"... ኢትዮጵያ ውስጥ ሕጉ ተቀምጧል አሠሪና ሠራተኛው ግን የለም ..." አቶ አየለ ጌታቸው (በስቶክሆልም የአቢሲኒያ ምግብ ቤት ባለቤት)

በያሬድ ክንፈ (ከስዊድን - አፕሪል 2005)

Ato Ayele Getachewመሃል ስቶክሆልም፣ ቫናዲስ ጎዳና 20 ላይ "አቢሲኒያ ምግበ አቤት" ይገኛል። ባለቤቶቹ ባልና ሚስቶቹ አቶ አየለ ጌታቸውና ወ/ሮ እመቤት ውብዬ አበጋዝ ናቸው። የዛሬ 17 ዓመት በስደት ይኖሩበት በነበረው ግብፅ ነው ትዳር የመሠረቱት። አማኑዔል፣ ኤደን እና ፅዮን የተባሉ የ13፣ የ8ና የ4 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሦስት ልጆች አሉዋቸው። አማኑዔል "ቀይ ክትፎ"ን ከምግቦች ሁሉ አስበልጦ ይወዳል።

አቢሲኒያ ምግብ ቤት በተከፈተ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ደንበኞችን ከማፍራቱም በላይ ሥራውን በጀመረ በዓመቱ በ2003 እ.ኤ.አ. በስዊድን በሚገኙ ምግብ ቤቶች መካከል በተደረገው ውድድር አንደኛ በመሆን የዓመቱ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል። "ሹካና ማንኪያ አናቀርብልዎትም!" ይላል የአቢሲኒያ ማስታወቂያ - በጣቶቻቸው ተመግበው ለማያውቁት ስዊድናውያንና አውሮጻውያን።

በበጋ ወራት አቢሲኒያ በረንዳ ላይ ቁጭ ብለው አንድ ገበታ ሞልተው የሚመገቡ ሞልተዋል። በአጋጣሚ በአውቶቡስ፣ በመኪና፣ በእግርና በሳይክል ሲያልፉ አንዱን ገበታ (መሶብ) ለአራት፣ ለአምስት፣ ... ወርረው በጣቶቻቸው የሚመገቡትን ሰዎች የተመለከቱ ስዊድናውያን በሌላ ጊዜ መጥተው "በጋራና በጣቶች የሚበላውን ምግባችሁን ልንቀምስ እንፈልጋለን" ብለው ይጠይቃሉ። ይመገባሉ። አድንቀውና አመስግነው ይሄዳሉ። እንደሄዱ ግን አይቀሩም። ይደግማሉ። ያዘወትራሉም። አይተውት፣ ቀምሰውት፣ አሽትተውት፣ ... የማያውቁትን ኢትዮጵያዊ ምግብ ይላመዱታል።

ኢትዮጵያን በመልካም ገፅታዋ የማያውቋትና በድርቅና በልመና ብቻ የሚያውቋት ይገረማሉ። እናም ይጠይቃሉ። እንዲህ፦ "አገራችሁም እንደዚህ ጠግባችሁ ትበላላችሁ?" ... "አገራችሁ እንዲህ የተትረፈረፈ ምግብ አለ? ..." ወይን ጠጆቻችንን የጠጡቱ ደግሞ፦ "ኢትዮጵያ ውስጥ የወይን ፋብሪካ አለ? - እኔ አላምንም። ፈፅሞ ሊሆን አይችል። በፍፁም!" ... "ኢትዮጵያ ውስጥ የወይን ተክል ይበቅላል?" ... አንዳንዶቹ ጥያቄዎች አንጎል ያዞራሉ። አቶ አየለና ባለቤቱ ግን በኢትዮጵያዊ ትህትና ተገቢውን ምላሽ ይሰጣሉ።

ፎቅና ምድር የሆነው አቢሲኒያ ምግብ ቤት ጠቅላላ ስፋቱ 205 ካሬ ሜትር ነው። 80 መቀመጫዎች አሉት። በጥቁር ቆዳ ላይ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ምስል በዘይት ቀለም ቅብ በቀኝ በኩል ያለው የመጀመሪያው ክፍል ግድግዳ ላይ ተሰቅሏል። ከፊት ለፊቱ ንግሥተ ሣባ ንጉሥ ሠለሞንን ስትጎበኝ የሚያሳይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሣዊ ስዕል ተሰቅሏል። ግድግዳዎቹ ኢትዮጵያን በሚወክሉ ጌጣጌጦች፣ ቅርፃቅርፆች፣ ስዕሎችና ፎቶግራፎች ተውበዋል። ወጥ ቤቱ ደግሞ በኢትዮጵያዊ የወጥ ቤት ዕቃዎችና የምግብ ዕቃዎች ተሞልቷል።

ምድር ቤቱ በአክሱም ወንበሮችና ሶፋዎች ግጥም ብሏል። በርጩማዎች/ዱካዎችም አሉ። የብረት ወንበሮቹ መቀመጫ የባንዲራችንን ቀለማት በያዘ ጨርቅ አጊጧል። ዘመናዊ ኢትዮጵያዊ ምግበ ቤት ስለመሆኑ በመጀመሪያ ዕይታ ለመመስከር የሚያንገራግር ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም። ወደ ሙሉ ቃለምልልሱ እናምራ። መልካም ንባብ!!

 

ያሬድ የምግብ ቤት ሥራን እንዴትና መቼ ጀመርክ?

አቶ አየለ የምግብ ቤት ሥራን የጀመርኩት በ1967 ዓ.ም. ዕድገት በሕብረት ዘመቻ ጎንደር ነበር የተመደብኩት። የዘመቻው ቦታ ቀበብታ ነበር። ያ ቦታ ስለተሰረዘ መድኃኒዓለም ት/ቤት ፊት ለፊት ያለው ቶታል ባለቤት አጎቴ ነው። አቶ ፀጋ አሣምረው ይባላል። እሱ 8 ሰው መቆሚያ የምትይዝ ቡና ቤት ሰጥቶኝ፣ ሻይ ቡና በመሸጥ እዚያ ሥራ ጀመርኩ።

ያሬድ ትርፉ ያንተ ነበር?

አቶ አየለ ሙሉ ለሙሉ ሰጥቶኝ፣ እራሴ ነኝ የማንቀሳቅሳት። በዚያውም እሱን የማደያውን ሥራ እያገዝኩት የመጀመሪያ ሥራዬን የጀመርኩት እዚያ ነው። ከዛ በ1970 ዓ.ም. ላይ ፒያሣ ውስጥ "ፋኖስ" የምትባል ሬስቶራንት ጀመርኩ። ከዛ እርሻ ሰብልን ኮንትራት ወስጄ እሠራ ነበር። በመጨረሻም የአዲስ ጐማን ኮንትራት እየሠራሁ እያለ ነው ከአገር ልወጣ የቻልኩት።

ያሬድ በስደት ስንት አገሮች ኖረሃል?

አቶ አየለ መጀመሪያ በእግሬ ወደ ጅቡቲ ነው የወጣሁት። ጅቡቲ "ሸርኮሊ ኢታሊያ" የሚባል ሬስቶራንት ውስጥ በምግብ ሥራ ጀመርኩ። እዚያ ነው የጣሊያኑን የምግብ ሙያ ያዳበርኩት። ከዛም ወደ ካይሮ (ግብፅ) ወጣሁኝ። ካይሮም እንደዚሁ አልፎ አልፎ እሠራ ነበር። ከካይሮ ኖርዌይ ገባሁኝ።

ያሬድ ኖርዌይ ውስጥ 'ሠላም' የሚባል ምግብ ቤት ነበረህ?

አቶ አየለ አዎ!

ያሬድ ሠላም ምግብ ቤት ምን ያህል ጊዜ ሠራህ?

አቶ አየለ ወደ ሦስት ዓመት ተኩል።

ያሬድ የራስህ ነበር?

አቶ አየለ የራሴ ነበር። 3 ፎቅ ነበረው። ባር፣ ሬስቶራንት እና ናይት ክለብ ነበር። እዛ ወደ 52 ዓይነት ምግብ እሠራ ነበር። 16ቱ የጣሊያን ምግብ፣ የቀረውን የአውሮፓና የኢትዮጵያ ምግብ። በመጨረሻም ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች ቤቱ ተቃጠለ። ከዛ በኋላ "ኳሊቲ አምባሣደር" በተሰኘ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ውስጥ ሼፍ ሆኜ እሠራ ነበር።

ያሬድ 'ወርቃማ' መጽሔት ላይ በሠላም ሆቴል ቃጠሎ ምክንያት ምንም አይነት ኢንሹራንስ እንዳልተከፈለህ ተናግረህ ነበር። አሁንስ ምንም የኢንሹራንስ ካሣ አላገኘህም?

አቶ አየለ አሁንም ምንም አላገኘሁም። ለዚህ ነው ለሰባት ዓመታት ያህል ተቀጥሬ ሥሠራ ቆይቼ፤ ወደ ስዊድን መጥቼ ይሄንን 'አቢሲኒያ ሬስቶራንት'ን ይዤ ሥራ የጀመርኩት። 85 መቀመጫ ነው ያለው።

ያሬድ ሠላም ሆቴል መቼ ነበር የተቃጠለው?

አቶ አየለ በ1992 እ.ኤ.አ.

ያሬድ እዚህ መቼ ነው የመጣኸው?

አቶ አየለ በ2002። ሜይ 1 ቀን ነው ሥራ የጀመርኩት።

ያሬድ አቢሲኒያን ባለቤት ሆነህ ነው የጀመርከው?

አቶ አየለ አዎ! ራሴ ገዝቼው ነው ሥራ የጀመርኩት።

ያሬድ ባለቤትህ አቢሲኒያ ላይ ድርሻ (ሼር) አላት?

አቶ አየለ አዎ! ግማሽ ግማሽ የሁለታችን ነው። ሦስት ልጆች አሉን። እኔ ነኝ እንግዲህ ሙያውን የምሠራው።

ያሬድ እሷ በምን ታግዝሃለች?

አቶ አየለ እሷ በማስተናገድ ታግዘኛለች። ዕቃ ማቅረብ አልፎ አልፎ ታግዘናለች።

ያሬድ የምግብ ሥራ ሙያን በተመለከተ ትምህርት ቤት ተምረሃል?

አቶ አየለ ኖርዌይ ውስጥ የሁለት ዓመት ትምህርት ተምሬአለሁኝ - የአውሮፓን ምግብ አሠራር። በ1990 የሚስ ዩኒቨርስ ውድድር ያዘጋጀችው ኖርዌይ ነበረች። የተዘጋጀውም በኳሊቲ አምባሣደር ሆቴል ውስጥ ነበር። ለ82 የዓለም ውብ ቆንጆዎች እኔ ነበርኩ የመገብኳቸው።

ያሬድቁርስ ነበር የመገብካቸው?

አቶ አየለ አዎ! የዚያን ጊዜ የቁርስ ኃላፊ ነበርኩኝ።

ያሬድአቢሲኒያን ስትጀምሩ የተመዘገበ ካፒታላችሁ ስንት ነበር?

አቶ አየለ የተመዘገበ ካፒታላችን 100 ሺህ የስዊድ ክሮር ነው፤ ቤቱን የገዛነው አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ክሮነር ነ

ያሬድጥሬ ገንዘብ ከፍላችሁ ነው የገዛችሁት?

አቶ አየለ አዎ! እንግዲህ ሠርተናል። ምንም የተበደርነው ብድር አላገኘንም።

ያሬድአሁንስ ካፒታላችሁ ምን ያህል ደርሷል?

አቶ አየለ ካፒታላችን ብዙ ጊዜ በዕቃና በጥሬ ዕቃ ላይ ነው። ለምሳሌ የአገራችንን መጠጥ ነው ጠቅላላ የምናመጣው - በኮንቴይነር። ወደ 7 ሺህ ወይም 8 ሺህ ጠርሙስ ቢራዎች እናመጣለን። እና ካፒታላችን ብዙ ጊዜ ያለው ዕቃ ላይ ነው።

ያሬድካፒታላችሁ በግምት ምን ያህል ደርሷል?

አቶ አየለ ... ካፒታላችንን እንኳ መናገሩ ጥቅም የለውም። ግን ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለነው።

ያሬድትርፋማ ናችሁ?

አቶ አየለ በጣም አትራፊ ነን።

ያሬድበዓመት ምን ያህል ታተርፋላችሁ? ... በግምት

አቶ አየለ እኛ እራሳችን ደሞዝተኛ ነን። በየወሩ የ20 ሺህ ክሮነር ደምወዝተኞች ነን። እያንዳንዳችን። እና ካፒታላችን እያደገ ነው ያለው።

ያሬድአንተና ባለቤትህን ማለትህ ነው?

አቶ አየለ አዎ!

ያሬድስንት ሠራተኞች አሏችሁ?

አቶ አየለ ሰባት ሠራተኞች አሉን።

ያሬድከናንተ ሌላ ማለት ነው?

አቶ አየለ አዎ!

ያሬድአንድ ላይ ዘጠኝ ናችሁ?

አቶ አየለ ዘጠኝ ነን።

ያሬድስዊድናውያን ናቸው ወይንስ ኢትዮጵያውያን?

አቶ አየለ የማስተናገዱን ሥራ በሙሉ የሚሠሩት ስዊድናውያን ናቸው።

ያሬድሰባቱም?

አቶ አየለ  ወጥ ቤት ሦስት አሉን፣ አራት አስተናጋጆች አሉን።

ያሬድኢትዮጵያውያን ሠራተኞች የሏችሁም?

አቶ አየለ ኢትዮጵያውያን በረዳትነት ወጥ ቤት ውስጥ ነው የሚሠሩት።

ያሬድእዚህ ስዊድን ውስጥ መጥታችሁ ይህንን ሥራ ስትጀምሩ ምን ዓይነት የተሻለ የንግድ ሕጎችና ለንግድ የተቻቹ ሁኔታዎች አጋጠሟችሁ፤ ከዚህ በፊት ከነበራችሁ ልምድ የተለዩና ጠቃሚ የሆኑ?

አቶ አየለ ስካንዲኔቪያን የንግድ ሕግ ለየት ይላል። የኖርዌይ በጣም የጠበቀ ነው። አሠራሩም ሕጉም። የምግብ አሠራር ችሎታ የሌለው ዝም ብሎ መሥራት፣ መክፈት የማይችልበት ደረጃም አለ - ኖርዌይ ውስጥ። ስዊድን ውስጥ ግን ቀለል ያለ ነው። ሁሉም ነገር ደረጃ አለው። ምግብን በሚመለከት በጣም ከፍተኛ ቁጥጥር አለ። የስዊድን ህዝብ ጠቅላላው ውጭ ወጥቶ መብላት ለምዷል። እና ስለዚህ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ እኛ ቤት 95 በመቶ ሴቶች ናቸው። ሴቶች ብዙ ጊዜ አዳዲስ ነገር የመሞከር ፍላጎት አላቸው። ስለዚህ ብዙ ጊዜ ደንበኞቻችን ሴቶች ናቸው - በግሩፕ መጥተው የሚቀምሱት።

ያሬድቅድም ልጠይቅህ የፈለግሁት ምን ዓይነት የተሻለ የንግድ ሕግ አለ? ለምሳሌ እዚህ ስዊድን ውስጥ አንድ ሰው የንግድ ሥራ ሲጀምር ለ6 ወራት ከቀረጥ ነፃ ይሆናል፣ እንዲሁም የተወሰነ ገንዘብ ይደጎማል። እንዲህ እንዲህ ያሉትን ነገሮች ለማለት ነው።

አቶ አየለ እኛ እዚህ አገር አዲስ ስለነበርንና የስዊድንን ሕግ ስለማናውቀው ምንም የተደረገልን ነገር አልነበረም። ነገር ግን ቢያንስ ስድስት ወር ያለታክስ መቆየት ነበረብን። እኛ ግን ከመጀመሪያው ወር ጀምረን ታክስ እየከፈልን ነበር የቆየነው። እናም አለፈን።

ያሬድእንዲካካስላችሁ አልጠየቃችሁም?

አቶ አየለ ሊያካክሱልን አልቻሉም። ወቅቱ አለፈ። እና ደግሞ ከመጀመሪያ ጀምረን ገበያው ስለነበረን ምንም አላገኘንም እንጂ፣ አዲስ ለሚከፍት ሰው ዕድሉ አለው። እና እንደገና ደግሞ እኔ ከአገር ቤት አንድ ጥሬ ዕቃ ለማምጣት፣ አገር ቤት ውስጥ ጉምሩክ ለብቻው የራሱ ሕግ አውጥቶ ወይኑን ለ15 ለ20 ቀን ከነመኪናው ያስረዋል። እዚህ ግን የተቦሪ (ጉተምበርግ) የተባለው ከተማ ልክ በመርከብ መጥቶ፣ አንድም ወደቦታው ሳልሄድ በስልክ ብቻ "ይህንን ክፈል፣ ይሄንን ጨርስ" ተብሎ መጨረሻ ቤቴ ድረስ ዕቃው ይደርሰኛል። በጣም ትልቁ ልዩነት እዚህ አገር ይሄ ነው። ማንኛውንም ነገር በስልክ መጨረስ ይቻላል።

ያሬድእንደነገርከኝ በጅቡቲ፣ በግብፅ፣ በኖርዌይና እዚህ በስዊድን በዚህ ሙያና የንግድ ዘርፍ ለብዙ ዓመታት ሠርተሃል። እነዚህን አገሮች በዚህ የንግድ ዘርፍ ጎቹና አፈፃፀማቸውን ከኢትዮጵያ ጋር እንዴት ታወዳድራቸዋለህ?

አቶ አየለ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕጉ ተቀምጧል። አሠሪና ሠራተኛው ግን የለም። ለምሳሌ ትልቅ ኮራፕሽን አለ። ለምሳሌ ይሄ የምታየው በርጩማ የአገር ቤት በርጩማ ነው። ሦስት እግር ነው። ከቸርችል ጐዳና ነው የገዛሁት። ደረሰኝ አለኝ። እኔ ግን ወደ ውጭ ማውጣት አቃተኝ። "አይወጣም!"። ቅርስ አደረጉት። የአባብያ አባ ጃፋር ወንበር አይደለም። ምንም አይደለም። እና ስዊድን የሚገኘው የኢትዮጵያ አምባሣደር ደውለውና ጽፈው እንኳን ሊወጣ አልቻለም። በመጨረሻ ላይ ግን በሰው ወጣ። ያ ማለት እንግዲህ ምንድን ነው? ኤልሲ ከፍቼ፣ አገሪቷ ውስጥ ፊት ለፊት የምታገኘውን ዕቃ እምቢ ብለውኝ፤ ግን በሌላ ጎን ይወጣል። ትልቁ ችግር ያገራችን ይሄ ነው።

ቡና ለምሳሌ እኔ በዓመት 200 ኪሎ አይደለም በወር 200/300 ኪሎ ማውጣት እፈልጋለሁ። "300 ኪሎ ማውጣት አትችልም። ኮንቴይነር ሙላ" ይላሉ። እና እንዲህ እንዲህ አይነቱ ሲስተም መጥፋት አለበት። አገሪቷ እንድታድግ ከተፈለገ፣ የሚፈልግ ሰው 50 ኪሎም ይሁን ምን፤ ኤልሲ ይክፈትና በሕጋዊ መንገድ ያውጣ።

ያሬድበአዋሽ ወይን ጠጅ ፋብሪካ የሚመረት በጠርሙስ የታሸገ ጠጅ ወደ ስዊድን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስገባኸውና እያስገባህ ያለኸው አንተ መሆንህን ነግረኸኝ ነበር። ስለሱ ልታጫውተኝ ትችላለህ?

አቶ አየለ እንግዲህ ከአዋሽ ወይን ጠጅ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ... በጣም ጎበዝ ሰው ነው። በጣም ለአገሪቷና ለድርጅቱ እድገት የሚፈልግ ሰው ነው። በእውነቱ ላመሰግነው እፈልጋለሁ። አቶ ረዘነ ይባላል። ከሱ ጋር ተመካክረን ነው እንግዲህ ይህንን ምርት የጀመርን። አሁን ወደ አሜሪካም እየተላከ ነው ያለው - ይሄ ጠጅ። ለአሜሪካ ትንሽ ጣፋጭነት ይፈልጋሉ። እኔ ደግሞ ትንሽ እንዲመር። በየጊዜው በሚልኩልኝ ላይ የሕዝቡን፣ የጠጭውን አስተያየት እየሰጠ፣ አሁን በሚፈለገው ደረጃ ላይ ደርሷል። እስካሁን ምንም እንከን የለውም። አንድ ዓመት በላይ የተቀመጡ ጠጆች አሉ - ጥራታቸውን ለማቆየት። ጠጁም ወይኑም ኳሊቲ ነው። ብዙ ሰዎች ወደውታል። በቅርብ ጊዜ 'ሲስተም ቦላጌት' የሚባለው የስዊድን ብቸኛው የመጠጥ አከፋፋይ ሊገዛው ነው።

ያሬድጠላስ በፋብሪካ ተመርቶ፣ በጠርሙስ መታሸግ የሚጀምረው መቼ ይመስልሃል?

አቶ አየለ ጠላ እንኳ በፋብሪካ ሊቀርብ የሚችልበት ደረጃ የለም። ለምን? ታሽ የመቆምጠጥ ፀባይ አለው። ጠጅን ለሚፈለገው ዓለ ኢትዮጵያ ማቅረብ ትችላለች። ደረጃውንም የጠበቀ ስለሆነ። ቢራዎቹንም ማከፋፈል ጀምረናል።

ያሬድከኢትዮጵያ ስንት ዓይነት ቢራዎች ታመጣለህ?

አቶ አየለ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ባቲና ካስትልን እናመጣለን። በቅርብ ጊዜም ዳሽንን እጀምራለሁ። አምቦ ውሃም አለን።

ያሬድየትኞቹን የወይን ጠጆች ታስመጣለህ?

አቶ አየለ ከቀይ ወይን አክሱሚት፣ ዱከም፣ ጉደር። ከነጭ ወይን ክሪስታልና ከሚላ ናቸው። ከሚላ በወይን ኤክስፐርቶች እዚህ አገር ተደናቂ ሆኗል።

ያሬድየትኛው የወይን ጠጅ ነው እዚህ ስዊድን ውስጥ ተወዳጅ የሆነው?

አቶ አየለ ከሚላ ነጭ ወይን በጣም ተደንቋል።

ያሬድከቀይ ወይንስ?

አቶ አየለ ከቀይ ወይን ዱከም ነው። ብዙዎች አክሱሚትን ይወዱታል። ጣፋጭነት ስላለው ብዙ ጊዜ ሴቶቹ በጣም ይወዱታል።

ያሬድከቢራዎቹስ?

አቶ አየለ ከቢራዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ በጣም ተወዳጅ ነው። እዚህ አገር በ17ኛው ክ/ዘመን መሃል ከተማው ላይ ሐውልት አለ። በብር የተሠራ። ልክ እንደ አፄ ምኒልክ አደባባይ ላይ እንዳለው። እና ከታሪክም፣ ከኃይማኖትም ጋር አያይዘው በጣም ይወዱታል። ቅ/ጊዮርጊስ በጣም ይሄዳል።

ያሬድጠጁስ እንዴት ነው?

አቶ አየለ በጣም ጥሩ ነው። በብርሌ ሲጠጡት መጨረሻው ላይ አንገታቸውን ወደላይ እስከሰማይ ድረስ ቀና ስለሚያደርጉት አንዳንዴ ሳቅ ያመጣል እንጂ ደህና ነው።

ያሬድከሲስተም ቦላጌት ጋር ምን ዓይነት ደረጃ ላይ ደርሳችኋል? (ሲስተም ቦላጌት የስዊድን ብቸኛው መጠጥ አከፋፋይ ሲሆን ካለእሱ ፈቃድ ውጭ የአልኮል መጠጥ ወደ ስዊድን አስገብቶ ማከፋፈልም ሆነ መሸጥ አይቻልም)

አቶ አየለ "ጠቅላላ የኢትዮጵያን የመጠጥ ምርት ብታቀርቡልን እንገዛችኋለን" ብለው ስምምነት ላይ ደርሰናል። አሁን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እዚህ ያለውን ኤምባሲ አነጋግረናቸው፣ እነሱም ቀረጥ ነፃ ወይም ቅናሽ እንዲሆንላቸው እየሞከሩ ነው ያሉት።

ያሬድእዚህ አገር የመጠጥ ቀረጥ ምን ያህል ነው?

አቶ አየለ በአንድ ሊትር ወይን 22 ክሮነር ከዜሮ ስምንት ሳንቲም ነው ቀረጡ። ያ ተከፍሎ ዋጋ የለውም፤ የጣሊያን ያለቀረጥ ገብቶ እዚህ በጣም ርካሽ ስለሚሸጥ።

ያሬድቢራሳ?

አቶ አየለ ቢራ በአንድ ጠርሙስ 7 ክሮነር ከ20 ሣንቲም ቀረጥ አለው።

ያሬድሌሎቹስ አልኮሎች?

አቶ አየለ አልኮሎች በጣም ውድ ናቸው።

ያሬድአልኮል ትሸጣለህ?

አቶ አየለ አዎ! አሁን በቅርብ ጊዜ እንዲያውም የቡና አረቄና የብርትኳን አረቄ አምጥቼ በጣም ተወዳጅ ሆኗል። በሚቀጥለው እንግዲህ እሱም ግማሽ ኮንቴይነር ይገባ ይሆናል።

ያሬድየትምህርት ደረጃህን ልትነግረኝ ትችላለህ - በኢትዮጵያና በውጭ?

አቶ አየለ ኢትዮጵያ ውስጥ እኔ መሃል ከተማ ቁጭራ ውስጥ ነው የተወለድሁት። ኃብተጊዮርጊስ ድልድይ። እዛ እስከ 12ኛ ክፍል ተምሬአለሁ። 12ኛ ክፍል ጨርሼ ነው እንግዲህ ዕድገት በሕብረት ዘመቻ ጣቢያው ተሰርዞ ከዛ ወደ ንግድ ዓለም የገባሁት። ከዚያ ኖርዌይ ውስጥ የ2 ዓመት የምግብ ሙያ ነው የተማርኩት።

ያሬድዲፕሎማ ነው፣ ዲግሪ ነው፣ ... ወይስ?

አቶ አየለ እዚ የሚሰጠው እንደ ዲፕሎማ አይነት ወረቀት ነው። በዚያ ወረቀት ማንኛውም አይነት ሆቴል ውስጥ ተቀጥረህ መሥራት ትችላለህ - በሙያው።

ያሬድበየትኛውም ዓለም?

አቶ አየለ አዎ! በየትኛውም ዓለም። እኔ እንግዲህ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ውስጥ ነው ተቀጥሬ ሼፍ ሆኜ ስሠራ የቆየሁት፣ መጨረሻ ላይ ማለት ነው። 350 አልጋ ያለው ሆቴል ውስጥ ነው።

ያሬድ እዚህ አገር ያሉት ጋዜጦች አቢሲኒያ ሆቴልን በማስተዋወቅ ረገድ ስለሚሠሩት ሥራ ልትነግረኝ ትችላለህ?

አቶ አየለ አቢሲያን በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ጋዜጦች አውጥተውናል። እዚያ ፊት ለፊት የምታየው "ዮርደን ሩንት ፖ ሬስቶራንገር" ከ18 የዓለም ምርጥ ሬስቶራንቶች ውስጥ አንደኛ አቢሲኒያ ነው ብለው ነው ያወጡት። 'አፍቶን ብላደት' (ከስዊድን ጋዜጦች አንዱ) ነው ያወጣው። ከዚህ በፊትም አፍቶን ብላደት "እንደሽቶ ይሸታል ... ከእንግዲህ ወዲህ የቱርክ፣ የጃፓን፣ ... ምግብ መብላት ምን ያረጋል? ልዩ በእጅ የሚበላ የኢትዮጵያ ምግብ መጥቷል ..." እያሉ ነው የሚያስተዋውቁልን፣ ጋዜጣ ላይ የሚጽፉልን። እና አሁን ባለፈውም 'ስቨንስክ ዳግብላድ' ቅድም ለአንተ አንድ ትርጉሙን ሰጥቼሃለሁ። "አቢሲኒያ ሄዳችሁ ቋንጣ ፍርፍርና ጎረድ ጎረድ ሳትበሉ፣ ጠጅ ሳትጠጡ እንዳትቀሩ" ብለው ነው የፃፉት። "እንደውም እኔ እንድበላው አልፈለጉም ነበር። 'ይሄ ለአገራችን ሰው ነው እንጂ ለውጭ ሰው አይሆንም' ብለውኝ፤ እኔ ግን ሞከርኩት። ተስማማኝ" ብሎ ነው ጋዜጠኛው የፃፈው።

ያሬድማስታወቂያ ጋዜጦች ላይ ታወጣለህ? አንዳንዶቹን አይቻቸዋለሁ።

አቶ አየለ አዎ! አልፎ አልፎ ከፍለን እናወጣለን። አልፎ አልፎም እራሳቸው መጥተው ተመግበው ነው የሚጽፉልን። አሁን የፊት ለፊቱ የጋዜጣ ገፅ ላይ የወጣው፣ እኛ ከፍለን እናውጣው ብንል 250 ሺህ ክሮነር ግምት ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጀመሪያ በረራውን ወደስዊድን ሲጀምር የፊት ገፅ ላይ ማውጣት ፈልጎ 250 ሺህ ክሮነር ነው የተጠየቀው። ለእኛ ግን በነፃ ነው የሚያወጡልን። የስዊድን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በ1994 እ... የዓለም ዋንጫ 3ኛ የወጣ ጊዜ የፊት ለፊት ገፅ ላይ አልወጣም። እኛ ግን ከ4500 ሬስቶራንቶች ያሸነፍን ጊዜ የፊት ለፊት ገፅ ላይ ነው የወጣነው። እዚያ ላይ የተፃፈልን "በመጡ በአንድ ዓመታቸው ስቶክሆልምን አንቀጠቀጡ" ተብሎ ነው።

ያሬድበ2003 የወርቅ ሽልማቱን ካገኛችሁ በኋላ ሌላ ሽልማት አግኝታችኋል?

አቶ አየለ ባለፈው ደግሞ በቴሌቭዥን በተደረገው ውድድር 2ኛ ወጥተናል።

ያሬድማን ነበር ውድድሩን ያዘጋጀውና የሸለማችሁ?

አቶ አየለ የስዊድን መንግሥት ቴሌቭዥን ጣቢያው ነው። 'ስቨሪየ አንድ' (ስዊድን አንድ) የሚባለው።

ያሬድየሥራ ሰዓታችሁ ...?

አቶ አየለ የሥራ ሰዓችን እንግዲህ አገር ቤት ከሰሙት ይደነግጣሉ። ከጠዋቱ 3 ሰዓት (በሐበሻ) እስከ ምሽቱ 6 ሰዓት እንሠራለን።

ያሬድ በየቀኑ?

አቶ አየለ አዎ! በየቀኑ ዓመት ሙሉ እንደዚያ ነው የምሠራው እኔ።

ያሬድመቼ ነው የምታርፉት?

አቶ አየለ እንግዲህ አንደኛችንን እስከመጨረሻ በምንሄድበት ጊዜ ይሆናል። (ከሣቅ ጋር) ... በዓመት ጁን ላይ አንድ ወር ሁል ጊዜ እንዘጋለን።

ያሬድሙሉ ለሙሉ ሬስቶራንቱን ዘግታችሁ?

አቶ አየለ አዎ!

ያሬድበእረፍቱ ጊዜ ሠራተኞቹ ደምወዛቸው ይከፈላቸዋል?

አቶ አየለ አዎ! የወር ደምወዛቸውን እንከፍላለን።

ያሬድሠራተኞችህን ይዘህ ኢትዮጵያ ለመሄድ እንዳሰብክ ነግረኸኝ ነበር። ስለሱ ለአንባብያን ልትነግርልኝ ትችላለህ?

አቶ አየለ ከዚህ በፊት አንድ ወንድ አስተናጋጅ ነበረን። እሱ በጣም የኢትዮጵያን ምግብ ወዶት ... እና "እባክህ!" ሲለኝ፤ ለአንድ ሣምንት ኢትዮጵያ ልኬው፣ ተመግቦ ... አዋሽ ፓርክን አየ። ከዚያ መጥቶ ለእንግዶቼ አገሬን ያኮራልኝ ጀመር። ስለአገሬ ባህል፣ ስለአገሬ ምግብ እያስረዳልኝ ... ለእኔም ትልቅ ገበያ አገኘሁበት። አሁንም እነኝህ በራሳቸው ትራንስፖርት ነው የሚሄዱት፣ እኔ እዚያ ያለውን ወጪ ነው የምችላቸው። ግን ሲመለሱ እርግጠኛ ነኝ ምን ያህል ባህልና ታሪክ እንዳለን አይተው ስለሚመለሱ፤ ትልቅ የሥራ ዕድል እንደሚኖረኝ አልጠራጠርም።

ያሬድመጀመሪያ ለብቻው የጋበዝከውን ሠራተኛህን የትራንስፖርቱን ወጪ የቻልከው አንተ ነበርክ?

አቶ አየለ አዎ! ሁሉንም ወጪውን ችዬ ነው የላክሁት። "ጥሬ ክትፎ ብቻ እንዳታበሉት፤ እዚህ (ስዊድን) ክትፎ ይበላል" ብዬ ነው የላክሁት፤ ስጋው ምናልባት ሌላ ችግር እንዳያመጣበትና እኔም ላይ እንዳይመጣ።

ያሬድኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ እንዳንተ በተመሳሳይ ሙያና ንግድ ለተሰማሩ ሰዎች የምትለው ነገር አለ?

አቶ አየለ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ልመክረውና ላበረታታው የምችለው እንግዲህ ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆቴልም፣ ግሮሰሪም፣ ምግብ ቤትም፣ ... በተከፈተበት ሰዓት ለ6 ወር ባለቤቱ ይቆማ፣ ተፍ ደፍ ይልና ከዛ በኋላ ቤቱን ይረሳዋል። እሱ ከረሳው የቤቱ ገበያ እንደተረሳ ማወቅ አለበት። ባለንብረት ሁልጊዜም ከሠራተኛው በላይ መሥራትም፣ መትጋትም አለበት። በየደቂቃው በላተኛው ጋር እየሄደ "ምን ልጨምር? ምን ጎደለ? ..." ባህላችንም ነው። የሚስተካከልም ካለ መጠየቅ አለበት። የኛ ሰው መጥፎ ብትነግረው ቆጣሃል። ጥፋታችንን መቀበል አለብን። የሚሠራ ሰው ይሳሳታል። መበርታት አለብን። መትጋት አለብን። ... ብዙ ጊዜ ኪሣቸው ውስጥ ነው የሠሩበት ገንዘብ የሚቀመጠው። መሳቢያ ውስጥ እንኳ ገንዘብ አይቀመጥም። ኪሱ እየከተተ ቡናው ቤት ውስጥ ራሱ እየጠጣ ነው የሚያስተናግደው። ስካንዲኔቪያን አገሮች ውስጥ ውሃ ነው 'ጂ መጠጣት የምትችለው፤ አልኮል እየጠጣህ ማስተናገድ አትችልም። እና ብዙ ከምንማራቸው ነገሮች አንዱ ይሄ ነው። መበርታትና መጠንከር ያለብን እንዲህ እንዲህ ያለውን ነው። ገበያም በአንድ ጊዜ አይመጣም። አለመሰልቸት ዋናው ነው።

ያሬድበአገራችን ወግና ባህል አድርገን ከያዝናቸው ነገሮች አንዱ ወንድ ልጅ ጓዳ ገብቶ መሥራት የለበትም የሚለው ነው። ወንድ ልጅ በቤት ውስጥ ሥራ ባለቤቱን አያግዛትም። በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወንዶች ከሚስቶቻቸው ጋር በዚህ ምክንያት ችግ ይፈጠርባቸዋል። ይጨቃጨቃሉ። አልፎ አልፎም ይፋታሉ። ይህንን በተመለከተ ምን አይነት አስተያየት አለህ?

አቶ አየለ ይሄ እንግዲህ በጣም መጥፎ ባህል ነው። ጓዳ ገብቶ መሥራት ምንም ነውር የለውም። ተሳስቦ መኖርና ማደር ደግሞ በጣም የተሻለ ነው። አገር ቤት ምንድን ነው የጊዜው ሁኔታና የሠራተኛም ዋጋም ርካሽ ስለሆነ ከአቅሙ በላይ ገብታ ሴትዮዋም ከምትሠራ ወንዱም ከሚሠራ ብለው ሠራተኛ ይቀጥራሉ። ልጆቻቸውን በደንብ ሊያሳድጉበት በሚችሉበት ገንዘብ ለሠራተኛ አውጥቶ፤ ዕድገት የለውም። እዚህ አገር ደግሞ በይበልጥ እኔ እማውቀው ስካንዲኔቪያ ውስጥ፣ ኖርዌይ ጠቅላይ ምኒስትሯ የቤት ሠራተኛ የላትም። በበጋ ወራት ራሷ ነች መኪናዋን የምታጥበው። ባሏ ጓዳ ገብቶ ይሠራል። እሷም ትሠራለች። የንጉሡ ልጆች እንኳ በክብረ በዓላት ቀን ነው ወጥ ቤት ያላቸው እንጂ የራሳቸውን ምግብ ሠርተው በልተው ነው ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱት። እና ይሄን ይሄን ባህል እኛ አገር መማር አለብን። እኛ አገር ትንሽም ዕድገት ስናገኝ ወጪያችን ይበዛል። ኑሯችንንም አናውቀውም። ተሳስበን ብንሠራና ወንዱ ይበልጥ ቢያግዛቸው (ሴቶቹን) የልጆቹንም ዕድገት፣ ... ምንም ማድረግ ይቻል ነበር።

ያሬድ... ለምሳሌ በ1940 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን ስዊድናዊ የኢትዮጵያ መንጃ ፈቃድ አሳይተኸኛል። እንዲህ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ትሰበስባለህ ... ስለነሱ ልታጫውተኝ ትችላለህ?

አቶ አየለ አሁን እኝህ መንጃ ፈቃዳቸውን ያየኸው ሰው በ1940 ዓ.ም. የመጀመሪያው አየር ኃይል ሲቋቋም እዚያ የነበሩ ሰዎች ናቸው። እኔ ጋር ይመጣሉ። ከ50 ዓመት በኋላ ትዝታቸውን የተወጡት እዚህ እኔ ጋር መጥተው ነው። እንደውም መጀመሪያ ሲገቡ "ውሻ አለ?" ነው ያሉኝ። ... (ከሣቅ ጋር)

ያሬድለምን?

አቶ አየለ ድሮ አገር ቤት እያሉ "ውሻው ታስሯል? ... ቆይ ውሻው ይታሰር ..." ሲሉ የነበረውን አስታውሰው "ውሻ አለ?" አሉኝ። ሊያስቁኝ ፈልገው ነው። ብዙዎቹ እዚህ የሚመጡት ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ ናቸው። በጣም ደስተኞች ናቸው። እና እኝህ ሰውዬ (ባለመንጃፈቃዱ) የመጀመሪያው የአየር ኃይል ፓይለት ናቸው። ከዛም ስዊድን ተመልሰው እንደገና ወደ ኢትዮጵያ ሄደው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ሠርተዋል። ከዛ በኋላ 'ሳስ' የሚባለው ስካንዲኔቪያን ኤርላይንስ ላይ ይሠሩ ነበር። አሁን የ88 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ናቸው። ከሳቸው ሌላም በ1940 ዓ.ም. የጃንሆይ የመጀመሪያው ሹፌር የነበሩ ሰውዬ እኔ ጋር መጥተው መንጃ ፈቃዳቸውን አሳይተውኛል።

ያሬድእነኝህን ስብስቦችህን በተለይ ፎቶግራፎቹን ኢትዮጵያውያን ያዩአቸው ዘንድ መድረክ ለማዘጋጀት ብንሞክር ልትተባበረን ትችላለህ?

አቶ አየለ እችላለሁ!

ያሬድአመሰግናለሁ!

አቶ አየለ ምንም አይደል!

ያሬድተጨማሪ ልትናገር የምትሻው ነገር ካለ?

አቶ አየለ መናገር የምፈልገው ... እዚህ ስዊድን ውስጥ ሁለት ሬስቶራንቶች ነን ያለነው። ምናልባት አንድ ሚሊዮን ህዝብ ስቶክሆልም ውስጥ ስላለ፣ እዚህ ያለው ኢትዮጵዊ አሁንም አልተንቀሳቀሰም። መንቀሳቀስ አለበት። ቢቻል 10 ... 15 የኢትዮጵያ ሬስቶራንቶች ቢከፈ ገበያችንም ያድጋል። ከዚህ በተጨማሪ እዚህ ያለው የቅባት ሱቅ፣ የበርበሬ ሲቅ፣ ... የሚጠብቀው ኢትዮጵያዊውን ተጠቃሚዎችን/ገዢዎችን ብቻ ነው። ያ ከሚሆን ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየጊዜው ስለሚመላለስ ኢትዮጵያዊው እንዲያውም በርበሬም፣ ሽሮም፣ ... ከሱቅ መግዛት ላይፈልግ ይችላል። ለነጩ ኅብረተሰብ የምትሆን 50 ግራምም ብሆን፣ ... ልክ እንደ ሽቶ ... ትንሽ ትንሽ ግራም መሸጥ ቢችል ... ነጩ ገበያ ውስጥ ቢገባ ... አሁንም የተለያየ ሱቅ መክፈት ይችላል። ገበያችንንና የአገራችንን ጥቅምም ማሳደግ እንችላለን። እኔ አሁን 20 ኪሎ በርበሬ ባመጣ'ኮ የአገሬን ገበሬ ጭምር ነው የምጠቅመው። ስለዚህ እንደዚህ እንደዚህ ገበያ ውስጥ ነው መግባት ያለብን እንጂ፤ እዚህ ካለው ኢትዮጵያዊ ብቻ ገበያ መጠበቅ የለብንም። ይህንን ነው መናገር የምፈልገው።

ያሬድየልጆችህን ዕድሜ ብትነግረኝ?

አቶ አየለ አማኑኤል 13 ዓመት ሆኖታል። ኤደን 8 ዓመቷ ነው። ፅዮን 4 ዓመቷ ነው። አማኑኤል ሁልጊዜ ቀይ ክትፎ ነው የሚበላው። ጎረድ ጎረድ ነው። ፍቅሩ ሥጋ ነው።

ያሬድየት ነው የተወለዱት?

አቶ አየለ ሦስቱም ኖርዌይ ነው የተወለዱት።

ያሬድበስደት ስንት ዓመት ኖረሃል ማለት ነው?

አቶ አየለ 19 ዓመት ሊሞላኝ ነው።

ያሬድበጣም አመሰግናለሁ!

አቶ አየለ ምንም አይደለም!

ማስታወሻ፦ የአቢሲኒያን ሙሉ አድራሻ፣ የምግብ ሜኑ፣ ... እንዲሁም ተጨማሪ መረጃ ለመፈለግ የምግብ ቤቱን ድኅረ-ገፅ ይመልከቱ

Hosted by www.Geocities.ws

1