመሰከሩባቸው፣ ወይ ደግሞ ሄደው እንዲመሰክሩ አይደረግም። እንዲሁ አዲስ አበባ ቁጭ ብለዋል። ከዚህ ከግድያው ጋር የተያያዙትን ደግሞ በተለይ ወንዶች የሆኑትንና የተማሩትን በየቦታው የታሰሩትን እንዲፈቱ የማድረግ ሁኔታና ሌሎችም በሙሉ ... አንዱ ኧርጀንት የሚሆነው ይሄ ነው።

ሌላው ደግሞ ከዚሁ ችግር ጋር የተያያዙ ሰዎች አሉ። ሪቬንጅ እንዳይመጣ ከእንግዲህ በኋላ፣ ሪቬንጅ እንዳይኖርና በሠላማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲፈለግ ለማድረግ ከችግሩ ጋር የተያያዙ ሰዎች አሉ። መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ያሉትን በተለይ ከመጀመሪያ ጀምሮ እና በመንግሥት ደረጃ ያሉትን ደግሞ ከችግሩ ጋር የተያያዙት ሰዎች ብዙ መረጃዎች ጠቋሚዎች አሉ። ሌላ ተገላቢጦሽ የሚናገሩትን በሙሉ እነዚያን ሁሉ ማስገባት። እና መረጃን ደግሞ አለማጥፋት። ምክንያቱም የበለጠ ውሸት ውስ  ስለሚያስገባ። መረጃዎችን የማጥፋት እርምጃን እንዲቆም ማድረግ። ምክንያቱም ... በተለይ ደግሞ አንድ ቡድን መጥቶ እዚያ አካባቢ መረጃ እያጠፉ ነበር። ሴቶች ነበሩ'ኮ "ማነው ባልሽን የገደለው?" እያሉ የሚጠየቁት። ... መከላከያ ሠራዊት አሜን ብሎ ስህተቱን መቀበል አለበት። ምክንያቱም ምን መሰለህ ስህተት ተከስቷል። ኦረዲ የመከላከያ ሠራዊት ዩኒፎርሙ በየቦታው ሰው በሚያይበት ቦታ ሰው እየሸሸ ነው አሁን። ምክንያቱም ገዳይ ሆኗል።

ኢድራ፦ ለኢትዮጵያውያን አድማጮችዎ አጠር ያለ መልዕክት ካለዎት?

አቶ ኦኬሎ ያለአግባብ የሰው ልጅ ንፁኅ ነው። መገደል እንደዚሁ ደግሞ ዝም ብሎ መጨፍጨፍ አግባብነት የለውም። ሁለተኛ ደግሞ ከወንጀል ጋር በተለይ ደግሞ ከሂዩመን ካይንድስ አጌይንስት ሂዩመን የሚሉትን የተያያዙትን ጉዳዮች ጋር ማንኛውም መንግሥት የወደፊት ይሁን የኋላ ይሁን ምክንያቱም ይሄ ችግር ተደጋግሟል። ደርግም ሠርቷል። ነገ ደግሞ ሌላው ሊሠራው ይችላል። እና ይሄ ሁሉ በጄኖሳይድና ሂዩማን ካይንድስ አጌይንስ ሂዩማኒቲ የሚሉትን ነገሮች ከግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ የሚመጣ መንግሥትም ለወደፊትም ቢሆን የሌላ ዘር ለማጥፋት ጥረት እንዳያደርግና ይሄ ሁሉ ደግሞ በተለይ ደግሞ ሰብዓዊ መብቶች በሚሚለከት ማንኛውም ሰው ይሄንን ኃላፊነት መረከብ እንዳለበት ነው። እና ማወቅ እንዳለበት ነው። እመራለሁ የሚል ሰው ካለ ይሄን ሁሉ መቀበል መቻል አለበት። ስለዚህ ስህተቶቹ ሲኖሩ ደግሞ መቀበል መቻል አለበት ማንኛውም አመራር ላየ ያለ። ዝም ብሎ ከመከራከርና መፍትሔው እንዳይገኝ ከማድረግ ተቀብሎ ከዛ ... መሄድ የሚያስችልበት ሁኔታ ቢመቻች - ማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ ቢያመቻች። 

ኢድራ፦ አቶ ኦኬሎ ወደፊት ሰፋ ያለ ውይይት እንደምናደርግ ተስፋ እናደርጋለን። በዛሬው ዕለት ከእኛ ጋር ተገኝተው ለአድማጮቻችን ስለሰጡን አስተይየት ከፍ ያለ ምስጋና እናቀርብልዎታለን። ጤና ይስጥልኝ ጌታዬ!

አቶ ኦኬሎ እሺ! አመሰግናለሁ!

ወደ ዋና ገጽ መልሰኝ

 

Hosted by www.Geocities.ws

1